1ኤሊሁ እንዲህ ሲል ንግግሩን ቀጠለ፥
2“ንጹሕ ነኝ ብለህ ታስባለህ? 'ከእግዚአብሔር ይልቅ ጻድቅ ነኝ' ብለህስ ታስባለህ?
3ጻድቅ መሆኔ ምን ይጠቅማል? ኃጢአት አድርጌ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የሚበልጥ ምን ያገኘኝ ነበር?' ብለሃልና።
4ለአንተና ለወዳጆችህ ምላሽ እሰጣለሁ።
5ወደ ሰማይ ቀና በሉና ተመልከቱት፤ ከእናንተ ከፍ የሚለውን ሰማይ ተመልከቱ።
6ኃጢአትን ብታደርግ እግዚአብሔርን ምን ትጎዳዋለህ? መተላለፍህ እጅግ የበዛ ቢሆን ለእርሱ ምኑ ነው?
7ጻድቅ ብትሆንስ ምን ልትሰጠው ትችላለህ? ከእጅህስ ምን ይቀበላል?
8አንተም ሰው ነህና ክፋትህ ሌላውን ይጎዳ ይሆናል፤ ጽድቅህም ሌላውን የሰው ልጅ ይጠቅመው ይሆናል።
9በብዙ በደል ምክንያት ሰዎች ይጮኻሉ፤ ከኃያላኑ እጅ የሚያድናቸውን ፍለጋ ይጣራሉ።
10ነገር ግን 'በሌሊት ዝማሬን የሚሰጥ፥
11የምድር አራዊትን ከሚያስተምርበት በበለጠ የሚያስተምረን፥ ከሰማይ አዕዋፍም ይልቅ ጥበበኞች የሚያደርገን ፈጣሪያችን እግዚአብሔር የት አለ?' ማንም አላለም።
12በዚያን ጊዜ ይጮኻሉ፥ ነገር ግን በክፉ ሰዎች ትዕቢት ምክንያት እግዚአብሔር ምንም ምላሽ አይሰጣቸውም።
13ያለጥርጥር እግዚአብሔር የሞኞችን ጩኸት አይሰማም፤ ሁሉን ቻዩም ትኩረት አይሰጠውም።
14ጉዳይህን በፊቱ አቅርበህ እየተጠባበቅኸው እያለህ እንዳላየኸው ከተናገርክ እንዴት አድርጎ መልስ ይሰጥሃል!
15ማንንም ተቆጥቶ አይቀጣም፥ በሰዎች ትዕቢት እምብዛም ግድ አይለውም ካልክ እንዴት አድርጎ መልስ ይሰጥሃል?
16ስለዚህ ኢዮብ አፉን የሚከፍተው ስንፍናን ለመናገር ብቻ ነው፤ ዕውቀት የሌለበትን ቃል መናገርንም ያበዛል"።