1ከሴት የተወለደ ሰው ጥቂት ቀናት ቢኖርም፥ በመከራ የተሞሉ ሆኑ።
2እንደ አበባ ከመሬት ይወጣል፥ ይረግፋልም፤ እንደ ጥላም ይፈጥናል፥ ነገር ግን አይቆይም።
3እንደዚህ ያለውን ሰው ትመለከታለህን? ከአንተስ ጋር እኔን ወደ ፍርድ ታመጣኛለህን?
4ከርኩስ ነገር ንጹሕን ማውጣት ማን ይችላል? ማንም የለም።
5የሰው ዕድሜ የተወሰነ ነው፥ የወራቶቹም ቍጥር በአንተ እጅ ነው፥ እርሱም ሊያልፈው የማይችለውን ገደብ ቀጠርህለት።
6እንደ ተቀጣሪ ሰው የቀሩትን ቀኖች እዲደሰትባቸው፤ እዲያርፍም ከእርሱ ዘወር በል።
7ዛፍ ቢቈረጥ ደግሞ ሊያቈጠቍጥ፥ ቅርንጫፉም ማደግ እንዳያቆም ተስፋ ሊኖረው ይችላል።
8ምንምእንኳ ሥሩ በምድር ውስጥ ቢያረጅ፥ ግንዱም በመሬት ውስጥ ቢሞት፥
9የውኃ ሽታ ሲያገኝ ዳግም ያቈጠቍጣል እንደ አትክልትም ቅርንጫፍ ያወጣል።
10ሰው ግን ይሞታል፤ ይደክማል፤ በርግጥ ሰው እስትንፋሱን ይሰጣል፥ እርሱስ ወዴት አለ?
11ውኃ ከሐይቅ እንደሚያልቅ፤ ወንዙም እንደሚቀንስና እንደሚደርቅ፤
12እንዲሁ ሰዎች ይተኛሉ ዳግም አይነሱም፤ ሰማይ እስኪያልፍ ድረስ አይነቁም፥ ከእንቅልፉቸውም አይነሱም።
13በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ! ቍጣህ እስኪያልፍ ድረስ በሸሸግኸኝ ኖሮ! ቀጠሮም አድርገህ ምነው ባሰብኸኝ ኖሮ!
14በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን? መለወጤ እስኪመጣ ድረስ፥ የሰልፌን ዘመን ሁሉ በትዕግሥት በተጠባበቅሁ ነበር።
15በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር፤ የእጅህንም ሥራ በተመኘኸው ነበር።
16ለእርምጃዬ ጥንቃቄንና ገደብን ታደርግለታለህ፤ ኃጢአቴንም አትቆጣጠርብኝም።
17መተላልፌን በከረጢት ውስጥ ታትመዋለህ፥ ኃጢአቴንም ትሸፍንልኛለህ።
18ነገር ግን ተራራ እንኳ ይወድቃል ይጠፋልም፥ ዓለቶችም እንዲሁ ከስፍራቸው ይለቃሉ፤
19ውኆች በድንጋዮቹ ላይ ይወርዳሉ፤ ጎርፎቹም የምድሩን አፈር ይወስዳሉ፤ እንዲሁ የሰውን ተስፋ ታጠፋዋለህ።
20ሁልጊዜ ታሸንፈዋለህ፥ እርሱም ያልፋል፤ፊቱን ትለውጣለህ፥ እርሱንም ወደ ሞት ትሰድደዋለህ።
21ልጆቹ ወደ ክብር ቢመጡም አያውቅም፤ ቢዋረዱም ይህ ሲሆን አያይም።
22ነገር ግን የራሱ ሰውነት ሕመም ብቻ ይሰማዋል፥ ለራሱም በሃዘን ያለቅሳል።