1በእርግጥ ብር የሚወጣበት፥ ወርቅም የሚነጠርበት ስፍራ አለ።
2ብረት ከመሬት ውስጥ ይወሰዳል፥ መዳብም ከድንጋይ ቀልጦ ይወጣል።
3ሰው የጨለማ መጨረሻ ድረስ ይወርዳል፤ በጨለማና ባስፈሪ ስፍራ ውድ ድንጋይ ይፈላልጋል።
4ሰው ከሚኖርበት ርቆ መውረጃ ይቈፍራሉ፤ ከሁሉ እግር በተረሳ ስፍራ፥ ከሰዎችም ሩቅ ሆኖ እየተንጠላጠለ ይወዛወዛል።
5ከምድር እንጀራ ቢገኝም፤ ከታችኛው ክፍል ግን እሳት ይገላበጣል።
6ድንጋይዋ ሰንፔር የሚገኝበት ስፍራ ነው፥ አፈሯም ወርቅን ይዟል።
7ያን መንገድ ጭልፊት አያውቀውም፥ የአሞራም ዓይን አላየውም።
8ኲሩ እንስሶች ይህን መንገድ አልሄዱበትም፥ አስፈሪው አንበሳም በዚያ አላለፈም።
9ሰው ቡላድ ድንጋይ ላይ እጁን ይጭናል፥ ተራራዎችንም ከሥራቸው ይገለብጣል።
10በድንጋይ ውስጥ መንዶልዶያን ፈልፍሎ ይሰራል፤ በዚያም ዓይኑ የከበሩ ነገሮችን ሁሉ ያያል።
11ፈሳሹም እንዳያልፉ ይገድባል፤ በዚያም የተሰወሩትን ወደ ብርሃን ያወጣቸዋል።
12ጥበብ ግን የት ትገኛለች? የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው?
13ሰው ዋጋዋን አላወቀም በሕያዋንም ምድር አትገኝም።
14ከምድር ጥልቅ ያለ ውሃ፦ "በእኔ ውስጥ የለችም' አለ፤ ባሕርም፦ "እኔ ጋር የለችም" አለ።
15ወርቅ ሊገዛት አይችልም፥ ዋጋዋም በብር አይመዘንም።
16በኦፊር ወርቅ፥ በከበረም መረግድና በሰንፔር አትገመትም።
17ወርቅና ብርሌ አይተካከሉአትም፥ በነጠረ ወርቅ ጌጥም አትለወጥም።
18ዛጐልና አልማዝ ከቁጥር አይገቡም። በርግጥ የጥበብ ዋጋ ከቀይ ዕንቍ ይበልጣል።
19የኢትዮጵያ ቶጳዝዮን አይስተካከላትም፥ በንጹህ ወርቅም አትገመትም።
20ታዲያ ጥበብ ከወዴት ትመጣለች? የማስተዋልስ ስፍራ የት ነው?
21ጥበብ ሕይወት ካላቸው ነገሮች ሁሉ ዓይን ተሰውራለች፥ ከሰማይ ወፎችም ተሸሽጋለች።
22ጥፋትና ሞት፦ “ወሬዋን ብቻ በጆሮቻችን ሰምተናል” አሉ።
23እግዚአብሔር ወደ እርሷ የሚወስደውን መንገድ ያስተውላል፥ስፍራዋንም ያውቃል።
24ምክንያቱም እርሱ የምድርን ዳርቻ፥ ከሰማይም በታች ያለውን ሁሉ ያያል።
25እርሱ አስቀድሞ ለነፋስ ሃይል መጠንን አደረገ፥ ውኆችንም በስፍር ሰፈረ፥
26እርሱ ለዝናብ ሥርዓትን፥ ለነጐድጓድ መብረቅም መንገድን አደረገ፥
27በዚያን ጊዜ ጥበብን አያት፥ ገለጣትም አጸናት፥ በርግጥም መረመራት።
28ለሰዎችም፦ እነሆ፥ “እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ ከክፋትም መራቅ ማስተዋል ነው” አለ።