1በርግጥ በዚህ ጉዳይ ልቤ ተናውጧል፤ ስፍራውንም ለቋል።
2ኦ እስቲ አድምጡ፤ የድምፁን ሁካታ፥ ከአፉም የሚወጣውን ድምፅ አድምጡ።
3እርሱ ድምፁን ከሰማይ በታች ወዳለ ስፍራ ሁሉ ይልካል፥ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም መብረቁን ይልካል።
4ከእርሱ በኋላ ድምፅ ይጮኻል፤ በግርማዊ ድምፁም ያንጎደጉዳል፤ ድምፁ በሚሰማበት ጊዜ የመብረቁን ብልጭታ አይከለክልም።
5እግዚአብሔር በድምፁ በሚያስደንቅ ሁኔታ ያንጎደጉዳል፤ ልናስተውላቸው የማንችላቸውን ታላላቅ ነገሮችንም ያደርጋል።
6በረዶውን፥ 'በምድር ላይ ውደቅ'፤ እንዲሁም ዝናቡን፥ 'ብርቱ ዝናብ ሆነህ ውረድ' ይለዋል።
7ሰዎች ሁሉ ያደረገውን ሥራውን እንዲያዩ የእያንዳንዱን ሰው እጅ ከመሥራት ይከለክላል።
8ከዚያም አራዊት ወደ መደበቂያቸው ይሄዳሉ፥ በዋሻዎቻቸውም ውስጥ ይቆያሉ።
9ዐውሎ ነፋስ ከደቡብ መኖሪያው ይመጣል፤ ቅዝቃዜም በሰሜን ከተበተነው ነፋስ።
10በእግዚአብሔር እስትንፋስ በረዶ ይገኛል፤ የውኆቹም ስፋት እንደ ብረት ይቀዘቅዛል።
11በርግጥ ጥቅጥቁን ደመና በሙቀት ይበትነዋል፤ መብረቆቹን በደመናዎች መካከል ይበትናቸዋል።
12በመላው ዓለም ላይ ፈቃዱን ያደርጉ ዘንድ በአመራሩ ደመናትን ያሽከረክራቸዋል።
13እነዚህ ሁሉ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፤ ይህንን የሚያደርገው አንዳንድ ጊዜ ለማቅናት፥ አንዳንዴም ምድሩን ለማጠጣት፥ አንዳንዴም የቃል ኪዳን ታማኝነቱን ለማሳየት ነው።
14ኢዮብ ሆይ፥ ይህንን ስማ፤ ቆም በልና የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራዎች አስብ።
15እግዚአብሔር እንዴት ፈቃዱን በደመናት ላይ እንደሚፈጽም፥ የመብረቁንም ብልጭታ በእነርሱ ውስጥ እንዲበራ እንደሚያደርግ ታውቃለህ?
16በዕውቀቱ ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራዎች፥ የደመናትንም መንሳፈፍ ታስተውላለህ?
17ከደቡብ በሚመጣው ነፋስ ምክንያት ምድር ጸጥ በምትልበት ጊዜ ልብስህ እንዴት እንደሚሞቅ ታስተውላለህ?
18ከብረት የተሠራ ጠንካራ መስታወት የሚመስለውን ሰማይ እንደ እርሱ መዘርጋት ትችላለህ?
19አዕምሮአችን ከመጨለሙ የተነሣ ክርክራችንን በሥርዓት ማቅረብ አልቻልንምና ምን እንደምንመልስለት አስተምረን።
20ላነጋግረው እንደምፈልግ ይነገረው ዘንድ ይገባል? አንድ ሰው እንዲዋጥ ይፈልጋል?
21እነሆ፥ ነፋስ በውስጡ ካለፈና ደመናውን ካጠራው በኋላ በሰማይ ላይ የሚያበራውን ፀሐይ ሰዎች ለማየት አይችሉም።
22እንደ ወርቅ የሚያብረቀርቅ ብርሃን ከሰሜን ይመጣል- በእግዚአብሔር ዘንድ አስፈሪ ግርማ አለ።
23ሁሉን ቻዩን በሚመለከት እኛ ልናገኘው አንችልም፤ እርሱ በጽድቁና በኃይሉ ታላቅ ነው። ሰዎችን አያስጨንቅም።
24ስለዚህ፥ ሰዎች ይፈሩታል። ጥበበኞች ነን ብለው የሚያስቡትን አይመለከታቸውም"።