1ኢየሱስ በአንድ ስፍራ መጸለዩን በፈጸመ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ እንዲህ አለው፣ “ጌታ ሆይ፣ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እኛን መጸለይ አስተምረን” አለ።
2ኢየሱስም፣ “በምትጸልዩበት ጊዜ፣ 'በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ መንግሥትህ ትምጣ
3የዕለት እንጀራችን በየዕለቱ ስጠን።
4እኛን የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን። ወደ ፈተናም አታግባን በሉ'" አላቸው።
5ኢየሱስም፣ “ከእናንተ ወዳጅ ያለው በእኩለ ሌሊት ውድ ወዳጁ ዘንድ በመሄድ
6‘አንድ ወዳጄ ከሌላ ስፍራ ወደ እኔ መጥቶ የማስተናግድበት ምንም ስለሌለኝ፣ ሦስት እንጀራ አበድረኝ የማይለው ማነው’?
7በቤት ውስጥ ያለው ወዳጁ ‘አታስቸግረኝ፤ በሩ ተዘግቶአል ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ ተኝተዋል። ለመነሣትና ለአንተ እንጀራ ለመስጠት አልችልም’ ይለዋልን?
8ምንም እንኳን ወዳጁ ስለሆናችሁ ተነሥቶ እንጀራ ባይሰጣችሁም ያለ ዕረፍት ስለነዘነዛችሁት ብቻ ተነስቶ የምትፈልጉትን ያህል እንጀራ ይሰጣችኋል፤
9ለምኑ ይሰጣችኋል፣ ፈልጉ ታገኛላችሁ፣ አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤
10የሚለምን ሰው ሁሉ ይቀበላልና የሚፈልግም ሰው ያገኛል፣ ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል።
11አባት ከሆናችሁት ከእናንተ ዓሣ ሲለምነው በዓሣ ፈንታ እባብ ወይም
12ዕንቁላል ሲለምነው በዕንቁላሉ ፈንታ ጊንጥ የሚሰጠው ማን ነው?
13ስለዚህ፣ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን የምታውቁ ከሆነ፣ በሰማይ የሚኖረው አባታችሁማ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም?”
14በኋላ ኢየሱስ ጋኔን እያወጣ ነበር፤ እርሱም ድዳ ነበር። ጋኔኑም በወጣ ጊዜ ድዳው ሰውዬ ተናገረ፤ ሕዝቡም ተደነቁ።
15ነገር ግን ከሕዝቡ አንዳንዶቹ፣ “አጋንንትን የሚያወጣው የአጋንንት አለቃ በሆነው በብዔል ዜቡል ነው” አሉ።
16ሌሎች ሊፈትኑት ፈልገው ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት።
17ኢየሱስ ግን ዐሳባቸውን አውቆ፣ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ይፈርሳል፤ እርስ በርሱ የሚለያይ ቤተ ሰብም ይወድቃል።
18ሰይጣን ራሱን በራሱ የሚቃረን ከሆነ መንግሥቱ እንዴት ይጸናል? እናንተ ግን እኔን አጋንንትን የሚያወጣው በብዔል ዜቡል ነው ትሉኛላችሁ።
19እኔ በቡዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ የእናንተ ተከታዮች የሚያወጧቸው በማን ነው? ከዚህም የተነሣ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል።
20እኔ ግን በእግዚአብሔር ኃይል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፣ እንግዲያውስ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ መጥቷል።
2121 በሚገባ የታጠቀ ብርቱ ሰው ቤቱን በሚጠብቅበት ጊዜ የቤቱ ንብረት ያለ ስጋት ይሆናል፤
22ከእርሱ የበረታ ሰው ሲያሸንፈው ግን ያ ከእርሱ የበረታው ሰው መሣሪያውን ይቀማዋል፣ የቤቱንም ሀብት ይበዘብዛል።
23ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፣ ከእኔ ጋርም የማይሰበስብ ይበትናል።
24ርኩስ መንፈስ ከሰው በሚወጣበት ጊዜ ውሃ በሌለባቸው ስፍራዎች እየተዘዋወረ ማረፊያ ይፈልጋል። ምንም ማረፊያ ሲያጣ ‘ወደ ወጣሁበት ቤት እመለሳለሁ’ ይላል።
25በሚመለስበት ጊዜ ያንን ቤት ተጠርጎና ጸድቶ ያገኘዋል።
26ከዚያም ከእርሱ ይልቅ የከፉ ሰባት ሌሎችን ከእርሱ ጋር ይዞ ይሄድና ሁሉም በዚያ ሰው ውስጥ ገብተው ይኖራሉ። ከዚያም ያ ሰው በመጨረሻ የሚገጥመው ሁኔታ ከመጀመሪያው ይልቅ የከፋ ይሆናል።
27ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች በሚናገርበት ጊዜ፣ ከሕዝቡ መካከል አንዲት ሴት ድምጿን ከፍ አድርጋ፣ “አንተን የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች የተባረኩ ናቸው” አለችው።
28እርሱ ግን፣ “የተባረኩትስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው” አለ።
29የሕዝቡም ቊጥር እየጨመረ ሲሄድ፣ እንዲህ ማለት ጀመረ፣ “ይህ ትውልድ ክፉ ትውልድ ነው። ምልክት ይፈልጋል፤ ሆኖም ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም።
30ልክ ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደ ሆነላቸው፣ የሰው ልጅም ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናልና።
31የደቡብ ንግሥት በፍርድ ወቅት ከዚህ ትውልድ ጋር ትነሣና ትፈርድበታለች፣ ምክንያቱም የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና፤ እነሆም ከሰሎሞን የሚበልጥ በዚህ አለ።
3232 የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ይነሡና ይፈርዱበታል፣ ምክንያቱም በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋል፤ እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።
33አንድ ሰው መብራት ካበራ በኋላ ብርሃኑ በማይታይበት ሰዋራ ስፍራ አያስቀምጠውም ወይም እንቅብ በላዩ ላይ አይደፋበትም። ነገር ግን ወደዚያ ቤት የሚገቡ እንዲታያቸው ከፍ ባለ ስፍራ ላይ ያስቀምጠዋል።
34ዓይን የሰውነት መብራት ነው። ዓይንህ ጤናማ ከሆነ፣ መላ ሰውነትህ በብርሃን የተሞላ ይሆናል። ዓይንህ ሕመምተኛ ከሆነ ግን መላ ሰውነትህ ጨለማ ይሆናል።
35ስለዚህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን ጨለማ እንዳይሆን ተጠንቀቅ።
36እንግዲህ መላ ሰውነትህ ምንም ጨለማ የሌለበትና በብርሃን የተሞላ ከሆነ፣ በዚያን ጊዜ በሙሉ ብርሃኑ መብራት በአንተ ላይ እንደሚያበራ ያህል ይሆናል።
37ንግግሩንም ሲያበቃ አንድ ፈሪሳዊ በቤቱ ምግብ ይመገብ ዘንድ ጋበዘው፤ ኢየሱስም ከፈሪሳዊው ቤት ሄዶ ለማዕድ ቀረበ።
38ኢየሱስ ወደ ማዕድ ከመቅረቡ በፊት እጁን ባለመታጠቡ ፈሪሳዊው ተደነቀ።
39ጌታ ግን እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ፣ እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጸዳላችሁ፣ ውስጣችሁ ግን በስስትና በክፋት የተሞላ ነው።
40እናንተ ማስተዋል የሌላችሁ ሰዎች፣ ውጪውን የፈጠረ የውስጡንስ አልፈጠረምን?
41በውስጥ ያለውን ለድኾች ስጡ፣ ከዚያም ሁሉም ነገር ንጹሕ ይሆንላችኋል።
42ነገር ግን እናንተ ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ካመረታችሁት አዝሙድና ጤና አዳም ዐሥራት እያወጣችሁ ፍትሕንና የእግዚአብሔርን ፍቅር ንቃችሁ ትተዋላችሁ። ሌላውን ነገር ማድረግ ሳትተዉ ፍትሕ ማድረግንና የእግዚአብሔርን ፍቅር መጠበቅ ያስፈልጋችኋል።
43እናንተ ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! በምኲራቦች የክብር መቀመጫዎችንና በገበያ ስፍራም የከበሬታ ሰላምታን ትወዳላችሁና።
44ሰዎች የማን እንደሆኑ ሳያውቁ የሚረማመዱባቸው መቃብሮችን ትመስላላችሁና ወዮላችሁ!"
45የአይሁድ የሕግ መምህር የነበረ አንድ ሰው፣ “መምህር ሆይ፣ በምትናገረው ነገር እኛንም እየሰደብኸን ነው” ብሎ መለሰለት።
46ኢየሱስም እንዲህ አለ፣ “እናንተም የሕግ መምህራን፣ ለመሸከም የሚከብድ ሸክም በሰዎች ላይ ትጭናላችሁና፣ እናንተ ግን እነዚያን ሸክሞች በአንድ ጣታችሁ እንኳ አትነኳቸውምና ወዮላችሁ!
47የገደሏቸው የእናንተ አባቶች ሆነው ሳለ እናንተ ግን የቀደሙ ነቢያትን መቃብር የምታንጹ ናችሁና ወዮላችሁ!።
48ከዚህም የተነሣ አባቶቻችሁ በሠሩት ሥራ ምስክሮችና ከእነርሱም ጋር የምትስማሙ ናችሁና፣ ምክንያቱም እናንተ የመታሰቢያ መቃብራቸውን የምታንጹላቸው ነቢያት በእርግጥም በአባቶቻችሁ የተገደሉ ነበር።
49በዚህ ምክንያት በእግዚአብሔር ጥበብ እንዲህ ተብሏል፣ ‘ነቢያትንና ሐዋርያትን ወደ እነርሱ እልካለሁ፣ እነርሱም አንዳንዶችን ያሳድዳሉ ይገድሉማል።
50ስለሆነም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ለፈሰሰው የነቢያት ሁሉ ደም ይህ ትውልድ ተጠያቂ ነው’።
51ተጠያቂ የሚሆነውም ከአቤል ጀምሮ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ መካከል እስከ ተገደለው እስከ ዘካርያስ ድረስ ለፈሰሰው የነቢያት ደም ነው። አዎን፣ ይህ ትውልድ ተጠያቂ ነው እላችኋለሁ።
5252 እናንተ የአይሁድ የሕግ መምህራንም የዕውቀትን ቊልፍ ጨብጣችሁ ሳላችሁ እናንተ ራሳችሁ የማትገቡ፣ ሊገቡ ያሉትን እንዳይገቡ የምትከለክሉ ናችሁና ወዮላችሁ!
53ኢየሱስ ከዚያ ለመሄድ እንደተነሣ፣ የአይሁድ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ተቃወሙት፣ ብዙ ጉዳዮችን አስመልክተው ከእርሱ ጋር ተከራረኩ።
54ይህንም ያደረጉት ራሱ በተናገረው ቃል ሊያጠምዱት ፈልገው ስለነበረ ነው።