1መንፈሴ ተጨረሰ፥ ቀኖቼም አለቁ፥ መቃብርም ተዘጋጅቶልኛል።
2በርግጥ አላጋጮች ከእኔ ጋር አሉ፥ ዓይኔም ይህን ማላገጣቸውን ሁልጊዜ ያያል።
3አሁንም መያዣን ለራስህ ሰጥተህ ዋስ ሁነኝ፤ ከአንተ ሌላ የሚረዳኝ ማን አለ?
4እግዚአብሔር አንተ ልባቸው እንዳያስተውል አድርገሃል፤ በላዬም ከፍ እንዲሉ አታደርጋቸውም።
5ለጥቅም ብሎ ጓደኞቹን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው፥ የልጆቹ ዓይን ይታወራል።
6ነገር ግን እርሱ ለሰዎች መተረቻ አደረገኝ፤ በፊቴም ላይ ተፉብኝ።
7ዓይኔ ከኀዘን የተነሣ ፈዘዘ፥ የሰውነቴ ክፍሎች በሙሉ እንደ ጥላ ቀጠኑ።
8ጻድቅ ሰዎችም በዚህ ነገር ይደነቃሉ፥ ንጹሑም ሰው በዐመጸኞች ላይ ይበሳጫል።
9ጻድቅ ግን መንገዱን ያጸናል፥ ንጹሕ እጆች ያሉትም ሰው ብርታትን እየጨመረ ይሄዳል።
10እናንተ ሁላችሁ ግን እስቲ ወደ እኔ ኑ፤ ከመካከላችሁ አንድም ጠቢብ አላገኝም።
11ቀኖቼ አለቁ፤ እቅዶቼ አበቃላቸው፥የልቤም ምኞት ሳይቀር ከንቱ ሆነ።
12እነዚህ አሿፊ ሰዎች ሌሊቱን ወደ ቀን ይለውጣሉ፤ ብርሃንም የሚሉተ ወደ ጨለማ የቀረበውን ነው።
13ሲኦልን እንደ ቤቴ ካየሁ፤ መቀመጫዬንም በጨለማ ከዘረጋሁ፤
14ለጉድጓድም፦ “አንተ አባቴ ነህ” ፤ ለትልም፦ “አንቺ እናቴ እኅቴም ነሽ” ብዬ ካልሁ።
15ታዲያ ተስፋዬ ወዴት ነው? ተስፋዬንስ የሚያይልኝ ማን ነው?
16ተስፋስ ወደ አፈር ስንወርድ፥ አብሮኝ ወደ ሲኦል ይወርዳልን?