1ሁሉን ከሚችል አምላክ ሃጢያተኛ የሚፈረድበት ጊዜ ለምን አልተወሰነም? ለእርሱስ ታማኝ የሆኑት የፍርዱ ቀን እንደመጣ ለምን አያዩም?
2የድንበር ምልክትን የሚያፈርሱ ኅጢያተኛ ሰዎች አሉ፤ የሌሎችን መንጋ በግፍ ወስደው የሚያሰማሩ አመጸኞች አሉ።
3የድሀ አደጎችን አህያ ቀምተው ይነዳሉ ፤ የመበለቲቱንም በሬ በመያዣ ይወስዳሉ።
4ድሆችን ከመንገዳቸው ያስወጣሉ፤ የምድርም ችግረኞች ሁሉ ከእነርሱ ይሸሸጋሉ።
5እነዚህ ችግረኞች፥ በምድረ በዳ እንዳሉ የሜዳ አህዮች ወደ ስራቸው ይወጣሉ፥ ምግብን ፍለጋ በጥንቃቄ ይሄዳሉ፤ ምንአልባት ምድረ በዳው ለልጆቻቸው መብልን ይሰጣቸዋል።
6ድሆቹም በሌሎች ሰዎች በእርሻ ውስጥ በምሽት ያጭዳሉ፤ ከበደለኞችም መከር ወይንን ይቃርማሉ።
7ራቁታቸውን ያለ ልብስ ምሽቱን ሁሉ ይተኛሉ፥ በብርድም ጊዜ መጐናጸፊያ የላቸውም።
8ከተራሮች በሚወርድ ዝናብ ይረጥባሉ፤ መጠለያም ስለሌላቸው ከቋጥኝ ስር ይጋደማሉ።
9ድሀ አደጉን ህጻን ከእናቱ ጡት የሚነጥሉ ኅጢያተኞች አሉ፤ በደለኞችም ልጆችን በመያዣነት ይወስዳሉ።
10ነገር ግን ድሃዎቹ ያለ ልብስ ራቁታቸውን ይሄዳሉ፤ ተርበውም ቢሆን የሌሎችን እህል ነዶ ይሸከማሉ፤
11ድሃ ሰዎች በኁጢኣን አጥር ውስጥ ዘይት ይሰራሉ፤ ወይንም ይጠምቃሉ፥ ነገር ግን እነርሱ በጥም ይሰቃያሉ።
12በከተማ ውስጥ ሰዎች ያቃስታሉ ፤ የቆሰሉም ለእርዳታ ይጮኻሉ፤ እግዚአብሔር ግን ልመናቸውን አይመለከትም።
13እነዚህ ኅጢያተኞች በብርሃን ላይ ያምጻሉ፤ መንገዱን አያውቁም፥ በጎዳናውም አይጸኑም።
14ነፍሰ ገዳዩም ማልዶ ይነሣል፤ ችግረኞችንና ድሆችን ይገድላል፤ በሌሊትም እንደ ሌባ ነው።
15የአመንዝራም ዓይን ድግዝግዝታን ይጠብቃል። "የማንም ዓይን አያየኝም" ይላል፥ ፊቱንም እንደሌላ ይለውጣል።
16አመጸኞች ቤቶችን በጨለማ ይሰረስራሉ፤ በቀን ግን ይሸሸጋሉ፤ ለብርሃንም ግድ የላቸውም።
17ለእነርሱ ጥዋት እንደ ድቅድቅ ጨለማ ነውና፤ ከድቅድቅ ጨለማ ሽብር ጋርም ተወዳጅተዋል።
18ይሁን እንጂ በውኃ ላይ እንዳለ አረፋ በርረው ይጠፋሉ፤ የርስት እድል ፈንታቸውም የተረገመ ነው፤ በወይን ቦታቸውም ላይ ለመስራት ማንም አይሄድም።
19ድርቅና ሙቀት በረዶውን እንደሚያቀልጥ፤ እንዲሁ ሲኦል ሃጢያተኞችን ታጠፋለች።
20የተሸከመችው ማኅፀን ትረሳዋለች፤ ትልም በደስታ ይበላዋል፤ ዳግመኛም አይታሰብም፤ በዚህ ሁኔታ ዓመጸኝነት እንደ ዛፍ ይሰበራል።
21የማትወልደውን መካኒቱን ሃጥያተኛው ይጎዳታል፤ ለመበለቲቱም ምንም አይነት በጎነት አያደርግም።
22ነገር ግን እግዚአብሔር በኃይሉ ኃያላንን ጎትቶ ይጥላል፤ እርሱም ይቆማል በሕይወቱ ግን አይጠነክርም።
23እግዚአብሔር በደኅንነት እንዳሉ እንዲያስቡ ይፈቅዳል፥ በዚያም ደስ ይላቸዋል፤ ነገር ግን ዓይኖቹ በመንገዳቸው ላይ ናቸው።
24እነዚህ ሰዎች ለጥቂት ጊዜ ከፍ ከፍ ይላሉ፤ በርግጥ ግን፥ ይዋረዳሉ፤ እንደ ሌሎች ሁሉ ተሰብስበው፤ እንደ እሸት ራስ ጫፍ ይቈረጣሉ።
25እንደዚህስ ባይሆን ሐሰተኛ የሚያደርገኝ፥ ንግግሬንም ከንቱ የሚያደርግ ማን ነው?