1ከዚህም በኋላ ኢዮብ አፉን ከፍቶ የተወለደበትን ቀን ረገመ።
2እንዲህም አለ፦
3“ያ የተወለድሁበት ቀን ፤ 'ወንድ ልጅም ተፀነሰ' የተባለበት ሌሊት ይጥፋ”
4ያ ቀን ጨለማ ይሁን እግዚአብሔርም ከላይ አያስበው ፤ የጸሀይ ብርሀንም አያግኝው።
5ጨለማና የሞት ጥላ የራሳቸው እንደሆነ ይቁጠሩ፤ ዳመናም ይኑርበት፤ ቀኑን የሚያጨልሙ ነገሮች ሁሉ በርግጥ ያስደንግጡት።
6ያንን ሌሊት ድቅድቅ ጨለማ ይያዘው፤ በዓመቱ ካሉት ቀኖች ጋር ደስ አይበለው፤ በወራት ውስጥ ገብቶ አይቈጠር።
7ያቺ ምሽት መካን ትሁን፤ ወደ እርሷም የደስታ ድምጽ አይግባበት።
8ሌዋታንን እንዴት ማንቃት እንዳለባቸው የሚያውቁ ያንን ቀን ይርገሙት።
9አጥቢያ ኮከቦች ይጨልሙ፤ ያ ቀን ብርሃንን ሲጠባበቅ አያግኝ፥ የንጋትንም ወገግታ አይመልከት፤
10ምክንያቱም የእናቴን ማኅፀን ደጅ አልዘጋምና፥ መከራንም ከዓይኔ አልሰወረምና።
11ከማኅፀን ስወጣ ስለ ምን አልሞትሁም? እናቴ ስትወልደኝስ ስለምን አልጠፋሁም?
12ጕልበቶቿ ስለ ምን ተቀበሉኝ? ጡቶቿስ እንድጠባ ስለ ምን ተቀበሉኝ?
13ይሄኔ በጸጥታ በተጋደምሁ፤
14አሁን ፈርሶ ያለውን መቃብር ለራሳቸው ከገነቡት የምድር ነገሥታትና አማካሪዎች ጋር፥ አንቀላፍቼም ባረፍሁ ነበር፤
15ወይም ባንድ ወቅት ቤታቸውን በብር ከሞሉ ወርቅም ከነበራቸው መኳንንት ጋር በተጋደምሁ ነበር፥
16ወይም ያለጊዜያቸው እንደተወለዱ፥ ብርሃንንም አይተው እንደማያውቁ ሕፃናት በሆንሁ ነበር።
17በዚያ ክፉዎች ረብሻቸውን ያቆማሉ፤ የደከሙትም በዚያ ያርፋሉ።
18በዚያ እስረኞች አርፈው በአንድነት ይቀመጣሉ፤ የአስጨናቂውን ጠባቂ ድምፅ አይሰሙም።
19ታናናሽና ታላላቅ ሰዎች በዚያ አሉ፤ በዚያም ባሪያ ከጌታው ነጻ ወጥቶአል።
20በመከራ ላለ ሰው ብርሃን ፤ ነፍሳቸው መራራ ለሆነችባቸውስ ህይወት፤
21የተሰወረን ሀብት ከሚፈልጉ ይልቅ ሞትን እየተመኙ ላልመጣላቸው ህይወት ለምን ተሰጠ?
22መቀበሪያቸውን ባገኙ ጊዜ እጅግ ደስ ለሚላቸው፥ ሐሤትንም ለሚያደርጉ ሕይወት ለምን ተሰጠ?
23መንገዱ ለጠፋበት ሰው፥ እግዚአብሔርም አጥር ላጠረበት ሰው ብርሃን ለምን ተሰጠ?
24በመመገብ ምትክ ሲቃዬ ፈጥኖ ይመጣልና፥ መቃተቴም እንደ ውኃ ፈስሶአል።
25የፈራሁት ነገር መጥቶብኛልና፥ የደነገጥሁበትም ደርሶብኛል።
26በእርጋታና በጸጥታ አልተቀመጥሁም፥ አላረፍሁም ይልቅ መከራና ችግር መጣብኝ።