መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኢዮብ 31

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ስለገባሁ፤ እንዴት ድንግሊቱን በምኞት እመለከታለሁ?
2ከላይ ከእግዚአብሔር የሆነው እድል ፈንታ ፥ ሁሉንም የሚችል አምላክስ ርስት ከአርያም ምንድን ነው?
3መዓት ለኃጢአተኛ፥ ጥፋትም ክፋትን ለሚያደርጉ ነው ብዬ አስብ ነበር።
4እግዚአብሔር መንገዴን አያይምን? እርምጃዬንስ ሁሉ አይቈጥርምን?
5በሐሰት ሄጄ እንደ ሆነ እግሬም ለሽንገላ ቸኵሎ እንደ ሆነ፥
6በእውነተኛ ሚዛን ልመዘን፥ እግዚአብሔርም ትክክለኛቴን ይወቅ።
7እርምጃዬ ከትክክለኛው መንገድ ፈቀቅ ብሎ፥ ልቤም የዓይኔን ምኞት ተከትሎ፥ ነውርም በእጄ ላይ ተጣብቆ እንደ ሆነ፥
8እኔ ልዝራ፥ ሌላ ሰውም ይብላው፤ መከሩም ከእርሻዬ ላይ ይነቀል።
9ልቤ ወደ ሌላይቱ ሴት ጐምጅቶ እንደ ሆነ፥ የጎረቤቴን ሚስት ለማየት ደጃፉ አድብቼ እንደ ሆነ፥
10ሚስቴ ለሌላ ሰው እህል ታዘጋጅ፥ ሌሎችም ከእርስዋ ጋር ይተኙ።
11ይህ ክፉ ወንጀል ነውና፥ በፈራጆችም ሊቀጣ የሚገባው በደል ነውና፤
12ይህ እስከ ሲኦል ድረስ የሚበላ እሳት፥ ያመረትኩትን ሁሉ የሚያቃጥል ነውና።
13ወንድ ወይም ሴት ባሪያዎቼ ከእኔ ጋር በተምዋገቱ ጊዜ፥ ሙግታቸውን በትክክል ሳላይ ቀርቼ እንደ ሆነ፥
14እግዚአብሔር ሊከሰኝ በተነሣ ጊዜ ምን አደርጋለሁ? ሊፈርደኝም በመጣ ጊዜ እንዴት እመልስለታለሁ?
15እኔን በማኅፀን የሰራኝ እነርሱንስ የፈጠረ አይደለምን? በማኅፀንስ ውስጥ ሁላችንን የሠራን አንድ አይደለምን?
16ድሀዎችን ከፍላጎታቸው ከልክዬ፥ የመበለቲቱንም ዓይን በለቅሶ አጨልሜ እንደ ሆነ፥
17እንጀራዬን ለብቻዬ በልቼ እንደ ሆነ፥ አባት የሌላቸውንም ከእርሱ እንዳይበሉ ከልክዬ እንደ ሆነ፤
18ይልቁን እርሱ ከታናሽነቴ ጀምሬ እንደ አባቱ ሆኜ ከእኔ ጋር አሳድጌው ነበር፥ እናቱንም ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ መራኋት፤
19አንድ ሰው የሚለብሰው አጥቶ ሲጠፋ፥ ወይም ድሀ ያለ ልብስ ሲሆን እንዲያው አይቼ እንደ ሆነ፥
20በበጎቼም ጠጕር ያልሞቀና፥ በልቡ ያልባረከኝ እንደ ሆነ፤
21በከተማው በር ረዳት ስላለኝ፥ አባት በሌላቸው ላይ እጄን አንሥቼ እንደ ሆነ፥
22ትከሻዬ ከመጋጠሚያው ይውደቅ፥ ክንዴም ከመገናኛው ይሰበር።
23ከእግዚአብሔር የሆነ ቁጣ ለእኔ አስደንጋጭ ነውና ከግርማውም የተነሳ እነዚህን ነገሮች ማድረግ አልችልም።
24ወርቅን ተስፋዬ አድርጌ፥ ጥሩውንም ወርቅ”በአንተ እታመናለሁ“ ብዬ እንደ ሆነ፤
25ሀብቴ ስለ በዛ፥ እጄም ብዙ ስላከማቸ ደስ ብሎኝ እንደ ሆነ፤
26ፀሐይ ሲበራ ተመልክቼ፥ ጨረቃ በድምቀት ስትሄድ አይቼ፥
27ልቤ እነርሱን ለማምለክ በስውር ተስቦ፥ አፌም እጄን ስሞ እንደ ሆነ፤
28በላይ ያለውን እግዚአብሔርን መካድ ነውና ይህም ዳኞች ሊቀጡት የሚገባ ወንጀል በሆነ ነበር።
29በሚጠላኝ በማንም መጥፋት ደስ ብሎኝ ወይም ክፉ ነገር በሆነበት ጊዜ ራሴን አስደስቼው እንደ ሆነ፤
30ለነፍሱ እርግማንን በመናገር፥ አንደበቴ ኃጢአት እንዲሰራ በርግጥ አልፈቀድኩለትም፤
31በድንኳኔ የሚኖሩ ሰዎች፦ “ከኢዪብ ማዕድ ያልጠገበ ማን ይገኛል?” ብለው ካልተናገሩ፤
32መጻተኛው በከተማ ጎዳና እንዳያድርም፥ ሁልጊዜ ደጄን ለመንገደኛ እከፍት ነበር፤
33በደሌንም በብብቴ በመሸሸግ ኃጢአቴን እንደ ሰዉ ሁሉ ደብቄ እንደ ሆነ፤
34የሕዝብን ብዛት ከመፍራቴ የተነሳ፥ የዘመዶቼም ንቀት አስደንግጦኝ፥ ዝም ብዬ ከቤቴ ሳልወጣ ቀርቼ እንደ ሆነ፤
35ኦ የሚያዳምጠኝ አንድ ሰው ምነው በኖረኝ! ይኸው የእጄ ፊርማ ምልክት፤ ሁሉን የሚችል አምላክ ይመልስልኝ! ባላጋራዬ የጻፈው የክስ ጽሑፍ ምነው በተገኘልኝ!
36በግልጽ ትከሻዬ ላይ አድርጌ እሸከመው ነበር፥ እንደ አክሊልም ራሴ ላይ አስቀምጠው ነበር።
37የእርምጃዎቼን ቍጥር በግልጽ አስታውቀው፥ እንደ ተማመነ አለቃም ፊትለፊቱ እወጣ ነበር።
38የእርሻዬ መሬት በእኔ ላይ ጮሆ እንደ ሆነ፥ ትልሞቹም አብረው አልቅሰው እንደ ሆነ፤
39የምርቱን ዋጋ ሳልከፍል በልቼ፥ የባለቤቶቹንም ነፍስ አሳዝኜ እንደ ሆነ፥
40በስንዴ ፋንታ እሾኸ፥ በገብስም ፋንታ አረም ይብቀልበት።“ የኢዮብም ንግግር ተፈጸመ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።