መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሰቆቃው ኤርሚያስ 2

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ጌታ በቁጣው ጥቁር ደመና የጽዮንን ሴት ልጅ ፈጽሞ ከደናት! የእስራኤልን ውበት ከሰማይ ወደ ምድር ጣለ፥ በቁጣው ቀን የእግሩን መር ግጫ ችላ አለ።
2ጌታ የያዕቆብን ከተማዎች ሁሉ ዋጠ፥ ርኅራኄም አልነበረውም። በቁጣው የጽዮንን ሴት ልጅ የተመሸጉ ከተማዎች ጣለ፤ መንግሥቱ ንና ልዑላኗን አቃለለ፥አዋርዶ ወደ ምድር መትቶ ጣላችው።
3በብርቱ ቁጣው የእስራኤልን ብርታት ሁሉ ቆረጠ፥ ከጠላት ፊት ቀኝ እጁን ወደ ኋላ መለሰ፥ በዙሪያው ያለውን ሁሉ እንደሚበላ የሚንቦገቦግ እሳት ያዕቆብን አቃጠለ።
4እንደ ጠላት ቀስቱን በእኛ ላይ ገተረ፥ እንደ ባላጋራ ወርውሮ ሊገድል እጆቹ ተዘጋጅተው በተጠንቀቅ ቆመ። ለዓይን እጅግ የከበሩትን ሰዎች ሁሉ አረደ፥ በጽዮን ሴት ልጅ ድንኳን ውስጥ ቁጣውን እንደ እሳት አፈሰሰ።
5ጌታ እንደ ጠላት ሆነ። እስራኤልን ዋጠ። ቤተ መንግሥቶቿን ሁሉ ዋጠ፤ምሽጎቿን አጠፋ። በይሁዳ ሴት ልጅ ውስጥ ለቅሶንና ሰቆቃን አበዛ።
6ድንኳኑን እንደ አትክልት ቦታ አጠፋ። የታላቁን ጉባዔ ስፍራ አፈረሰ። በቁጣው ትኩሳት ንጉሡንና ካህኑን ንቋልና እግዚአብሔር በጽዮን ታላቁን ጉባዔና ሰንበትን እንዲረሱ አደረገ።
7ጌታ መሠዊያውን ጣለ፥ መቅደሱን አልተቀበለም። የቤተ መንግሥቶቿን ግንቦች በጠላት እጅ አሳልፎ ሰጠ። በታላቅ ጉባዔ ቀን እንደሚሆን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የድል ድምጽ አሰሙ።
8እግዚአብሔር የጽዮንን ሴት ልጅ የከተማ ቅጥር ለማፍረስ ወሰነ። የመለኪያውን ገመድ ዘረጋ፥ቅጥሩን ከማፍረስ እጁን አልመለሰም። ምሽጎቿ እንዲያለቅሱ፥ቅጥሮቿ አቅመ አልባ እንዲሆኑ አደረገ።
9በሮቿ ወደ መሬት ሰመጡ፥ የበሮቿን መቀርቀሪያዎች አጠፋ፥ ሰበረም።ንጉሧና ልዑላኖቿ የሙሴ ሕግ በሌለበት በአሕዛብ መካከል ናቸው። ነቢያቶቿም እንኳን ሳይቀሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ ራዕይ አላገኙም።
10የጽዮን ሴት ልጅ ሽማግሌዎች መሬት ላይ ተቀምጥዋል፥ በዝምታም ይቆዝማሉ። በራሳቸው ላይ አቧራ ነሰነሱ፥ የሐዘንም ልብስ ለበሱ። የኢየሩሳሌም ደናግል ራሳቸውን ወደ መሬት ዝቅ አደረጉ።
11እንባዬ ደረቀ፥ዓይኖቼ ቀሉ፥ የውስጥ ሰዉነቴ ታወከ። ልጆችና የሚያጠቡ ሕጻናት በመንደሮች መንገዶች ላይ ያለ ምንም ተስፋ ደክመዋልና፥ የሕዝቤም ሴት ልጆች ደቅቀዋልና ጉበቴ በመሬት ላይ ተዘረገፈ።
12በከተማይቱ መንገዶች ላይ እንደ ቆሰለ ሰው ዝለው ሳሉ፥ በእናቶቻቸው እቅፍ ነፍሳቸው እየፈሰሰች ሳሉ፥ እናቶቻቸውን፦ «እሕሉና ወይኑ የት አለ?» ይላሉ።
13የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፥ ስለ አንቺ ምን ማለት እችላለሁ? የጽዮን ድንግል ሆይ አጽናናሽ ዘንድ ከምን ጋር አመሳስልሻለሁ? ውድቀትሽ እንደ ባሕር ታላቅ ነው። ሊፈውስሽ የሚችል ማነው?
14ነቢያቶችሽ የሚያስትና ከንቱ ራዕይ አይተውልሻል። በረከትሽን ይመልሱ ዘንድ በደልሽን አለገለጡም፤ ነገር ግን የሚያስት ትንቢትና የሚያጠምድ ራዕይ ተቀበሉ።
15በመንገድ የሚያልፉ ሁሉ እጃቸውን በአንቺ ላይ ያጨበጭባሉ። በኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ይዝታሉ፥ራሳቸውንም ይነቀንቃሉ፥ ደግሞም «'የውበት ሁሉ መጨረሻ'፥ 'የምድር ሁሉ ደስታ' ብለው የሚጠሯት ከተማ ይህቺ ናትን?» ይላሉ።
16ጠላቶችሽ ሁሉ አፋቸውን እጅግ ይከፍታሉ፥ ያላግጡብሻልም። እያፏጩና ጥርሳቸውን እያፋጩ፦ «ዋጥናት! በእርግጥም የተጠባበቅናት ቀን ይህቺ ናት! አገኘናት! አየናትም!» ይላሉ።
17እግዚአብሔር የወሰነውን አደረገ። ከረዥም ጊዜ በፊት ያወጀውን ቃሉን ፈጸመ። አፈረሰ፥ርኅራኄም አልነበረውም፤ ጠላትሽ በአንቺ ላይ እንዲደሰት ፈቀደ፥ የጠላቶሽን ብርታት ከፍ ከፍ አደረገ።
18ልባቸው ወደ ጌታ ጮኽ፤የጽዮን ሴት ልጅ ቅጥር ሆይ እንባሽ እንደ ወንዝ ቀንና ሌሊት ይፍሰስ። ለራስሽ የእፎይታ ጊዜ አትስጪ። የአይኖችሽን ማፍሰስ አታስቁሚ።
19በሌሊት ተነሺና ጩኺ፥ ከሌሊቱ መጀመሪያ አንስቶ በጌታ ፊት ልብሽን እንደ ውኃ አፍስሺ። በየመንገዱ ራስ ላይ በረሀብ ደክመው ስለወደቁት ልጆችሽ ሕይወት እጆችሽን ወደ እርሱ አንሺ።
20እግዚአብሔር ሆይ ተመልከት፥ ጽኑ መከራን ስላመጣህባቸው ስለ እነዚያ ሰዎች ግድ ይበልህ። ሴቶች የራሳቸውን ፍሬ፥ የሚሳሱላቸውን ልጆቻቸውን ይብሉን? ካህኑና ነቢዩ በጌታ መቅደስ ውስጥ ይታረዱን?
21ወጣቱና ሽማግሌው በአንድነት በየመንገዶቹ በመሬት ላይ ወደቁ። ደናግሎቼና ኃያላን ወንዶቼ በሰይፍ ወደቁ። በቁጣህ ቀን አረድሃቸው፥በጭካኔ ገደልካቸው፥ ርኅራኄም አልነበረህም።
22በከበረው ጉባዔ ቀን እንደሚሆን ከዙሪያው ሁሉ ሽብርን ጥራህብኝ፤ ማንም አላመለጠም፥ በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን የተረፈ ማንምአልነበረም። የተንከባከብኳቸውንና ያሳደግኋቸውን ጠላቴ አጠፋቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።