1አንድ ቀንም ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ሌሎች ኅጢአተኞች ሁሉ ኢየሱስን ለመስማት መጡ።
2ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን፣ "ይህ ሰው ኅጢአተኞችን ይቀበላል፤ ከእነርሱም ጋር ይበላል" በማለት እርስ በርሳቸው አጒረመረሙ።
3ኢየሱስ እንዲህ በማለት ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤
4"ከእናንተ መካከል መቶ በጎች ያሉት ከዚያም ከእነርሱ አንዱ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በዱር ትቶ የጠፋበትን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልግ የማይሄድ ማንነው?
5ባገኘውም ጊዜ ከመደሰቱ የተነሣ በጫንቃው ይሸከመዋል።
6ወደ ቤቱም ሲመለስ ወዳጆቹንና ጎረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ፣ 'የጠፋብኝን በጌን አግኝቻለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ' ይላቸዋል።
7እንዲሁም ንስሓ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሓ በሚገባ በአንድ ኅጢአተኛ በሰማይ ታላቅ ደስታ እንደሚሆን እነግራችኋለሁ።
8ወይስ ዐሥር የብር ሳንቲሞች ያላት ሴት ከዐሥሩ አንዱ ቢጠፋበት፣ እስከምታገኛው ድረስ መብራት አብርታ፣ ቤቷንም ሁሉ ጠርጋ በትጋት የማትፈልግ ሴት ማን ናት?
9ባገኘችም ጊዜ ወዳጆቿንና ጎረቤቶቿን ሁሉ በአንድነት ጠርታ፣ 'የጠፋብኝን የብር ሳንቲሜን አግኝቻለሁና ኑ ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ' ትላቸዋለች።
10"እንደዚሁም ንስሓ በሚገባ በአንድ ኅጢአተኛ በእግዚአብሔር መላአክት ፊት ታላቅ ደስታ እንደሚሆን እነግራችኋለሁ።"
11ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አለ፣ "አንድ ሰው ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤
12ታናሹ ልጅም አባቱን፣ 'አባቴ ሆይ፣ በኋላ ከሀብትህ ከሚደርሰኝ ድርሻዬን ስጠኝ' አለው። አባቱም ሀብቱን ለሁለቱም ልጆቹ አካፈላቸው።
13ከጥቂት ቀናትም በኋላ ታናሹ ልጅ ድርሻውን ይዞ ወደ ሩቅ አገር ሄደ። እዚያም ገንዘቡን ሁሉ አላግባብ እየጨፈረ አባከነ።
14እርሱም ያለውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ በዚያ አገር ጽኑ ራብ ሆነ። ከዚህም የተነሳ ችግር ላይ ወደቀ።
15በዚያም አገር ዐሳማ ያረባ ወደ ነበረ ወደ አንዱ ሰው ዘንድ ሄዶ ተቀጠረ። ሰውዬው ዐሳማዎችን እንዲጠብቅለት አሰማራው።
16እርሱም የሚበላውን ምግብ የሚሰጠው ስላልነበረ፣ ዐሳማዎቹ ከሚመገቡት መኖ ለመብላት ይፈልግ ነበር።
17እርሱም አንድ ቀን ወደ ልቡ ተመልሶ እንዲህ አለ፤ 'ምግብ የሚተርፋቸው የአባቴ ቤት ሠራተኞች ስንት ናቸው?
18እኔ ግን እዚህ የምበላውን አጥቼ በራብ እሞታለሁ! ተነሥቼ ወደ አባቴ ቤት ልሂድና እንዲህ ልበለው፤ "አባቴ ሆይ፣ በእግዚአብሔርና በአንተ ፊት ኅጢአት አድርጌአለሁ።
19ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ መጠራት አይገባኝም፤ ከአገልጋዮችህ እንደ አንዱ ቊጠረኝ።"
20ስለዚህ ታናሹ ልጅ ተነሥቶ ወደ አባቱ መጣ። ልጁ ገና ከሩቅ እየመጣ ሳለ፤ አባቱ አይቶ በርኅራኄ ሮጦ ተቀበለውና ዐቅፎ ሳመው።
21ልጁ፣ 'አባቴ ሆይ፣ በእግዚአብሔርና በአንተ ፊት ኅጢአት አድርጌአለሁ። ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም' አለ።
22አባቱም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ "ፈጥናችሁ ምርጡን ልብስ አምጡና አልብሱት፣ በጣቱ ቀለበት፣ በእግሩም ጫማ አድርጉለት።
23ከዚያም የሰባውን ወይፈን አምጡና ዕረዱት። እንብላ፤ እንደሰት።
24ይህ ልጄ ሞቶ ነበረ አሁን በሕይወት አለ፤ ጠፍቶም ነበረ ተገኝቶአል።" ይደሰቱም ጀመር።
25ታላቁ ልጅ በዕርሻ ቦታ ነበረ። ወደ ቤትም በተቃረበ ጊዜ፣ ሙዚቃና ጭፈራ ሰማ።
26ከአገልጋዮቹ አንዱን ጠርቶ፤ ምን እየሆነ እንዳለ ጠየቀው። አገልጋዩም፣ 'ወንድምህ መጥቶአል።
27በደኅና ስለተመለሰም አባትህ የሰባውን ወይፈን አርዶለታል' አለው።
28ታላቁ ልጅ ይህን ሰምቶ ተቈጣ፤ ወደ ቤትም ሊገባ አልፈለገም። አባቱም ወጥቶ እንዲገባ ለመነው።
29እርሱ ግን አባቱን እንዲህ አለው፤ 'እነሆ፣ ይህን ሁሉ ዘመን እንደ ባሪያ አገለገልሁህ፤ ከትእዛዝህ አንዱንም ሳላጎድል ከአንተ ጋር ኖርሁ፤ ከባልንጀሮቼ ጋር እንድደሰት አንዲት የፍየል ግልገል እንኳ አልሰጠኸኝም፤
30ነገር ግን ይህ ልጅህ ገንዘብህን ሁሉ ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር አባክኖ ሲመጣ፣ የሰባውን ወይፈን አረድህለት።'
31አባቱ እንዲህ አለው፤ “ልጄ ሆይ፣ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ ያለኝ ሁሉ የአንተ ነው።
32ነገር ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበር፤ አሁን በሕይወት አለ፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአል። ስለዚህ ልንበላና ልንደሰት ይገባናል።'