1የአሮን ልጆች ናዳብና አብዩድ እያንዳንዳቸው ጥናዎቻቸውን ወስደው እሳት አደረጉበት ከዚያም ዕጣን ጨመሩበት፡፡ ከዚያ በያህዌ ፊት እርሱ እንዲያቀርቡ ያላዘዛቸውን ያልተፈቀደ ዕሳት አቀረቡ፡፡
2ስለዚህም ከያህዌ ዘንድ እሳት ወጥታ በላቻቸው፣ እነርሱም በያህዌ ፊት ሞቱ፡፡
3ከዚያም ሙሴ አሮንን፣ “ያህዌ ‘ወደ እኔ በሚቀርቡ ላይ ቅድስናዬን እገልጻለሁ፡፡ በሰዎች ሁሉ ፊት እከብራለሁ’ ሲል ይህን ማለቱ ነው” አለው፡፡ አሮንም ምንም አልመለሰም፡፡
4ሙሴ የአሮን አጎት የሆነውን የዑዝኤልን ልጆች ሚሳኤልንና ኤልጻፋንን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፣ “ወደዚህ ኑና ከመቅደሱ ደጃፍ ወንድሞቻችሁን ተሸክማችሁ ከሰፈር አውጣቸው፡፡”
5ስለዚህም ሙሴ እንዳዘዘው ቀርበው የክህነት ቀሚሳቸውን እንደለበሱ ተሸክመው ከሰፈር አወጧቸው፡፡
6ከዚያም ሙሴ ለአሮንና ለልጆቹ ለአልአዛርና ለኢታምር እንዲህ አላቸው፣ “እንዳትቀሰፉ ፀጉራችሁን አትንጩ፣ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፣ ያህዌ በህዝቡ ላይ ሁሉ እንዳይቆጣ ተጠንቀቁ፡፡ ነገር ግን ቤተዘመዶቻችሁና መላው የእስራኤል ቤት የያህዌ እሳት ለበላቻቸው ያልቅሱ፡፡
7እናንተ ግን ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትለፉ፣ የያህዌ የቅባት ዘይት በእናንተ ላይ ነውና ትሞታላችሁ፡፡ ስለዚህም ሙሴ እንዳዘዘው አደረጉ፡፡
8ያህዌ አሮንን እንዲህ አለው፣
9“አንተ፣ ወይም ከአንተ ጋር የሚሆኑ ልጆችህ ወደ መገናኛው ድንኳን ስትገቡ እንዳትሞቱ ወይን ጠጅ ወይም የሚያሰክር መጠጥ አትጠጡ፡፡ ይህ በትውልዳችሁ ሁሉ ቋሚ ስርዓት ይሆናል፣
10ቅዱስ በሆነውና ተራ በሆነው መሃል ለመለየት፣ ንጹህ በሆነውና ንጹህ ባልሆነው መሃል ለመለየት፣
11ለእስራኤል ህዝብ ሁሉ በሙሴ በኩል ያህዌ ያዘዘውን ስርዓት ሁሉ አስተምሩ፡፡”
12ሙሴ ለአሮንና ለተረፉት ልጆቹ ለአልአዛርና ለኢታምርን እንዲህ አላቸው፣ “በእሳት ለያህዌ ከቀረበው የእህል ቁርባን የተረፈውን መስዋዕት ውሰድ፣ እጅግ ቅዱስ ነውና እርሾ ሳይገባበት ከመሰዊያው አጠገብ ብሉት፡፡
13በተቀደሰው ስፍራ ብሉት፣ ምክንያቱም በእሳት ለያህዌ ከቀረበው መስዋዕት ይህ የአንተና የልጆችህ ድርሻ ነው፣ እንድነግርህ የታዘዝኩት ይህንን ነው፡፡
14ለመስዋዕት የተወዘወዘውን ፍርምባና ለያህዌ የቀረበውን ወርች እግዚአብሔር ደስ በሚሰኝበት በተቀደሰው ስፍራ ብሉት፡፡ እነዚህን ድርዎቻችሁን አንተ፣ እንዲሁም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ብሉት፣ እነዚህ የእስራኤል ህዝብ ከሚያቀርበው የህብረት መስዋዕት የአንተና የልጆችህ ድርሻ ሆነው ተሰጥተዋል፡፡
15ለያህዌ መስዋዕት ሆኖ የቀረበውን ወርች እና መስዋዕት ሆኖ የተወዘወዘውን ፍርምባ በእሳት ከተዘጋጀው የስብ መስዋዕቶች ጋር ከፍ አድርገው ለመወዘወዝና ለያህዌ መስዋዕት ለማድረግ በአንድነት ያቅርቧቸው፡፡ ይህም ያህዌ እንዳዘዘው ለዘለዓለም የአንተና የልጆችህ ድርሻ ይሆናል፡፡”
16ከዚያ ሙሴ ለኃጢአት መስዋዕት ስለሚሆነው ፍየል ጠየቀ፣እናም በእሳት እንደተቃጠለ አወቀ፡፡ ስለዚህም በአልአዛርና በኢታምር በተቀሩትም የአሮን ልጆች ላይ ተቆጣ፤ እንዲህም አላቸው፣
17“ይህ የኃጢአት መስዋዕት እጅግ የተቀደሰ ሆኖ ሳለና የጉባኤውን በደል በእረሱ ፊት እንድታስወግዱበትና ኃጢአታቸውንም እንድታስተረዩላቸው ሰጥቷችሁ ሳለ ስለምን በቤተ አምልኮው ስፍራ አልበላችሁትም?
18ተመልከቱ፣ ደሙ ወደ ቤተመቅደስ ውስጥ አልመጣም፤ እንዳዘዝኳችሁ በቤተ መቅደሱ አካባቢ ለትበሉት ይገባ ነበር፡፡”
19ከዚያም አሮን ለሙሴ እንደህ ሲል መለሰለት፣ “እነሆ፣ ዛሬ የኃጢአት መስዋዕታቸውን እና የሚቃጠል መስዋዕታቸውን በያህዌ ፊት አቀርቡ፣ እናም ይህ ነገር በእኔ ላይ ደርሷል፡፡ ዛሬ እኔ የኃጢአት መስዋዕቱን ብበላ ኖሮ ይህ በያህዌ ፊት ደስ ያሰኝ ነበርን?”
20ሙሴ ያንን ሲሰማ መልሱ አረካው፡፡