1አሁን እስቲ ተጣራ፤ የሚመልስ አንድ እንኳ አለ? ከቅዱሳንስ ወደየትኛው ትዞራለህ?
2ሰነፍን ሰው ቍጣ ይገድለዋል፥ ሞኙንም ቅንዓት ያጠፋዋል።
3ቂል ሰው ሥር ሲሰድድ አየሁ፥ ነገር ግን በድንገት ቤቱን ረገምሁት።
4ልጆቹም ከደኅንነት ከለላ ውጪ ናቸው፥ በከተማም አደባባይ የተረገጡ ናቸው፥ አንድም የሚያድናቸው የለም።
5የተሰበሰበውን ሰብል በተራቡ በሌሎች ተበላ፥ ከእሾህ ውስጥ እንኳ የወጡ ሰዎች ወሰዱት፤ ያለውም ሁሉ ሀብትን በተጠሙ ሰዎች ተዋጠ።
6ችግር እንዲሁ ከአፈር አይመጣም፥ መከራም ከመሬት አይመነጭም፤
7ነገር ግን የእሳት ፍንጣሪዎች ወደ ላይ እንደሚበርሩ፥ እንዲሁ ሰው መከራን በራሱ ላይ ያመጣል።
8እኔ ግን እግዚአብሔርን ወደራሱ፥ ጉዳዬን ወደ ማቀርብለት ወደ እግዚአብሔር እመለስ ነበር።
9እርሱ ታላቅና የማይመረመሩ ዋና ነገሮችንና የማይቈጠሩ አስደናቂ ነገሮችን ያደርጋል።
10በምድር ላይ ዝናብን ይሰጣል፥ በእርሻም ላይ ውኃ ይልካል።
11የተዋረዱትን በከፍታ ሊያኖር ፥ ኀዘንተኞችንም ለደኅንነት ከፍ ለማድረግ ይህንን ያደርጋል።
12እጃቸው እቅዳቸውን እንዳይፈጽም የተንኰለኞችን ወጥመድ ከንቱ ያደርጋል።
13ጠቢባንን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል የተንኮለኞችንም ዕቅድ ያጠፋል።
14በቀን ከጨለማ ጋር ይጋጠማሉ፥ በዕኩለቀንም በሌሊት እንዳሉ ያክል በዳበሳ ይሄዳሉ።
15ነገር ግን ድሀውን ከአፋቸው ሰይፍ፤ ችግረኛውንም ከኃያላን እጅ ያድነዋል።
16ስለዚህ ድሀው ተስፋ አለው፤ ፍትህ አልባነት ግን አፍዋን ትዘጋለች።
17እነሆ፥ እግዚአብሔር የሚያርመው ሰው ምስጉን ነው፤ ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን አምላክንተግሣጽ አትናቅ።
18ምክንያቱም እርሱ ይሰብራል፥ ይጠግናል ያቈስላል በኋላም በእጆቹ ይፈውሳል።
19እርሱ ከስድስት ክፉ ነገሮች ውስጥ ያወጣሃል፥ በርግጥ በሰባተኛው ክፋት አይነካህም።
20በራብ ጊዜ ከሞት፥ በጦርነትም ከሰይፍ ስለት ያድንሃል።
21ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፤ ጥፋትም ሲመጣ አትፈራም።
22በጥፋትና በራብ ላይ ትስቃለህ፤ የምድር አውሬዎችንም አትፈራም፤
23ከምድርህ ድንጋይ ጋር ኪዳን ይኖርሃል ከምድር አራዊትም ጋር በሰላም ትሆናለህ።
24ድንኳንህም በደህንነት እንዳለ ታውቃለህ፤ በረትህን ትጐበኛለህ አንድም አይጠፋብህም።
25ዘሮችህም ታላቅ እንደሚሆኑ፥ ትውልድህም እንደ ምድር ሣር እንደሚበዙ ታውቃለህ።
26የእህሉ ነዶ ደርሶ በወቅቱ ወደ አውድማ እንደሚገባ፥ ዕድሜን ጠግበህ ወደ መቃብር ትሄዳለህ።
27እነሆ፥ ይህንን ነገር መረመርን፥ ነገሩ እውነት ነው፤ ልብ በለው፤ የራስህም እውቀት አድርገው።