መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢዮብ 4

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ቴማናዊውም ኤልፋዝ እንዲህ ሲል መለሰ ፦
2አንድ ሰው ከአንተ ጋር ለመነጋገር ቢሞክር ታዝናለህን? ነገር ግን ከመናገር ራሱን ሊገታ የሚችል ማን ነው?
3እነሆ፥ አንተ ብዙዎችን ታስተምር ነበር፥ የደከሙትንም እጆች ታበረታ ነበር፥
4ቃልህ ሊወድቅ የተሰናከለውን ያስነሣ ነበር፥ አንተም የሚብረከረከውን ጕልበት ታጸና ነበር።
5አሁን ግን ጥፋት በአንተ ላይ መጥቶአል፥ አንተም ደከመህ፤ በርግጥ ደረሰብህ፥ አንተም ታወክህ።
6እግዚአብሔርን መፍራትህ ድፍረትን፥ ያካሄድህስ ቀናነት ተስፋን አይሰጥህምን?
7እባክህ ይህን እንድታስብ እለምንሃለሁ፥ ንጹሕ ሆኖ የጠፋ ማን አለ? ልበ ቅንስ ሆኖ የተደመሰሰ ማን ነው?
8እኔ እንዳየሁ፥ ኃጢአትን የሚያርሱ፥ ሁከትንም የሚዘሩ መልሰው ያንኑ ያጭዳሉ።
9በእግዚአብሔር እስትንፋስ ይጠፋሉ፥ በቍጣውም ንዳድ ያልቃሉ።
10የአንበሳ ግሳት፥ የቁጡ አንበሳ ድምፅ፥ የደቦል አንበሳ ጥርስ ተሰባብረዋል።
11ያረጀ አንበሳ አደን አጥቶ ይሞታል፥ የአንበሳይቱም ግልገሎች የትም ይበተናሉ።
12ለእኔም ነገሩ በምሥጢር መጣልኝ፥ ጆሮዬም ስለነገሩ ሹክሹክታን ሰማች።
13ከባድ እንቅልፍ በሰው ላይ በሚሆንበት ጊዜ፥ በሃሳብ ብዛት በሌሊት ሕልም ሲመጣ፥
14ድንጋጤና መንቀጥቀጥ መጡብኝ አጥንቶቼም ሁሉ ተንቀጠቀጡ
15በፊቴም መንፈስ አለፈ የሰውነቴም ጠጕር ቆመ።
16መንፈሱም ቆመ፥ መልኩን ግን ለመለየት አልቻልሁም፥ ቅርጹ በዓይኔ ፊት ነበረ፤ ጸጥታም ሆነ እንዲህም የሚል ድምፅ ሰማሁ፤
17“በውኑ ሥጋ የለበሰ ሰው ከእግዚአብሔር ይልቅ ጻድቅ ሊሆን ይችላልን?ሰውስ ከፈጣሪው ይልቅ ንጹህ ሊሆን ይችላልን?”
18እነሆ፥ እግዚአብሔር በአገልጋዮቹ ካልተማመነ፤ መላእክቱንም በስህተት ከወቀሳቸዋል፤
19ይልቁንስ በሸክላ ቤቶች ውስጥ በሚኖሩ፥ መሠረታቸውም በትቢያ ውስጥ ለሆነ፥ ከብል ቀድመው በሚጠፉት ዘንድ ይህ እንዴት እውነት ይሆን?
20በጥዋትና በማታ መካከል ይጠፋሉ፤ ማንም ሳያውቀው እስከ ወዲያኛው ይጠፋሉ።
21የድንኳናቸው ገመድ ከመካከላቸው የተነቀለ አይደለምን? ይሞታሉ፦ ያለጥበብም ይሞታሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።