መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሉቃስ 14

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በሰንበት ቀን ኢየሱስ ከፈሪሳዊያን አለቆች ወደ እንዱ ቤት እንጀራ ሊበላ በገባ ጊዜ፣ የሚያደርገውን ለማየት በቅርበት ይጠባበቁት ነበር፡፡
2በዚያም በእጅና በእግር ዕብጠት የሚሠቃይ አንድ ሰው በኢየሱስ ፊት ነበር።
3ኢየሱስ የአይሁድ ሕግ ዐዋቂዎችንና ፈሪሳውያንን፣ "በሰንበት ቀን መፈወስ በሕግ ይፈቀዳል ወይስ አይፈቀድም? "ብሎ ጠየቃቸው፡፡
4እነርሱ ግን ዝም አሉ፡፡ ኢየሱስ የታመመውን ሰው ይዞ ፈወሰውና አሰናበተው፡፡
5ቀጥሎም ኢየሱስ፣ "ከእናንተ ልጅ ወይም በሬ በሰንበት ቀን በጒድጓድ ውስጥ ቢወድቁ ወዲያውኑ የማያወጣቸው ማን ነው?" አላቸው።
6እነርሱ ለእነዚህ ነገሮች መልስ መስጠት አልቻሉም፡፡
7ኢየሱስ በግብዣ ቦታ የከበሬታ ወንበር ለመያዝ ሲሽቀዳደሙ በተመለከት ጊዜ እንዲህ በማለት አንድ ምሳሌ
8ነገራቸው፤ "አንድ ሰው ወደ ሰርግ ግብዣ ቢጠራህ በመጀመሪያ በከበሬታ ቦታ አትቀመጥ፣ ምናልባት በዚያ ቦታ የሚቀመጥ ከአንተ ይልቅ ክብር የሚሰጠው ሰው ተጋብዞ ይሆናል፡፡
9ሁለታችሁንም የጋበዛችሁ ሰው መጥቶ፣ 'ይህን ቦታ ለሌላ ሰው ልቀቅለት' ይልሃል፣ ከዚያም አንተ በሃፍረት ወደ ዝቅተኛ ቦታ ትሄዳለህ፡፡
10ነገር ግን ወደ ግብዣ ስትጠራ በዝቅተኛ ቦታ ተቀመጥ፤ አንተን የጋበዘህ ሰው መጥቶ፤ ወዳጄ ሆይ፣ 'ወደ ከፍተኛ ስፍራ መጥተህ ተቀመጥ' ይልሃል፡፡ ከዚያም በተጋባዦቹ ፊት ሁሉ የተከበርህ ትሆናለህ፡፡
11ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ዝቅ ዝቅ ይላል፡፡ ራሱንም ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ደግሞ ከፍ ከፍ ይላል፡፡
12ኢየሱስ ደግሞ ጋባዡን ሰው ደግሞ እንዲህ አለው፤ "የምሳ ወይም የራት ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ መልሰው ይጋብዙኛል በማለት ብድራትን በመፈለግ ወዳጆችህን ወይም ወንድሞችህን ወይም ዘመዶችህን ወይም ሀብታም ጎረቤቶችህን አትጋብዝ፡፡
13ነገር ግን ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችን፣ የአካል ጒዳተኞችን፣ ሽባዎችንና ዐይነ ስውራንን ጥራ፡፡
14ይህን በማድረግህ እነርሱ መልሰው ሊከፍሉህ ስለማይችሉ፣ የተባረክህ ትሆናለህ፡፡ በጻድቃን ትንሣኤ ቀንም እግዚአብሔር ብድራትህን ይከፍልሃል፡፡
15በማዕድ ተቀምጠው ከነበሩት አንዱ ኢየሱስ የተናገራውን ሰምቶ፣ "በእግዚአብሔር መንግሥት ማዕድ ተቀምጦ እንጀራ የሚበላ ሰው የተባረከ ነው" አለው፡፡
16ኢየሱስ ግን እንዲህ አለው፤ "አንድ ሰው ትልቅ የእራት ግብዣ አዘጋጅቶ ብዙ ሰዎችን ጋበዘ፡፡
17የግበዣውም ዝግጅት በተጠናቀቀ ጊዜ ወደ እራት ግብዣው ወደ ተጋበዙት ሰዎች፣ 'ሁሉ ተዘጋጅቶአልና ወደ ግብዣው ኑ' ብሎ መልእክተኞችን ላከ፡፡
18ነገር ግን እያንዳንዱ ተጋባዥ ከግብዣው ለመቅረት ምክንያት መደርደር ጀመረ፡፡ የመጀመሪያው፤ "መሬት ስለ ገዛሁ ሄጄ ማየት አለብኝባ ይቅርታ አድርግልኝ አለው፡፡
19ሌላው፣ 'አምስት ጥማድ በሬዎችን ገዝቻለሁ፣ እነርሱን ልፈትናቸው ስለምሄድ፤ ይቅርታ አድርግልኝ' አለው፡፡
20ሌላኛውም ሰው፣ 'ሚስት አግብቼ ሙሽራ ስልሆንሁ፣ ልመጣ አልችልም' አለ፡፡"
21አገልጋዩ ለጌታው እነዚህን ነገሮች ነገረው። ከዚያም የቤቱ ጌታ ተቈጥቶ አገልጋዩን 'ቶሎ ሄደህ በከተማው አውራ ጐዳናዎች ስላች መንገዶች ሁሉ ያሉ ድኾችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ዐይነ ስውራንን፣ ሽባዎችን ሁሉ ወደዚህ እንዲገቡ ጥራቸው' አለው።
22አገልጋዩም አለው፤ 'ጌታ ሆይ፤ ያዘዝኸኝን ሁሉ አድርጌአለሁ፤ አሁንም ትርፍ ቦታ አለ።'
23ጌታውም አገልጋዩን፣ 'ወደ ጎዳናዎችና ወደ ገጠር መንገዶች ውጣ፤ ቤቴም እንዲሞላ ያገኘሃቸውን ሁሉ እንዲገቡ ግድ በላቸው።
24"እላችኋለሁ፣ በመጀመሪያ ከተጋበዙት ከእነዚያ ሰዎች መካከል አንድ ሰው እንኳ ከእራቴ አይቀምስም' አለው።
25ሕዝብም ከኢየሱስ ጋር አብረው እየሄዱ ሳለ፣ እርሱ ዞር ብሎ እንዲህ አላቸው፤
26"ማንም ወደ እኔ ሊመጣ የሚወድ አባቱንና እናቱን፣ ሚስቱንና ልጆቹን፣ ወንድሞቹንና እኅቶቹን፣ እንዲያውም የራሱንም ሕይወት ስንኳ ስለ እኔ ብሎ ካልተወ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም፡፡
27የራሱንም መስቀል ተሸክሞ የማይከተለኝ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም፡፡"
28ከእናንተ አንድ ሰው ሕንጻ መሥራት ቢፈልግ ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገውን ገንዘብ በመጀመሪያ ተቀምጦ የማይተምን ማን ነው?
29መሠረቱን ሠርቶ መደመደም ቢያቅተው በዚያ የሚያልፉት ሁሉ ፣
30'ይህ ሰው መገንባት ጀምሮ መደምደም አቃተው እያሉ ይዘብቱበታል' ፡፡
31ወይም አንድ ንጉሥ ከሌላ ንጉሥ ጋር ሊዋጋ በሚነሣበት ጊዜ ሃያ ሺህ ሰራዊት አስከትቶ የሚመጣበትን በአሥር ሺህ ሰራዊት ለመመከት ተቀምጦ የማይመክር ማን አለ?
32መመከት የማይችል ከሆነ የሌላው ሰራዊት ገና ከሩቅ ሳለ መልእክተኛ ልኮ ዕርቅ ይጠይቃል፡፡
33እንዲሁም ከእናንተ ማንም ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም፡፡
34ጨው መልካም ነው፤ ነገር ግን ጨው ጣዕም ካጣ እንዴት ተመልሶ እንደ ገና የጨውነት ጣዕም ሊኖረው ይችላል?
35ለመሬትም ሆነ ለማዳበሪያነት የማይጠቅም በመሆኑ ወደ ውጪ ይጣላል፡፡ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ!"
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።