1ኤሊሁ እንዲህ በማለት ንግግሩን ቀጠለ፥
2"ትንሽ ጨምሬ እንድናገር ፍቀድልኝ፥ እግዚአብሔርን በመወገን ትንሽ አክዬ የምናገረው አለኝና ጥቂት ነገሮችን አሳይሃለሁ።
3ዕውቀቴን ከሩቅ አመጣለሁ፤ ጽድቅ የፈጣሪዬ ነው እላለሁ።
4በርግጥ ቃሎቼ ሐሰት አይደሉም፤ አንድ በዕውቀት የበሰለም ከአንተ ጋር ነው።
5ተመልከት፥ እግዚአብሔር ኃያል ነው፥ ማንንም አይንቅም፤ እርሱ በማስተዋል ብርታቱም ኃያል ነው።
6እርሱ የአመጸኞች ሰዎችን ሕይወት አይጠብቅም ነገር ግን ከዚያ ይልቅ መከራ ለሚቀበሉት ትክክል የሆነውን ነገር ያደርግላቸዋል።
7ፊቱን ከጻድቃን አይመልስም ነገር ግን ከዚያ ይልቅ እንደ ነገሥታት በዙፋኖች ላይ ያስቀምጣቸዋል፥ እነርሱም ይከብራሉ።
8ይሁንና፥ በሰንሰለት ቢገቡ፥ በመከራም ገመድ ቢታሰሩ
9ያን ጊዜ ያደረጉትን መተላለፋቸውንና በግፍ እንደተመላለሱ ይገልጥላቸዋል።
10ደግሞም እርሱ ጆሮዎቻቸውን ለትምህርቱ ይከፍታቸዋል፥ ከክፋታቸው እንዲመለሱም ያዛቸዋል።
11ቢሰሙትና ቢያመልኩት ቀኖቻቸውን በብልጽግና ዓመቶቻቸውንም በእርካታ ያሳልፋሉ።
12ይሁን እንጂ፥ ባይሰሙት በሰይፍ ይጠፋሉ፤ ዕውቀት ስለሌላቸው ይሞታሉ።
13ልባቸው ከእግዚአብሔር የራቀ እነዚያ ቁጣቸውን ያከማቻሉ፤ እግዚአብሔር በሚያስራቸው ጊዜ እንኳን ለዕርዳታ አይጮኹም።
14በወጣትነታቸው ይሞታሉ፤ ሕይወታቸውም በቤተ ጣዖት ዝሙት አዳሪዎች መካከል ይጠፋል።
15የሚሰቃዩትን ሰዎች በስቃያቸው አማካይነት ያድናቸዋል፤ በመከራቸው አማካይነትም ጆሮዎቻቸውን ይከፍታል።
16በእርግጥ እርሱ ከጭንቀት አውጥቶ የሰባ ምግብ የሞላበት ጠረጴዛ በፊትህ ወደሚቀመጥበትና ስቃይ ወደሌለበት ሰፊ ስፍራ ሊያወጣህ ይፈልጋል።
17ነገር ግን አንተ በክፉ ሰዎች ፍርድ ተሞልተሃል፤ ፍርድና ፍትሕም ይዘውሃል።
18ብልጽግና ወደ መታለል እንዲስብህ እትፍቀድለት፤ መጠኑ የበዛ ጉቦም ፍትሕን እንድታዛባ እንዲያደርግህ አትፍቀድለት።
19ብልጽግናህ ከሐዘን ሊያርቅህ ይችላል? ወይም የኃይልህ ብርታት ሁሉ ሊረዳህ ይችላል?
20ሰዎች በየስፍራቸው በሚወገዱበት ጊዜ በሌሎች ላይ ኃጢአትን ለመሥራት ጨለማን አትመኝ።
21ኃጢአትን ከማድረግ ትርቅ ዘንድ በመከራ ተፈትነሃልና ወደ ኃጢአት እንዳትመለስ ተጠንቀቅ።
22ተመልከት፥ እግዚአብሔር በኃይሉ ከፍ ያለ ነው፤ እንደ እርሱስ ያለ አስተማሪ ማነው?
23ስለ መንገዱ ከቶ ማን አስተምሮታል? 'በደለኛ ነህ' ሊለውስ ከቶ ማን ይችላል?
24ሰዎች የዘመሩለትን ሥራዎቹን ለማወደስ አስታውስ።
25እነዚያን ሥራዎች ሰዎች ሁሉ አይተዋል፥ ነገር ግን እነዚያን ሥራዎች የሚያዩት ከርቀት ብቻ ነው።
26ተመልከት፥ እግዚአብሔር ትልቅ ነው፤ እኛም በሚገባ አናውቀውም፤ ዘመኖቹም አይቆጠሩም።
27እርሱ እንፋሎቱ ዝናብ ሆኖ ይወርድ ዘንድ የውሃ ነጠብጣቦችን ወደ ላይ ስቦ ያከማቻል፥
28ደመናዎች ወደ ታች ያፈስሱታል፥ በሰዎች ላይም በብዙ ያንጠባጥቡታል።
29በርግጥ የደመናዎቹን መዘርጋትና ከድንኳኑ የሚወጣውን መብረቅ ሊያስተውል የሚችል አለ?
30ተመልከት፥ መብረቁን በዙሪያው ይበትናል፤ ባህሩን በጨለማ ይከድነዋል።
31በዚህ መንገድ ሰዎችን ይመግባቸዋል፥ ብዙ ምግብንም ይሰጣቸዋል።
32ዒላማቸውን እንዲመቱ እስኪያዛቸው ድረስ እጆቹን በመብረቅ ነጓድጓድ ይሸፍናቸዋል።
33ዐውሎ ነፋስ እንደሚመጣ ድምፁ ለሰዎች ይነግራቸዋል፤ መቃረቡንም እንስሶች ደግሞ ያውቃሉ።