1ያህዌ ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፣
2“ለአሮንና ለልጆቹ እንዲህ በላቸው፣ የእስራኤል ሕዝብ ለእኔ ከለይዋቸው የተቀደሱ ነገሮች እንዲጠበቁ ንገራቸው፡፡ የተቀደሰው ስሜን አያርክሱ፡፡ እኔ ያህዌ ነኝ፡፡
3እንዲህ በላቸው፣ በዘመን ሁሉ ከትውልዳችሁ መሀል ማንም ንጹህ ያልሆነ ሰው የእስራኤል ህዝብ ለያህዌ ወደ ለየው ቅዱስ ነገሮች ቢቀርብ፣ ያ ሰው እኔ ፊት ከመቅረብ የተከለከለ ነወ፡፡ እኔ ያህዌ ነኝ፡፡
4ከአሮን ትውልድ ውስጥ ተላላፊ የቆዳ በሽታ ያለበት፣ ወይም ከሰውቱ ፈሳሽ የሚወጣ ንጹኅ እስኪሆን ድረስ ለያህዌ ከሚቀርብ መስዋዕት አይብላ፡፡ማንም ከሞተ ጋር በመነካካት ንጹህ ያልሆነውን ማንኛውንም ነገር የነካ፣ ወይም የዘር ፈሳሽ ካለበት ሰው ጋር በመነካካት፣
5ወይም የሚያረክሰውን ማናቸውንም በሆዱ የሚሳብ እንስሳ የነካ፣ ወይም ማናቸውንም የሚያረክሰውን ሰው የነካ፣ ማንኛውም አይነት እርኩሰት የሚያስከትል ነገር የነካ
6ማናቸውንም እርኩስ ነገር የነካ ካህን እስከ ምሽት ንጹህ አይደለም፡፡ ሰውነቱን በውሃ ካልታጠበ በቀር ከተቀደሱት ነገሮች አንዳች አይብላ፡፡
7ፀሐይ ስትጠልቅ፣ በዚያን ሰዓት ንጹህ ይሆናል፡፡ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ከተቀደሱት ነገሮች መብላት ይችላል፣ ምክንያቱም ለእርሱ የተፈቀዱ ምግብ ናቸው፡፡
8ሞቶ የተገኘን ማናቸውም ነገር አይብላ ወይም እርሱን የሚያረክሰውን በዱር እንስሳ የተገደለውን አይብላ፡፡
9ካህናት ትእዛዛቴን ይጠብቁ፣ ይህን ካላደረጉ በኃጢአት በደለኛ ይሆናሉ ደግም ስሜን በማቃለል ይሞታሉ፡፡ ለራሴ የለየኋቸው እኔ ያህዌ ነኝ፣
10ማንም የካህኑ ቤተሰብ ያልሆነ ሰው፣ የካህኑን እንግዶች ጨምሮ፣ ወይም ቅጥር አገልጋዮቹ ጭምር ቅዱስ ከሆነው አንዳች አይብሉ፡፡
11ነገር ግን ካህኑ በገንዘቡ ባሪያ ቢገዛ ያ ባሪያ ለያህዌ ከተለዩ ነገሮች መብላት ይችላል፡፡ የካህኑ ቤተሰብ አባላት እና በቤቱ የተወለዱ ባሪያዎች ከእርሱ ጋር ከእነዚህ የተቀደሱ ነገሮች መብላት ይችላሉ፡፡
12የካህኑ ሴት ልጅ ካህን ያልሆነ ሰው ብታገባ ለመስዋዕት ከመጣው ውስጥ አንዳች አትበላም፡፡
13ነገር ግን የካህኑ ሴት ልጅ ባሏ የሞተባት ከሆነች፣ ወይም ከባሏ ከተፋታች፣ እና ልጅ ያልወለደች ከሆነች እንደ ልጅነቷ ዘመን ለመኖር ወደ አባቷ ቤት ብትመለስ ከአባቷ ምግብ መብላት ትችላለች፡፡ ነገር ግን ማንም የካህን ቤተሰብ ያልሆነ ከካህናት ምግብ መብላት አይችልም፡፡
14አንድ ሰው ሳያውቅ ቅዱሱን ምግብ ቢበላ፣ ከወሰደው አንድ አምስተኛ ጨምሮ ለካህኑ ይመልስ፡፡
15የእስራኤል ህዝብ ለያህዌ የወዘወዙትንና ያቀረቡትን ቅዱስ ነገሮች ማቃለል የለባቸውም፣
16ያልተፈቀደላቸውን ቅዱሱን ምግብ በመብላት ራሳቸውን በደለኛ የሚያደርጋቸውን ኃጢአት እንዲሸከሙ ማድረግ የለባቸውም እነርሱን ለራሴ የለየሁት እኔ ያህዌ ነኝ”
17ያህዌ እንዲህ አለው፣
18“ለአሮንና ልጆቹ እንዲሁም ለእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንዲህ በላቸው፣ ‹ማንኛውም እስራኤላዊ፣ ወይም በእስራኤል የሚኖር ባይተዋር፣ ለስዕለትም ይሁን፣ ወይም ለበጎ ፈቃድ መስዋዕት ሲያቀርቡ፣ ወይም ለያህዌ የሚቃጠል መስዋዕት ሲያቀርቡ፣
19ተቀባይነትን እንዲያገኝ ከቀንድ ከብታቸው፣ ከበግ ወይም ፍየሎች ውስጥ ነውር የሌለበትን ተባዕት እንስሳ ያቅርቡ፡፡
20ነውር ያለበትን ግን አታቅርቡ፡፡ ይህን እኔ አልቀበልም፡፡
21ከከብቱ ወይም ከመንጋው ለስዕለት የህብረት መስዋዕት ለያህዌ የሚሰዋ ሁሉ፣ ወይም የበጎ ፍቃድ መስዋዕት የሚያቀርብ ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ ነውር የሌለበትን መስዋዕት ያቅርብ፡፡ በእንስሳው ላይ እንከን አይኑርበት፡፡
22ዕውር፣ አንካሳ ወይም ሰንካላ፣ ወይም ኪንታሮት፣ ህመም፣ ወይም ቁስል ያለበትን እንስሳ አትሰዉ፡፡ እዚህን በእሳት መስዋዕት አድርጋችሁ በመሰዊያ ላይ ለያህዌ አታቅርቡ፡፡
23የበጎ ፈቃድ መስዋዕት አድርጋችሁ ጎደሎ ወይም ትንሽ በሬ ወይም በግ ማቅረብ ትችላላችሁ፣ እንዲህ ያለው መስዋዕት ግን ለስዕለት ተቀባይነት የለውም፣
24ለያህዌ ሰንበር ያለበት፣ የተሰበረ፣ የተዘነጠለ፣ ወይም የዘር ፍሬው የተቀጠቀጠ እንስሳ አታቅርቡ፡፡ እነዚህን በምድራችሁ አታቅርቡ፣
25ለእግዚአብሔር ለምግብ የሚቀርብ አድርጋችሁ ከመጻተኛው እጅ አትቀበሉ፣ ምክንያቱም በእነዚህ ላይ ጉድለቶች ወይም ነውሮች አሉባቸው እነዚህን ከእናንተ አልቀበለም፡፡›”
26ያህዌ ሙሴን እንዲህ አለው፣
27“አንድ ጥጃ ወይም አንድ የበግ ወይም የፍየል ግልገል ሲወለድ፣ ከእናቱ ጋር ሰባት ቀናት ይቆይ፡፡ ከዚያም ከስምንተኛው ቀን አንስቶ፣ ለያህዌ በእሳት መስዋዕት ሆኖ መቅረብ ይችላል፡፡
28አንዲትን ላም ወይም ሴት በግ ከጥጃዋ ወይም ከግልገሏ ጋር በአንድ ቀን አትረዱ፡፡
29ለያህዌ የምስጋና መስዋዕት ስታቀርቡ፣ ተቀባይነት ባለው መንገድ አቅርቡ፡፡
30መስዋዕቱ በቀረበበት ቀን ይበላ፡፡ እስከ ማለዳው አንዳች አታስቀሩ፡፡ እኔ ያህዌ ነኝ፡፡
31ትዕዛዛቴን ጠብቁ አድርጓቸውም፡፡ እኔ ያህዌ ነኝ፡፡
32ቅዱስ ስሜን አታቃሉ፡፡ በቅድስናዬ በእስራኤል ህዝብ መታወቅ አለብኝ፡፡ እናንተን ለራሴ የለየሁት እኔ ያህዌ ነኝ፣
33አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ያህዌ ነኝ፡፡”