1ኢዮብም መናገሩን ቀጠለ፥ እንዲህም አለ፦
2እግዚአብሔር ይጠብቀኝ እንደ ነበረው ጊዜ፥ እንዳለፉት ወራት ምነው በሆንሁ!
3መብራቱ በራሴ ላይ እንደበራበት ወቅት፥ በጨለማ ውስጥ በብርሃኑ አልፌ እንደሄድሁበት ጊዜ፥
4ቀኖቼ ወደ ሙላታቸው በደረሱ ጊዜ፥ የእግዚአብሔር ወዳጅነት በድንኳኔ በነበረ ጊዜ፥
5ሁሉን የሚችል አምላክ ገና ከእኔ ጋር በነበረ ጊዜ፥ ልጆቼም በዙሪያዬ እያሉ፥
6መንገዴ በቅቤ ይታጠብ በነበረ ጊዜ፥ ድንጋዩ የዘይት ፈሳሽ ያፈስስልኝ በነበረ ጊዜ።
7ወደ ከተማው በር በወጣሁ ጊዜ፥ በአደባባዩ መሃል ወንበሬ ላይ በተቀመጥሁ ጊዜ፥
8ወጣቶች አይተው በአክብሮት ገለል አሉ፥ ሽማግሌዎችም ተነሥተው ቆሙ።
9በመጣሁ ጊዜ ልኡላን ከመናገር ይቆጠባሉ፥ እጃቸውንም በአፋቸው ላይ ይጭኑ ነበር።
10የብልሆች ድምፅ ጸጥ ይል፤ ምላሳቸውም በላንቃቸው ተጣበቀች።
11በጆሮአቸው ከሰሙኝ በኋላ ይባርኩኝ ነበር፥` በአይናቸው ዓይተው ያሞግሱኝና ይመሰክሩልኝ ነበር፤
12ምክንያቱም የሚጮኸውን ችግረኛ፥ ድሀ አደጉንና ረዳት የሌላቸውን አድን ነበረና።
13ሊጠፋ የቀረበ በረከት ወደ እኔ ይመጣል፤ ባል የሞተባትንም ሴት ልብ በደስታ እንድትዘምር አደርግ ነበርና።
14ጽድቅን ለበስሁ እርስዋም ለበሰችኝ፤ ፍትሃዊነቴም እንደ መጐናጸፊያዬና ጥምጣሜ ነበረ።
15ለአይነ ስውራን ዓይናቸው፥ መራመድ ለማይችሉም ሰዎች እግር ነበርሁ።
16ለችግረኞች አባት ነበርሁ፤ የማላውቀውንም ሰው ሙግት እመረምር ነበር።
17የኃጢአተኛውን መንጋጋ ሰበርሁ፥ የያዘውንም ከጥርሱ ውስጥ አስጣልሁ።
18እንዲህም አልሁ፦ “በጎጆዬ ሆኜ እሞታለሁ፥ ቀኖቼን እንደ አሸዋ አበዛለሁ፤
19ሥሮቼ ወደ ውኃ ይሰራጫሉ፥ ጠልም ምሽቱን ሁሉ በቅርንጫፎቼ ላይ ያድራል፤
20በእኔ ዘንድ ያለው ክብር ሁልጊዜ ትኩስ ነው፥ በእጄ ያለው የብርታቴ ቀስት አዲስ ነው።
21ሰዎች እኔን ለመስማት በትዕግሥት ተጠባበቁ፥ ምክሬንም ለማዳመጥ በጸጥታ ተቀመጡ።
22ንግግሬንም ከጨረስኩ በኋላ መልሰው አልተናገሩም፤ ቃሎቼም በላያቸው እንደ ውሃ ተንጠባጠበ።
23ዝናብን እንደሚጠብቁ ሁልጊዜ ይጠብቁኛል፤ የበልግ ዝናብን እንደሚሹት፥ ከቃሎቼ ለመጠጣት አፋቸውን ከፈቱ ።
24እነርሱ ባልጠበቁተ ጊዜ ሳቅሁላቸው፤ የፊቴንም ብርሃን ቸል አላሉትም።
25መንገድን እመርጥላቸውና አለቃቸው ሆኜ እቀመጣለሁ፤ ኅዘነተኞችን በቀብር ጊዜ እንደሚያጽናና ሰው፥ በሠራዊቱም መካከል እንዳለ ንጉሥ በመካከላቸው ኖርሁ።