1ኤሊሁም በመቀጠል እንዲህ አለ፥
2”እናንተ ጥበበኞች፥ ቃሎቼን አድምጡ፤ እውቀት ያላችሁ እናንተ ስሙኝ።
3ምላስ ምግብን እንደሚያጣጥም ጆሮም ቃላትን ያመዛዝናል።
4ትክክለኛ የሆነውን ለራሳችን እንምረጥ፤ መልካም የሆነውንም በመካከላችን እንፈልገው።
5ኢዮብ 'እኔ ጻድቅ ነኝ እግዚአብሔር ግን መብቴን ነፍጎኛል። መብት ቢኖረኝም እንደ ሐሰተኛ ተቆጥሬአለሁ።
6ምንም እንኳን ኃጢአት ባይኖርብኝም ቁስሌ የማይፈወስ ነው' ብሏልና።
7ስድብን እንደ ውሃ የሚጠጣ፥
8ክፋትን ከሚያደርጉት ጋር እንደሚወዳጅ፥ ከአመጸኞችም ጋር እንደሚመላለስ እንደ ኢዮብ ያለ ማነው?
9እርሱ፥ 'ሰው እግዚአብሔር የሚፈልገውን በማድረግ መደሰቱ ምንም አይጠቅምም' ብሏልና።
10ስለዚህ እናንተ አዋቂዎች ስሙኝ፤ አመጻን ማድረግ ከእግዚአብሔር ይራቅ፤ ኃጢአትን ማድረግም ሁሉን ቻይ ከሆነው ይራቅ።
11ለሰው እንደ ሥራው ይከፍለዋልና፤ እያንዳንዱም በየራሱ መንገድ ወደ ብድራቱ እንዲመጣ ያደርገዋል።
12በእርግጥ እግዚአብሔር አንዳችም አመጻን አያደርግም፥ ደግሞም ሁሉን ቻዩ ከቶም ፍትሕን አያዛባም።
13በምድር ላይ እርሱን ፈራጅ ያደረገው ማነው? ዓለሙንስ በሙሉ ከእርሱ በታች ያደረገው ማነው?
14እርሱ ፍላጎቱን በራሱ ላይ ብቻ ቢያደርግና መንፈሱንና እስትንፋሱን ወደ ራሱ ቢመልስ ኖሮ
15ያን ጊዜ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በጠፋ፥ ሰውም እንደገና ወደ ዐፈር በተመለሰ ነበር።
16አሁን እንግዲህ ማስተዋል ካለህ ይህንን ስማ፤ የቃሌንም ድምፅ አድምጥ።
17ፍትሕን የሚጠላ ማስተዳደር ይችላል? ጻድቅና ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ትኮንነዋለህ?
18እግዚአብሔር ንጉሡን፥ 'በደለኛ ነህ' ወይም ባለስልጣኖችን፥ 'አመጸኞች ናችሁ' አይልምን?
19እግዚአብሔር ለመሪዎች አያዳላም፤ ባለጸጋዎችንም ከድኾች አስበልጦ አይመለከታቸውም፤ ሁሉም የእጁ ሥራዎች ናቸውና።
20በቅጽበት ይሞታሉ፤ እኩለ ሌሊት ላይ ሰዎች ይንቀጠቀጣሉ፥ ይሞታሉም፤ ኃያላን ሰዎች ይወሰዳሉ፥ በሰው እጅ ግን አይደለም።
21የእግዚአብሔር ዐይኖች በሰው አካሄድ ላይ ናቸው፤ እርምጃዎቹንም ሁሉ ያያቸዋል።
22ክፉ አድራጊዎች የሚደበቁበት ጨለማ ወይም ድቅድቅ ጭጋግ የለም።
23እግዚአብሔር ከዚህ በላይ ሰውን መመርመር አይፈልግም፥ የትኛውም ሰው በእርሱ ፊት ቆሞ መሟገት አያስፈልገውም።
24ስለ አካሄዳቸው ተጨማሪ ምርመራ እንዳያስፈልጋቸው ኃያላኑን ሰዎች ይሰባብራቸዋል፤ በስፍራቸውም ሌሎችን ይሾማል።
25እንዲህ ባለ መንገድ ሥራቸውን ያውቃል፤ እነዚህን ሰዎች በጨለማ ይጥላቸዋል፤ እነርሱም ይጠፋሉ።
26በሌሎች ፊት፥ በአደባባይ ስለ ክፉ ሥራቸው እንደ ወንጀለኛ ይገድላቸዋል፥
27እርሱን ከመከተል ተመልሰዋልና፥ ከመንገዶቹም የትኛውንም ለመቀበል ፈቃደኞች አልሆኑምና።
28እንዲህ ባለ መንገድ የድኾች ጩኸት በፊቱ እንዲወጣ አደረጉ፤ እርሱም የተጨነቁትን ሰዎች ጩኸት ሰማ።
29በዝምታ በሚቆይበት ጊዜ ማን ሊወቅሰው ይችላል? ፊቱንስ ቢሰውር ማን ሊገነዘበው ይችላል?
30አመጸኛው ሰው ገዢ እንዳይሆን፥ በሕዝቡም ላይ ወጥመድን የሚያደርግ እንዳይገኝ እርሱ በሀገሮችና በግለሰቦች ላይ ይገዛል።
31አንድ ሰው እግዚአብሔርን እንዲህ እንደሚለው ገምቱ፥ 'በርግጥ በድያለሁ፥
32ከዚህ በኋላ ግን ከቶ ኃጢአትን አላደርግም፤ ላየው የማልችለውን አስተምረኝ፤ ኃጢአትን ሠርቻለሁ፥ ከእንግዲህ ግን አላደርግም'።
33እግዚአብሔር የሚያደርገውን የምትጠላ ሰው ብትሆንም፥ እግዚአብሔር የዚያን ሰው ኃጢአት የሚቀጣ ይመስልሃል? እኔ ሳልሆን አንተው መምረጥ አለብህ። ስለዚህ ትክክል ነው ብለህ የምታውቀውን ተናገር።
34ዐዋቂዎች ሰዎችም እንዲህ ይሉኛል፥ በእርግጥ የሚሰማኝ ጥበበኛ ሰው ሁሉ የሚለው እንዲህ ነው፥
35'ኢዮብ የሚናገረው የማያውቀውን ነው፤ ቃሎቹም ጥበብ የለባቸውም'።
36እንደ አመጸኞች ሰዎች ተናግሯልና ምነው ኢዮብ ብቻውን ከጉዳዮቹ ስለ ጥቂቶቹ በዝርዝር በተመረመረ።
37በኃጢአቱ ላይ አመጽን ጨምሯልና፤ በመካከላችን እጆቹን እያጨበጨበ ተሳድቧልና፤ እግዚአብሔርን በመቃወምም ብዙ ቃል ተናግሯል።"