መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሰቆቃው ኤርሚያስ 4

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ወርቁ ፈጽሞ ደበዘዘ፤ ንጹሁ ወርቅ ተለወጠ! የተቀደሱት ድንጋዮች በየመንገዱ ዳር ተበተኑ።
2የጽዮን ልጆች የከበሩ፥ከንጹህ ወርቅ በላይ የሚቆጠሩ ነበሩ። አሁን ግን በሸክላ ሠሪ እጅ እንደተሠሩ የሸክላ ዕቃዎች እንጂ ከምንም አልተቆጠሩም።
3ቀበሮዎች እንኳን ግልገሎቻቸውን ለማጥባት ጡቶቻቸውን ይገልጣሉ፥የሕዝቤ ሴት ልጅ ግን እንደ ምድረ በዳ ሰጎን ጨካኝ ሆነች።
4ከጥም የተነሳ የሚጠባው ሕጻን ምላስ ከላንቃው ጋር ተጣበቀ፤ሕጻናት እንጀራ ለመኑ፥ ነገር ግን የሚሰጣችው የለም።
5በውድ ዋጋ የሚገዛ ምግብ ይመገቡ የነበሩ ተጥለዋል፥ በየመንገዱ ተርበዋል፤ቀይ ግምጃ ይለብሱ የነበሩ አሁን በቆሻሻ ክምር መካከል ናቸው።
6ምንም እጅ ሳይወድቅባት በድንገት ከተገለበጠች ከሰዶም ኃጢአት ይልቅ የሕዝቤ ሴት ልጅ ኃጢአት ታላቅ ነው።
7መሪዎቿ እንደ በረዶ የሚያንጸባርቁ ነበሩ፥እንደ ወተትም ነጭ ነበሩ። ሰውነታቸው ከቀይ ዕንቁ ይልቅ ቀይ ነበረ፥ መልካቸውም እንደ ሰንፔር ነበረ።
8አሁን ጨለማው ገጽታቸውን አጥቁሮታል፥ ቆዳቸው ከመነመኑ አጥንቶቻቸው ጋር ስለተጣበቀም በመንገዶች ላይ ማንነታቸው አልታወቀም።
9በሰይፍ የተገደሉት በረሃብ ከሞቱት ይሻላሉ፥አንዳችም ሰብል ከእርሻ በመጥፋቱ በረሃብ ተወግተው ከተወገዱት ይሻላሉ።
10የርኁሩኆቹ ሴቶች እጆች የገዛ ልጆቻቸውን ቀቀሉ፤ በሕዝቤ ሴት ልጅ የጥፋት ቀን እነዚህ ልጆች መብል ሆኑአቸው።
11እግዚአብሔር ቁጣውን አረካ። ጽኑ ቁጣውን አፈሰሰ፤ በጽዮን እሳትን አያያዘ፥ መሠረትዋንም በላ።
12የምድር ነገሥታት ወይም በዓለም ከሚኖሩ ማናቸውም፥ ባላጋራ ወይም ጠላት በኢየሩሳሌም በሮች ይገባል ብለው አላመኑም።
13ነገር ግን የጻድቅን ደም በመካከልዋ ካፈሰሱ ከነቢያቶቿ ኃጢአትና ከካህናቷ በደል የተነሳ ይህን አደረጉ።
14አሁን እነዚያ ነቢያትና ካህናት እንደ ዓይነ ስውራን ሰዎች በየጎዳናዎቹ ይቅበዘበዛሉ። ማንም ልብሶቻቸውን መንካት እስከማይችል ድረስ በደም ረክሰዋል።
15«እናንተ ርኩሳን ለቃችሁ ሂዱ!» እያሉ በነቢያቱና ካህናቱ ላይ ይጮሁባቸዋል።«ለቃችሁ ሂዱ፥ለቃችሁ ሂዱ! አትንኩን!» ይሏቸዋል። ስለዚህ ወደ ሌላ ምድር ይቅበዘበዛሉ፥ ነገር ግን አሕዛብ እንኳን፥«ከእንግዲህ ወድያ በዚህ እንደ እንግዳ መኖር አይችሉም» ይላሉ።
16እግዚአብሔር ከማደሪያው በትኖአቸዋል፥ ከእንግዲህ ወድያ ወደ እነርሱ በርኅራኄ አይመለከትም። ማንም ከእንግዲህ ወድያ ካህናቱን በምንም መልኩ አክብሮ አይቀበላቸውም፥ ለሽማግሌዎቹም ግድ አልተሰኙም።
17የማይጠቅሙ ረዳቶችን እንኳ ለማግኘት ዓይኖቻችን ድከሙ፤ሊያድነን ወደማይችል ሕዝብ በጉጉት ተመለከቱ።
18በመንገዶቻችን ሁሉ እርምጃዎቻችንን ተከታተሉ። ፍፃሜያችን መጥቶአልና መጨረሻችን ቀርቦአል፥ ቀኖቻችንም አልቀዋል።
19አሳዳጆቻችን ከሰማይ ንስሮች ይልቅ ፈጣኖች ናቸው። በተራሮች ላይ አሳደዱን በምድረ በዳም ሸመቁብን።
20በእግዚአብሔር የተቀባው ንጉሣችን፥ የአፍንጫችን እስትንፋስ፥ በጉድጓቸው ተያዘ፤«በአሕዛብ መካከል በጥበቃው ሥር እንኖራልን» ብለን የተናገርንለት ንጉሣችን ነበር።
21በዖፅ ምድር የምትኖሪ የኤዶም ሴት ልጅ ሆይ፥ጽዋው ወደ አንቺም ያልፋልና ደስ ይበልሽ ሐሴትም አድርጊ። ትሰክሪያልሽ፥ እርቃንሽንም ትቀሪያልሽ።
22የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ በደልሽ ተፈጸመ። ከእንግዲህ ወዲያ በምርኮ አያኖርሽም። ነገር ግን የኤዶም ሴትልጅ ሆይ በደልሽን ይቀጣል። ኃጢአትሽንም ይገልጣል።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።