መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሉቃስ 13

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በዚያን ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ወደ ኢየሱስ መጥተው፣ የገሊላ ሰዎች ለእግዚአብሔር መሥዋዕት በሚያቀርቡበት ጊዜ፣ ጲላጦስ ስለ ገደላቸውና ደማቸውንም ከመሥዋዕታቸው ጋር ስላደባለቀባቸው ሰዎች ነገሩት፡፡
2ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ "እነዚያ የገሊላ ሰዎች ይህ ሁሉ የደረሰባቸው በዙሪያቸው ካሉት ከሌሎች የገሊላ ሰዎች ይልቅ ኅጢአተኞች ስለ ነበሩ ነውን?
3አይደለም፤ እናንተም ንስሓ ካልገባችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ ።
4ወይም በሰሊሆም ግንብ ተደርምሶባቸው የሞቱ ዐሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካሉ ሰዎች ይልቅ ኃጢአተኞች ስለ ነበሩ ነውን?
5አይደለም፤ ሁላችሁም ንስሓ ባትገቡ ትጠፋላችሁ።"
6ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ተናገረ፤ "አንድ ሰው በወይን አትክልት ቦታው የበለስ ዛፍ ተከለ፤ ፍሬዋንም ፈልጎ ወደ በለሲቱ መጣ፤ ነገር ግን ምንም ፍሬ አላገኘባትም።
7እርሱም ለአትክልተኛው እንዲህ አለው፤ "ተመልከት! ሦስት ዓመት ሙሉ ፍሬ ፈልጌ ወደ በለሲቱ መጣሁ፤ ግን ምንም ፍሬ አላገኘሁባትም፡፡ ቊረጣት ስለምን መሬትን ታበላሻለች።"
8አትክልተኛውም መልሰና እንዲህ አለ፣ "ለዚህ ዓመት ተዋት ዙሪያዋን ኮትኩቼ ማዳበሪያ አደርግላትና
9በሚቀጥለው ዓመት ታፈራ ይሆናል፤ ባታፈራ ግን ቊረጣት።"
10ኢየሱስም በሰንበት ቀን በአንዱ ምኲራብ እያስተማረ ነበር።
11ለዐሥራ ስምንት ዓመት ርኩስ መንፈስ ያጐበጣት አንዲት ሴት በዚያ ነበረች፡፡ እርስዋም ከመጒበጧ የተነሣ ቀና ብላ መቆም አትችልም ነበር፡፡
12ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና፣ "ተነሺና ከበሽታሽ ተፈወሺ" አላት።
13በእጁ ዳሰሳት፣ ወዲያውኑም ቀጥ ብላ ቆመች፤ እግዚአብሔርንም
14አመሰገነች፡፡ የምኲራቡ አለቃ ግን በሰንበት በመፈወሷ ተቈጣና ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ "ከሳምንቱ ቀኖች ሥራ የሚሠራባቸው ስድስት ቀኖች አሉ፤ ሄዳችሁ በእነዚያ ቀኖች ተፈወሱ እንጂ በሰንበት ቀን አይሆንም አላቸው።"
15ጌታ እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ "እናንት ግብዞች! በሰንበት ቀን ከእናንተ መካከል በሬውን ወይም አህያውን ከታሰረበት በረት አወጥቶ ውኅ የማያጠጣው ማን ነው?
16ይህች የአብርሃም ዘር የሆነች ለዐሥራ ስምንት ዓመት በሰይጣን ታስራ የኖረች ሴት በሰንበት ቀን ከበሽታዋ መፈታት አይገባትምን?"
17ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች በተናገረ ጊዜ፣ ይቃወሙት የነበሩ ሁሉ አፈሩ፣ ሕዝቡ ግን በተደረገው ድንቅ ነገር ሁሉ ደስ አላቸው።
18ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ "የእግዚአብሔር መንግሥት በምን ትመሰላለች? ከምንስ ጋር አነጸጽራታለሁ?
19አንድ ሰው የሰናፍጭ ዘር በአትክልት ቦታው እንደተከላት ዛፍዋም አድጋ፣ ወፎች በቅርንጫፎችዋ ላይ ጎጆአቸውን ሠርተው ማረፊያ ያደረጉባት ዛፍ ትመሰላለች።"
20እንደ ገናም እንዲህ አለ፤ "የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን ላነጻጽራት እችላለሁ?
21የእግዚአብሔር መንግሥት አንዲት ሴት ሊጡን ሁሉ እስኪያቦካ ድረስ በሶሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውስጥ የሰወረችውን እርሾ ትመስላለች።"
22ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ሳለ በየከተማውና በየገጠሩ እያስተማረ ያልፍ ነበር፡፡
23አንድ ሰው፣ "ጌታ ሆይ፤ የሚድኑት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸውን?" ብሎ ጠየቀው፡፡ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤
24"በጠባብዋ በር ለመግባት ታገሉ፣ ብዙዎች በዚህች በር ሊገቡ ይሞክራሉ ነገር ግን ሊገቡባት አይችሉም።
25የቤቱ ጌታ በሩን ይዘጋል፤ እናንተም በደጅ ቆማችሁ፤ አንኳኩታችሁ፣ 'ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ እንድንገባ ክፈትልን' ትላላችሁ፡፡ እርሱ መልሶ 'ከየት ነው የመጣችሁት? እኔ አላውቃችሁም' ይላችኋል፡፡
26ከዚያም እናንተ፣ 'ጌታ ሆይ፣ ከአንተ ጋር አብረን በልተናል፤ አብረንም ጠጥተናል፤ በአደባባዮቻችንም አስተምረሃል' ትላላችሁ፡፡
27እርሱ ግን እንዲህ ይመልሳል፤ 'ከየት እንደ መጣችሁ አላውቅም ፤ እናንተ ዐመፀኞች ከእኔ ራቁ እላችኋለሁ፡፡'
28በእግዚአብሔር መንግሥት አብርሃምን፤ይስሐቅን፤ ያዕቆብን፤ ነቢያትንም በምታዩበት ጊዜ፤ እናንተ ግን በውጪ ትጣላላችሁ ከዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፡፡
29ብዙ ሰዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ፤ ከሰሜንና ከደቡብ መጥተው በእግዚአብሔር መንግሥት በማዕድ ተቀምጠው ይደሰታሉ፡፡
30ይህንም እወቁ ኋለኞች ፊተኞች፤ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ፡፡"
31ከዚያ በኋላ፣ አንዳንድ ፈሪሳውያን ወደ እርሱ ቀርበው፣ "ሄሮድስ ሊገድልህ ይፈልጋልና ከዚህ ወጥተህ ወደ ሌላ ስፍራ ሂድ" አሉት፡፡
32ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ "ሂዱና ለዚያ ቀበሮ፣ 'ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ፤ በሽታኞችን እፈውሳለሁ፤ በሦስተኛም ቀን ሥራዬን እፈጽማለሁ' ይላል በሉት"
33ይሁን እንጂ ዛሬና ነገ ከዚያም በኋላ ነቢይ ከኢየሩሳሌም በቀር በሌላ ስፍራ መሞት ስለሌበት ወደ ኢየሩሳሌም መንገዴን መቀጠል አለብኝ" አለ።
34አንቺ ኢየሩሳሌም! ኢየሩሳሌም ሆይ! ነቢያትን የምትገድዪ፤ መልእክተኞችሽንም የምትወግሪ ነሽ፡፡ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ ሥር እንደምትሰበስብ እኔም ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ፡፡ እናንተ ግን አልፈለጋችሁም፡፡
35እነሆ፣ ቤታችሁ ባዶ ሆኖ ቀርቶአል፡፡ እላችኋለሁ፣ እናንተ 'በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው' እስከምትሉ ድረስ አታዩኝም፡፡"
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።