1ይህ እየሆነ ሳለ እርስ በርሳቸው እስኪረጋገጡ ድረስ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ሰዎች ተሰብስበው ባሉበት ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ይላቸው ጀመር። "ግብዝነት ከሆነው የፈሪሳውያን እርሾ ተጠንቀቁ።"
2ነገር ግን የሚገለጥ እንጂ ምንም የተሰወረ፣ የሚታወቅ እንጂ ምንም የተደበቀ ነገር የለም፡፡
3በጨለማ የተናገራችሁት ማንኛውም ነገር በብርሃን የሚሰማ፣ በጓዳ በጆሮ የተናገራችሁትም በከፍተኛ መድረኮች ላይ የሚታወጅ ይሆናል፡፡
4ለእናንተ ለወዳጆቼ፣ እንዲህ እላችኋለሁ፤ ሥጋን የሚገድሉትን ከዚያ በኋላ ግን ምንም ማድረግ የማይችሉትን አትፍሩ።
5ማንን መፍራት እንደሚገባችሁ እኔ እነግራችኋለሁ። ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም እሳት የመጣል ሥልጣን ያለውን እርሱን ፍሩት። አዎን፣ እርሱን ፍሩት ብዬ እላችኋለሁ።
6ሁለት ድንቢጦች ዝቅተኛ ዋጋ ባላቸው ሳንቲሞች ይሸጡ የለምን? ሆኖም ከእነርሱ አንዷም እንኳ በእግዚአብሔር ፊት የተዘነጋች አይደለችም።
7ነገር ግን የእናንተ የራሳችሁ ፀጉሮች እንኳ የተቈጠሩ ናቸው። አትፍሩ፣ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ።
8በሰዎች ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል፤
9በሰዎች ፊት የሚክደኝ ግን በእግዚአብሔር መላእክት ፊት የሚካድ ይሆናል ብዬ እነግራችኋለሁ፡፡
10በሰው ልጅ ላይ የተቃውሞ ንግግር የተናገረ ማንኛውም ሰው ይቅርታ ያገኛል፣ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ግን ይቅርታ አያገኝም፡፡
11በምኲራቦች፣ በገዢዎችና በባለ ሥልጣኖች ፊት በሚያቀርቧችሁ ጊዜ ለቀረበባችሁ ክስ እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ወይም ምን ማለት እንዳለባችሁ አትጨነቁ፤
12መንፈስ ቅዱስ በዚያ ወቅት ምን መናገር እንደሚገባችሁ ይነግራችኋልና"
13ከሕዝቡም መካከል አንድ ሰው፣ "መምህር ሆይ፣ ወንድሜ ርስት እንዲያካፍለኝ ንገረው" አለ።
14ኢየሱስም፣ "አንተ ሰው፣ በእናንተ ላይ ዳኛ ወይም አደራዳሪ አድርጎ የሾመኝ ማን ነው?" አለው።
15ለእነርሱም እንዲህ አላቸው፣ "ስግብግብነት ከሞላባቸው ምኞቶች ራሳችሁን ጠብቁ፣ ምክንያቱም የአንድ ሰው ሕይወት በሀብቱ ብዛት ላይ የተመሠረተ አይደለም"
16ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ በማለት ምሳሌ ነገራቸው፤ "የአንድ ሰው ዕርሻ ከፍተኛ ምርት አስገኘለት፤
17እርሱም፣ 'የተመረተውን እህል የማከማችበት የለኝምና ምን ማድረግ ይገባኛል?' ብሎ በልቡ ዐሰበ።
18እንዲህም አለ፤ 'እንግዲያውስ እንደዚህ አደርጋለሁ፣ ጐተራዎቼን አፍርሼ በምትኩ ትልልቅ ጐተራዎችን እሠራለሁ፣ የተመረተውን እህልና ሌሎች ንብረቶቼንም ሁሉ አከማችባቸዋለሁ።
19ነፍሴንም፣ "ነፍሴ ሆይ፣ ለብዙ ዘመን የሚበቃ ብዙ ሀብት ተከማችቶልሻልና አትጨነቂ ብዪ፣ ጠጪ ደስም ይበልሽ እላታለሁ'" አለ።
20እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለው፤ "አንተ ሞኝ ሰው፣ ዛሬ ማታ ከአንተ ልትወሰድ ነፍስህ ትፈለጋለች፣ ያዘጋጀሃቸው ነገሮች ታዲያ ለማን ይሆናሉ?"
21በእግዚአብሔር ፊት ባለ ጠጋ ያልሆነ ለራሱ ግን ሀብትን የሚያከማች ሰው ይህን ይመስላል።
22ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ "ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ምን እንበላለን ብላችሁ ስለ ሕይወታችሁ ወይም ምን እንለብሳለን ብላችሁ ስለ ሰውነታችሁ አትጨነቁ፡፡
23ምክንያቱም ሕይወት ከምግብ ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና፡፡
24የማይዘሩትን ወይም የማያጭዱትን ቁራዎችን ተመልከቱ። መጋዘን ወይም ጐተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ይመግባቸዋል። ከወፎች ይልቅ እናንተ ምን ያህል የላቀ ግምት ያላችሁ ናችሁ?
25ከእናንተስ ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንዲት ቀን መጨመር የሚችል ማን ነው?
26ታዲያ፣ ታናሽ የሆነውን ነገር እንኳ ማድረግ የማትችሉ ከሆነ ስለ ሌላው ጉዳይ ለምን ትጨነቃላችሁ?
27እንዴት እንደሚያድጉ አበቦችን ተመልከቱ፡፡ አይሠሩም ወይም አይፈትሉም። ሆኖም፣ ሰሎሞን እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነዚህ እንደ አንዱ እንዳልለበሰ እኔ እነግራችኋለሁ።
28ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ ቆሻሻ ማከማቻ እንደሚጣለው ሣር በሜዳ ላይ ያለውን እግዚአብሔር እንደዚህ የሚያለብሰው ከሆነ፣ እምነታችሁ ትንሽ የሆነውን እናንተንማ ምን ያህል የበለጠ አያለብሳችሁም?
29የምትበሉትንና የምትጠጡትን በመፈለግ አትጨነቁ።
30በዓለም ውስጥ ባሉት አገሮች የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ እነዚህን ይፈልጋሉና፣ እናንተም እነዚህን እንደምትፈልጉ አባታችሁ ያውቃል።
31ነገር ግን የእርሱን መንግሥት ፈልጉ፣ እነዚህም ነገሮች ይጨመሩላችኋል።
32አንተ ታናሽ መንጋ፣ መንግሥትን ሊሰጥህ አባትህ እጅግ ደስ ይለዋልና አትፍራ።
33ንብረቶቻችሁን ሽጡና ለድኾች ስጡ። በማያረጅ ከረጢት ሌቦች ሊቀርቡትና ብል ሊያጠፋው የማይቻለውን የማያልቀውን ሀብት በሰማይ አከማቹ።
34ንብረታችሁ ባለበት ልባችሁም በዚያ ይሆናልና።
35የሥራ ልብሳችሁን በአጭር ታጥቃችሁ በተጠንቀቅ ቁሙ፣ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤
36በሚመጣበትና በሩን በሚያንኳኳበት ጊዜ ፈጥነው በሩን እንደሚከፍቱለት ጌታቸው ከሠርግ ሲመለስ እንደሚጠባበቁ ሰዎች ሁኑ።
37በሚመጣበት ጊዜ ነቅተው ሲጠብቁ ጌታቸው የሚያገኛቸው እነዚያ አገልጋዮች የተመሰገኑ ናቸው። በእርግጥ እላችኋለሁ፣ እርሱም የሥራ ልብሱን ለብሶ ምግብ ለመመገብ እንዲቀመጡ ያደርጋቸውና ወደ እነርሱ መጥቶ ያገለግላቸዋል።
38ከሌሊቱ በስድስት ሰዓት ወይም በዘጠኝ ሰዓትም እንኳ ቢሆን ሲመጣ ተዘጋጅተው የሚያገኛቸው እነዚያ አገልጋዮች የተመሰገኑ ናቸው።
39በተጨማሪ ይህን እወቁ፤ የአንድ ቤት ጌታ ሌባ የሚመጣበትን ሰዓት የሚያውቅ ቢሆን ኖሮ የቤቱ በር እንዲሰበር ባልፈቀደም ነበር፡፡
40እናንተም እንደዚሁ ዝግጁ ሁኑ፣ ምክንያቱም የሰው ልጅ የሚመጣበትን ሰዓት አታውቁም።"
41ጴጥሮስ፣ "ጌታ ሆይ፣ ይህንን ምሳሌ የተናገርኸው ለእኛ ብቻ ነው ወይስ ለሌሎችም ሰዎች ሁሉ ነው?" አለ።
42ጌታም እንዲህ አለ፣ "ታዲያ ለሌሎቹ አገልጋዮቹ የተመደበላቸውን ምግብ በትክክለኛው ጊዜ ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው የሾመው ታማኝና ብልህ አስተዳዳሪ ማን ነው?
43ጌታው በሚመጣበት ጊዜ ይህን ሲያደርግ የሚያገኘው ያ አገልጋይ የተመሰገነ ነው"
44እውነት እላችኋለሁ፣ ባለው ንብረት ሁሉ ላይ ይሾመዋል።
45ያ አገልጋይ ግን በልቡ፣ 'የጌታዬ የመመለሻ ወቅት ይዘገያል' ቢልና ወንድና ሴት አገልጋዮችን መደብደብ፣ መብላትና መጠጣት እንዲሁም መስከር ቢጀምር፣
46የዚያ አገልጋይ ጌታ ባልጠበቀው ቀንና ባላወቀው ሰዓት ይመጣል፣ ይቆራርጠዋል፣ ካልታመኑት ጋርም ይደባልቀዋል።
47የጌታውን ፈቃድ ያወቀውና እንደ ፈቃዱ ሆኖ ለመገኘት ያልተዘጋጀውና ፈቃዱን ያልፈጸመው ያ አገልጋይ ከፍተኛ ቅጣት ይቀጣል።
48ነገር ግን ያላወቀና ቅጣት የሚያስከትልበትን ተግባር የፈጸመ ጥቂት ይቀጣል። ብዙ ከተሰጠው ከማንኛውም ሰው ብዙ ይጠበቅበታል፣ ከፍ ያለ አደራ ከተሰጠውም፣ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል።
49የመጣሁት በምድር ላይ እሳት ለመለኰስ ነው፣ ሆኖም አሁኑኑ ተቀጣጥሎ ባገኘው ደስ ባለኝ ነበር።
50ነገር ግን የምጠመቀው ጥምቀት አለኝ፣ ያንንም ጥምቀት እስከምፈጽመው ምን ያህል በጭንቀት እጠባበቀዋለሁ!
51በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት እንደ መጣሁ ታስባላችሁን? እንደዚያ አታስቡ፣ እነግራችኋለሁ፣ የመጣሁት ይልቁኑ መለያየትን ላመጣ ነው፡፡
52ከእንግዲህ ወዲህ በአንድ ቤት ውስጥ አምስት ሰዎች ቢኖሩ ሦስቱ በሁለቱ ላይ፣ ሁለቱም በሦስቱ ላይ የሚነሡና የሚለያዩ ይሆናሉ፡፡
53አባት በልጅ ላይ ልጅም በአባት ላይ፤ አማት በምራት ላይ፣ ምራትም በአማት ላይ ይነሡና ይለያያሉ፡፡
54ደግሞም ኢየሱስ ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው፤ "በምዕራብ በኩል ደመና ሲያንጃብብ በምትመለከቱበት ጊዜ ወዲያውኑ፣ 'ሊያካፋ ነው' ትላላችሁ፣ እንዳላችሁትም ይሆናል።
55የደቡብ ነፋስም ሲነፍስ፣ 'የሚያቃጥል ሙቀት ሊመጣ ነው' ትላላችሁ፣ እንዳላችሁትም ይሆናል።
56እናንተ ግብዞች፣ የምድርንና የሰማይን መልክ እንዴት እንደምትተረጒሙ ታውቃላችሁ፣ ታዲያ የአሁኑን ወቅት እንዴት እንደምትተረጒሙ እንዴት አታውቁም?
57እናንተ ራሳችሁ ትክክል የሆነውን ለምን አትፈርዱም?
58ከባላጋራህ ጋር ወደ ከተማው አስተዳዳሪ በምትሄድበት ጊዜ፣ በመንገድ ላይ ቅራኔህን ለመፍታት ጥረት ማድረግ አለብህና፣ ይህን ባታደርግ ዳኛው ለዕለቱ ተረኛ መኰንን አሳልፎ ይሰጥሃል፣ ተረኛው መኰንንም ወደ ወንጀለኛ ማረፊያ ክፍል ያስገባሃል።
59ዕዳህን ሙሉ በሙሉ እስካልከፈልህ ድረስ ከዚያ በፍጹም እንደማትወጣ እኔ እነግርሃለሁ።"