1ኢዮብም ሲመልስ እንዲህ አለ፦
2ዛሬም ቢሆን የኅዘን አቤቱታዬ መራራ ነው፤ መከራዬም ማቃሰት ከምችለው በላይ ይከብዳል።
3ኦ! እርሱን ወዴት እንደማገኘው ምነው ባውቅ! እርሱ ወዳለበት ስፍራ በሔድሁ!
4ጉዳዬን በፊቱ በተገቢ ሁኔታ ባቀረብሁ፥ አፌንም ለሙግት ሞልቼ አዘጋጅ ነበር።
5የሚመልስልኝን ቃሎች አውቅ ነበር፥ የሚለኝንም በተረዳሁ ነበር።
6በኃይሉ ብዛት ከእኔ ጋር ይምዋገት ነበርን? እንኳን! ያደምጠኝ ነበር።
7ጻድቅ ሰው ከእርሱ ጋር በዚያ ይዋቀሳል፤ እንደዚህም በዳኛዬ በእርሱ ለዘላለም ነጻ እወጣ ነበር።
8ነገር ግን፥ ወደ ምስራቅ ብሄድ፥ በዚያ የለም፤ ወደ ምዕራብም ብሔድ ላየው አልቻልኩም፤
9ወደሚሠራበት ወደ ሰሜን ብሄድ አላየሁትም፤ ራሱን ወደሚሰውርበት በደቡብም፥ላየው አልቻልኩም፤
10ነገር ግን የምሄድበትን መንገድ ያውቃል፤ ከፈተነኝም በኋላ እንደ ወርቅ እወጣለሁ።
11እግሮቼ እርምጃውን በጽናት ተከተሉ፤ ውልፍት ሳልል መንገዱን ጠብቄአለሁ።
12ከከንፈሩም ትእዛዝ አላፈገፈግሁም፤ የአፉን ቃል በልቤ ሰውሬአለሁ።
13እርሱ ግን በአይነቱ ብቸኛ ነው፤ እርሱንስ ማን ሊመልሰው ይችላል? እርሱ የወደደውን ነገር ያደርጋል።
14በእኔ ላይ የተወሰነብኝን ይፈጽማል፤ እንደነዚህም አይነት ብዙ አለ።
15ስለዚህ በእርሱ ፊት ደነገጥሁ፤ ስለእርሱም ባሰብሁ ጊዜ እፈራዋለሁ።
16እግዚአብሔር ልቤን አድክሞታል፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ አስደንግጦኛል።
17እንጂ ጨለማ ወይም ድቅድቁ ጨለማ ፊቴን ከመክደኑ የተነሣ አልጠፋሁም።