1የበረሃ ፍየሎች በዐለቶች መካከል የሚወልዱበትን ጊዜ ታውቃለህ? አጋዘኖችስ ግልገሎቻቸውን በሚወልዱበት ጊዜ ልታያቸው ትችላለህ?
2የእርግዝናቸውንስ ወራት ለመቁጠር ትችላለህ? የሚወልዱበትንስ ጊዜ ታውቃለህ?
3ይንበረከኩና ግልገሎቻቸውን ይወልዳሉ፤ የምጣቸውንም ሕመም ያበቃሉ።
4ግልገሎቻቸው ይጠነክራሉ፥ በገላጣው መስክ ላይም ያድጋሉ፤ ርቀው ይሄዳሉ፥ ወደ ወለዷቸውም አይመለሱም።
5የሜዳ አህያው በነጻነት እንዲሄድ የፈቀደለት ማነው?
6አራባህን ቤቱ፥ የጨውንም ምድር መኖሪያው ያደረግሁለትን የፈጣኑንስ አህያ እስራት የፈታ ማነው?
7በከተማ ባለው ሁካታ በንቀት ይስቃል፤ የነጂውንም ጩኸት አይሰማም።
8በመሰማሪያዎቹ በተራሮች ላይ ይንከራተታል፤ በዚያም የሚመገበውን የለመለመ ሣር ሁሉ ይፈልጋል።
9ጎሽ ሊያገለግልህ ይፈቅዳል? በበረትህስ አጠገብ ለማደር ይስማማል?
10ጎሽ ትልሞችህን እንዲያርስልህ በገመድ ልትቆጣጠረው ትችላለህ? ጓሉንስ ይከሰክስልሃል?
11ጉልበቱ ብርቱ ስለሆነ ትታመነዋለህ? እርሱ እንዲያከናውንልህ ተግባርህን ትተውለታለህ?
12ምርትህን ዐውድማ ላይ እንዲያከማችልህ፥ እህልህንም ወደ ቤት እንዲያገባልህ ትተማመነዋለህ?
13የሰጎን ክንፎች በደስታ ይራገባሉ፤ ነገር ግን እነርሱ የፍቅር ክንፎችና ላባዎች ናቸው?
14እንቁላሎቿን በአፈር ውስጥ ትጥላለች፥ እንዲሞቃቸውም በትቢያ ውስጥ ትተዋቸዋለች።
15እግር እንዲረግጣቸው ወይም የዱር አውሬ እንዲጨፈልቃቸው ትረሳቸዋለች።
16የእርስዋ ያልሆኑ ይመስል በጫጩቶቿ ትጨክናለች፤ ድካሟ ሁሉ ከንቱ እንደሚሆን በማሰብ አትፈራም፤
17እግዚአብሔር ጥበብን ነፍጓታልና አንዳች ማስተዋልንም አልሰጣትም።
18በፍጥነት በምትሮጥበት ጊዜ በፈረሱና በጋላቢው ላይ በንቀት ትሥቃለች።
19ለፈረስ ኃይሉን ሰጥተኸዋል? አንገቱንስ በጋማው አልብሰኸዋል?
20እንደ አንበጣ እንዲዘል አድርገኸዋል? የማንኮራፋቱ ገናናነት አስፈሪ ነው።
21በኃይል ይጎደፍራል፥ በብርታቱም ደስ ይለዋል፤ የጦር መሳሪያዎችን ለመገናኘት ይፈጥናል።
22በፍርሃት ላይ ይሳለቃል፥ አይደነግጥምም፤ ከሰይፍም ወደ ኋላ አይመለስም።
23ከሚብለጨለጨው ፍላጻና ጦር ጋር የፍላጻዎች መያዣ ጎኑ ላይ ይንኳኳል።
24በቁጣና በጭካኔ መሬትን ይውጣል፤ የመለከት ድምፅ ሲሰማ ይቁነጠነጣል።
25የመለከት ድምፅ በሚሰማበት ጊዜ ሁሉ 'አሃ!' ይላል፤ ጦርነትን፥ የአዛዦችን የሚንጎደጎድ ጩኸትና ሁካታ ከሩቅ ያሸታል።
26ጭልፊት ርቆ የሚመጥቀው፥ ክንፎቹንም ወደ ደቡብ የሚዘረጋው ባንተ ጥበብ ነው?
27ንስር ወደ ላይ የሚበረውና ጎጆውን ከፍ ባሉ ስፍራዎች የሚሠራው ባንተ ትዕዛዝ ነው?
28በገደል ላይ ይኖራል፥ መኖሪያ ምሽጉንም በገደሉ ጫፍ ላይ ያደርጋል።
29እዚያ ላይ ሆኖ የሚነጥቀውን ይቃኛል፤ ዐይኖቹም ከርቀት ይመለከቱለታል።
30ጫጩቶቹ ደግሞ ደም ይጠጣሉ፤ በድን ባለበት እርሱም በዚያ አለ"።