1ያን ጊዜ እግዚአብሔር ከብርቱ ዐውሎ ነፋስ ውስጥ ኢዮብን ጠራውና እንዲህ አለው፥
2"ዕውቀት በጎደለው ቃል ዕቅዴን የሚያጨልም ይህ ማነው?
3ጥያቄዎችን እጠይቅሃለሁና አሁን እንደ ሰው ወገብህን ታጠቅ፥ አንተም ልትመልስልኝ ይገባሃል።
4የምድርን መሠረቶች ባቆምኩ ጊዜ አንተ የት ነበርክ? ከፍ ያለ ማስተዋል ካለህ ነገረኝ።
5መጠኑን የወሰነው ማነው? የምታውቅ ከሆነ ንገረኝ። በላዩ ላይስ የመለኪያ ገመድ የዘረጋ ማነው?
6መሠረቶቹስ የቆሙት በምን ላይ ነው?
7የንጋት ከዋክብት በአንድነት በዘመሩና የእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ በደስታ በዘመሩ ጊዜ የማዕዘኑን ድንጋይ ያስቀመጠ ማን ነበር?
8ደመናትን ልብሱ፥ ድቅድቁንም ጨለማ መጠቅለያው ባደረግሁ ጊዜ
9ከማኅፀን የሚወጣ ይመስል ፈንድቶ በወጣ ጊዜ የባህሩን መዝጊያ የዘጋ ማነው?
10ያን ጊዜ ነበር ለባህሩ ገደብን ያደረግሁለት፥ በሮችንና መወርወሪያዎችን ባደረግሁለት ጊዜ፥
11እንዲህም ባልኩት ጊዜ፥ 'እስከዚህ ድረስ መምጣት ትችል ይሆናል፥ ከዚህ ግን አትለፍ፤ ለሞገድህ ትዕቢት ገደብ የማደርግለት እዚህጋ ነው'።
12ከተወለድክበት ጊዜ ጀምሮ ንጋት እንዲጀምር ከቶ ትዕዛዝ ሰጥተኸዋል? ወጋገኑስ በነገሮች መካከል ስፍራውን እንዲያውቅ አድርገኸዋል?
13የምድርን ማዕዘናት በመያዝ ክፉዎች ሰዎች ከእርሱ ላይ እንዲራገፉ አድርገሃል?
14ጭቃው ከማኅተም በታች እንደሚለወጥ የምድርም መልክ ተለውጧል፤ በእርሱ ላይ ያለው ነገር ሁሉ በግልጽ እንደ ቁራጭ ጨርቅ ተጠቅልሎ ቆሟል።
15ከክፉ ሰዎች 'ብርሃናቸው' ተወስዷል፤ ወደ ላይ የተነሣው ክንዳቸውም ተሰብሯል።
16ወደ ባህሩ መገኛ ሄደህ ታውቃለህ? ዝቅ ወዳለው ጥልቅ ስፍራስ ወርደህ ታውቃለህ?
17የሞት በሮች ተገልጠውልሃል? የሞት ጥላ በሮችንስ አይተኻቸዋል?
18ምድርን በስፋቱ ታውቀዋለህ? ይህንን ሁሉ የምታውቅ ከሆነ ንገረኝ።
19ብርሃን የሚያርፍበት ስፍራ መንገዱ የት ነው? የጨለማውስ ስፍራው የት ነው?
20ብርሃንና ጨለማን ወደ ሥራቸው ስፍራ ልትመራቸው ትችላለህ? ወደ መኖሪያቸው የሚመለሱበትን መንገድስ ልትፈልግላቸው ትችላለህ?
21ያን ጊዜ ተወልደህ ስለነበርና የዕድሜህም ቁጥር ታላቅ ስለሆነ ያለጥርጥር ታውቃለህ!
22ወደ በረዶው መጋዘን ገብተሃል? ወይም የአመዳዩን ማከማቻ አይተሃል?
23እነዚህን ነገሮች ለመከራ ጊዜ፥ ለጦርነትና ለውጊያ ቀናት ያስቀመጥኳቸው ናቸው።
24የመብረቅ ብልጭታ የሚሰራጭበት መንገድ የትኛው ነው? ወይም ነፋሳት ከምስራቅ በምድር ላይ የሚበተኑበት መንገድ የቱ ነው?
25ለዶፍ ዝናብ መውረጃን ያበጀለት ወይም ለመብረቅ ብልጭታ መንገድ ያዘጋጀለት ማነው?
26ሰው በሌለበት ምድር፥ ማንም በሌለበት ምድረ በዳ ላይ እንዲዘንብ ያደረገ ማነው?
27ሰው የሌለበትንና የባድማውን አካባቢ ፍላጎት የሚያረካ፥ ሣር እንዲበቅልበትስ የሚያደርግ ማነው?
28ዝናብ አባት አለው? የጤዛን ጠብታ የወለደው ማነው?
29በረዶስ የመጣው ከማን ማኅፀን ነው? የሰማዩን አመዳይ ማን ወለደው?
30ውኆች ራሳቸውን ይደብቁና እንደ ድንጋይ ይጠነክራሉ፤ የጥልቁም ገጽታ ግግር ይሆናል።
31ፕልያዲስ የተባለውን ኮከብ በሠንሰለት ልታስረው ወይም የኦሪዮንን እስራት ልትፈታ ትችላለህ?
32የከዋክብት ክምችት በተገቢው ጊዜአቸው እንዲታዩ ልትመራቸው ትችላለህ? ድብ የተባለውን ከነልጆቹ ልትመራቸው ትችላለህ?
33የሰማይን ሥርዓት ታውቃለህ? የሰማይን ሥርዓት በምድር ላይ መተግበር ትችላለህ?
34ብዙ የዝናብ ውሃ እንዲያጥለቀልቅህ ድምፅህን ወደ ደመናት ማሰማት ትችላለህ?
35'ይኸው እዚህ አለን' ብለው ይላኩህ ዘንድ የመብረቅ ብልጭታዎችን ልትልካቸው ትችላለህ?
36በደመናት ውስጥ ጥበብን ያኖረ ወይም ለእርጥበት ዕውቀትን የሰጠ ማነው?
37በጥበቡ ደመናትን ለመቁጠር የሚችል ማነው?
38ብናኙ ዐፈር ተበጥብጦ ጠንካራ ጓል በሚሆንበትና ጭቃው አፈር በአንድ ላይ በሚጣበቅበት ጊዜ የሰማይን የውሃ መያዣ አዘንብሎ ማፍሰስ የሚችል ማነው?
39በዋሻዎቻቸው በሚያደቡበትና በመኖሪያቸው ተጋድመው በሚጠባበቁበት ጊዜ
40ለአንበሳዪቱ አደን ልታድንላት ወይም ግልገሎቿን ልታጠግብላት ትችላለህ?
41ጫጩቶቻቸው ወደ እግዚአብሔር በሚጮኹበትና ምግብ በማጣት በሚንከራተቱበት ጊዜ ለቁራዎች ምግብ የሚሰጣቸው ማነው?