1ቀጥሎም ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ እንዲህም አለ፦
2በውኑ ጠቢብ ሰው ከንቱ በሆነ እውቀት ይመልሳልን? ራሱንስ በምሥራቅ ነፋስ ይሞላልን?
3ትርፍ በሌለው ወሬ ወይም በማይጠቅም ንግግር ይሟገታልን?
4በእርግጥ አንተ የእግዚአብሔርን አክብሮት ታሳንሳለህ፤ ለእግዚአብሔር ያለህን መሰጠት ታስቀራለህ።
5ሃጢያትህ አፍህን ያስተምረዋል፥ የተንኰለኛ አንደበት ቢኖርህ ትመርጣለህ።
6የሚፈርድብህ የራስህ አፍ እንጂ እኔ አይደለሁም፤ በርግጥም የራስህ ከንፈሮች ይመሰክሩብሃል።
7ከተወለዱት ሁሉ አንተ የመጀመሪያ ሰው ነህን? ወይስ ከኮረብቶች በፊት አንተ ነበርህ?
8የእግዚአብሔርን ምሥጢራዊ እውቀት ሰምተሃልን? ጥበብንስ ለራስህ ብቻ ገደብሃትን?
9እኛ የማናውቀው አንተ የምታውቀው ምንድር ነው? በእኛ ዘንድ የሌለ አንተ ብቻ የተረዳኸው ምን አለ?
10ከአባትህ በዕድሜ የሚበልጡ ሽበትም ያላቸው ሽማግሌዎችም ከእኛ ጋር አሉ።
11በውኑ የእግዚአብሔር ማጽናናት፥ በየውሃነት የቀረበልህ ቃልስ ጥቂት ሆነብህን?
12የነፍስህ ስሜት ለምን ይወስድሃል? ዓይኖችህስ ለምን በቁጣ ያፈጣሉ?
13መንፈስህ በእግዚአብሔር ላይ ተነስቷል፤ እንዲህ ያለ ቃል ከአፍህ እስከ ማውጣት ደረስህ።
14ንጹሕ ሆኖ ሊገኝ ሰው ማን ነው? ጻድቅ ሊሆን ከሴት የተወለደ እርሱ ማን ነው?
15እነሆ እግዚአብሄር በቅዱሳኑ እንኳ አይታመንም፤ በእርግጥ ሰማያትም በእርሱ አይን ንጹሕ አይደሉም።
16ይልቁንስ ኃጢአትን እንደ ውኃ የሚጠጣ ፥ አመጸኛና የተበላሸው የሰው ልጅ ምንኛ ያንስ?
17ስማኝ፥አሳይሃለሁ፤ያየሁትንም አሳውቅሃለሁ፤ በመካከላቸውም እንግዳ ያልገባባቸው ጠቢባን
18ጠቢባን ከአባቶቻቸው ተቀብለው ያስተላለፉትን ፤ የእነርሱ ቀደምት ትውልድ ያልሸሸጉትን ነገር እገልጥልሃለሁ።
19ለአባቶቻቸውም ፥ ምድሪቱ ለእነርሱ ብቻ ተሰጥታ ነበረ፥ በመካከላቸው እንግዶች አልፈው አያውቁም
20ክፉ ሰው ዕድሜውን ሙሉ በሕመም ይሰቃያል፥ ግፈኛም በፊቱ ያሉት ዓመታት ለስቃይ ይሆኑበታል።
21የሽብር ድምፅ በጆሮው ውስጥ ነው፤ በብልጽግናው እያለ አጥፊው ይመጣበታል።
22ከጨለማ ተመልሶ እንደሚወጣ አያስብም፥ ሰይፍም አሸምቆ ይጠብቀዋል።
23ወዴት አለ? እያለ እንጀራ ፍለጋ ብዙ ስፍራ ይዞራል፤ የጨለማ ቀን እንደ ደረሰበትም ያውቃል።
24ጭንቀትና ስቃይ ያስፈራሩታል፤ ለጦርነት ዝግጁ እንደ ሆነ ንጉሥ ይበረቱበታል።
25ምክንያቱም እጁን በእግዚአብሔር ላይ አንስቶአል፥ ሁሉንም በሚችል አምላክ ፊት በትዕቢት ሔዷልና፥
26በደንዳና አንገቱና በወፍራም ጋሻው ሆኖ፥ ይህ አመጸኛ ሰው በእግዚአብሔር ላይ ይመጣልና፥
27ይህ እውነት ነው፥ምንም እንኳ በስብ ፊቱን ቢከድንም፥ ስቡንም በወገቡ ላይ ቢያጠራቅም፥
28በፈረሱ ከተሞች ውስጥ፥ ሰውም በማይኖርበትና፥ ክምር ለመሆን በተመደቡ ቤቶች ውስጥ ይኖራልና፤
29ባለጠጋ አይሆንም፥ ሀብቱም አይጸናም፤ ጥላው እንኳ በምድር ላይ አይቆይም፤
30ከጨለማ ተለይቶ አይወጣም፤ ነበልባልም ቅርንጫፎቹን ያደርቃቸዋል፥ በእግዚአብሔር አፍ እስትንፋስም ይጠፋል።
31ዋጋው ከንቱነት እንዳይሆን፥ ራሱን እያሳተ በከንቱ ነገር አይታመን።
32ቀኑ ሳይደርስ የፍጻሜው ሰዓት ይመጣል፥ ቅርንጫፉም አይለመልምም።
33እንደ ወይን ያልደረሰውን ዘለላ ይጥላል፤ እንደ ወይራ ዛፍም አበባውን ያረግፋል።
34አምላክ የሌለው ህዝብ ጉባኤ ሁሉ ይመክናል፥ የሙሰኞችንም ድንኳን እሳት ትበላለች።
35ተንኰልን ይፀንሳሉ፥ በደልንም ይወልዳሉ፥ ማህጸናቸውም ማታለልን ያዘጋጃል።