1አሁንም ኢዮብ ሆይ፥ ቃሎቼን እንድትሰማ፥ ንግግሬንም እንድታደምጥ እለምንሃለሁ።
2ይኸው አሁን አፌን ከፍቻለሁ፤ ምላሴም በአፌ ውስጥ ተናግሯል።
3ቃሎቼ የልቤን ቅንነት ይናገራሉ፤ ከንፈሮቼ የሚያውቁትን በታማኝነት ይናገራሉ።
4የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ፤ የሁሉን ቻዩ እስትንፋስ ሕይወትን ሰጠኝ።
5ከቻልክ መልስልኝ፤ በፊቴም ቃሎችህን በቅደም ተከተል አዘጋጅና ቁም።
6ተመልከት፥ በእግዚአብሔር ፊት አንተ እንደሆንከው እንዲሁም እኔም ነኝ፤ እኔም ደግሞ ከጭቃ ተሠርቻለሁ።
7ተመልከት፥ ማስፈራራቴ አያስፈራህም፤ ተጽዕኖዬም ቢሆን አይከብድብህም።
8በእርግጥ በጆሮዬ ተናግረሃል፤ እንዲህ የሚለውንም የቃልህን ድምፅ ሰምቻለሁ፥
9ንጹሕ ነኝ መተላለፍም የለብኝም፤ አልበደልኩም፥ ኃጢአትም የለብኝም።
10ይኸው፥ እግዚአብሔር ሊያጠቃኝ አጋጣሚ ይፈልጋል፤ እንደ ጠላቱ አድርጎ ይቆጥረኛል።
11እግሮቼን በግንድ ውስጥ ያስገባቸዋል፤ መንገዶቼንም ሁሉ ይመለከታል።
12እግዚአብሔር ከሰው ይበልጣልና እንደዚህ መናገርህ ትክክል አይደለም ብዬ እመልስልሃለሁ።
13ለየትኛውም ሥራው ትኩረት አይሰጠውም በማለት ከእርሱ ጋር ለምን ትታገላለህ?
14ሰው ባያስተውለውም እግዚአብሔር አንድ ጊዜ፥ አዎን፥ ሁለት ጊዜ ይናገራል።
15ሰዎች አልጋቸው ላይ ተኝተው ከባድ እንቅልፍ በሚወድቅባቸው ጊዜ በህልም፥ በሌሊት ራዕይ ይናገራቸዋል።
16በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር የሰዎችን ጆሮ ይከፍትና በማስጠንቀቂያው ያስፈራራቸዋል፤
17ይህንን የሚያደርገውም ሰውን ከኃጢአታዊ ዓላማው ሊመልሰውና ከትዕቢት ሊጠብቀው ነው።
18እግዚአብሔር የሰውን ሕይወት ከጉድጓድ ይጠብቃል፥ ሕይወቱንም ወደ ሞት ከመውረድ።
19ደግሞም ሰው በአልጋው ላይ በሕመም ይቀጣል፥ በአጥንቶቹም ውስጥ በማያቋርጥ ስቃይ፤
20ሕይወቱ ምግብን፥ ነፍሱም ጣፋጩን መብል እስክትጠላ ድረስ።
21ሥጋው ሊታይ እስከማይችል ድረስ ጠፍቷል፥ የማይታዩ የነበሩት አጥንቶቹም አሁን ገጠው ወጥተዋል።
22በርግጥ ነፍሱ ወደ ጉድጓድ ቀርባለች፥ ሕይወቱም ሊያጠፏት ወደሚፈልጉት።
23ነገር ግን መካከለኛ ሊሆንለት የሚችል አንድ መልአክ ቢኖር፥ የትኛውን መልካም ነገር ማድረግ እንዳለበት የሚያሳየው፥ መካከለኛ የሚሆንለት ከሺህ መላእክት አንድ ቢገኝለት፥
24መልአኩም ለእርሱ ደግ ቢሆንና እግዚአብሔርን፥ 'ቤዛ የሚሆንለት አግኝቻለሁና ይህንን ሰው ወደ ጉድጓድ ከመውረድ አድነው' ቢለው
25በዚያን ጊዜ ሥጋው ከሕፃን ገላ ይልቅ ይታደሳል፤ ወደ ወጣትነት የብርታቱ ዘመንም ይመለሳል።
26እርሱ ወደ እግዚአብሔር ይጸልያል፥ እግዚአብሔርም ይራራለታል፥ እርሱም የእግዚአብሔርን ፊት በደስታ ያያል። እግዚአብሔርም ለሰውየው ድልን ይሰጠዋል።
27ከዚያም ያ ሰው በሌሎች ሰዎች ፊት እንዲህ ሲል ይዘምራል፥ 'ኃጢአትን ሠርቻለሁ፥ ትክክለኛ የሆነውንም አጣምሜአለሁ፥ ይሁን እንጂ ስለኃጢአቴ አልተቀጣሁም።
28እግዚአብሔር ነፍሴን ወደ ጉድጓድ ከመውረድ አዳናት፤ ሕይወቴም ብርሃን ማየቷን ትቀጥላለች"።
29ተመልከቱ፥ እግዚአብሔር እነዚህን ነገሮች ሁሉ በሰው ሕይወት ሁለት ጊዜ፥ አዎን፥ እንዲያውም ሦስት ጊዜ ያደርጋቸዋል፤
30ይኸውም የሕይወት ብርሃን ይበራለት ዘንድ ነፍሱን ከጉድጓድ ለመመለስ ነው።
31ኢዮብ ሆይ አስተውለህ ስማኝ፤ ዝም በል፥ እኔም እናገራለሁ።
32የምትናገረው ነገር ካለህ መልስልኝ፤ ትክክለኛ መሆንህን ለማረጋገጥ እፈልጋለሁና ተናገር።
33ካልሆነ ግን ጸጥ ብለህ ስማኝ፤ እኔም ጥበብን አስተምርሃለሁ“።