1እነሆ፥ ይህን ሁሉ ዓይኔ አይቷል፤ ጆሮዬም ሰምቶ አስተውያለሁ።
2እናንተ የምታውቁትን እኔም ደግሞ አውቀዋለሁ ከእናንተ የማንስ አይደለሁም።
3ቢሆንም ግን ሁሉን ከሚችል አምላክ ጋር መነጋገር እመርጣለሁ፥ ከእግዚአብሔርም ጋር መዋቀስ እፈልጋለሁ።
4እናንተ ግን እውነትን በሐሰት ለባጮች ናችሁ፤ ሁላችሁ ዋጋ የሌላችሁ ሃኪሞች ናችሁ።
5ምነው ሁላችሁ ዝም ብትሉ! ይህም ጥበብ ይሆንላችሁ ነበር።
6እንግዲህ ክርክሬን ስሙ፥ የከንፈሬንም ሙግት አዳምጡ።
7ለእግዚአብሔር ጽድቅ የሌለበትን ነገር ትናገሩለታላችሁን? ለእርሱስ በማታለል ታወሩለታላችሁን?
8ቸርነትንስ ታደርጉለታላችሁን? ለእግዚአብሔርስ በሸንጎ ጠበቃ ትሆኑለታላችሁን?
9እንደ ዳኛ ወደ እናንተ ቢዞርና ቢመረምራችሁ ይህ መልካም ይመስላችኋልን? ወይስ አንዱ ሌላውን ሰው እንደሚያታልል፣ በሸንጎ ትሳለቁበታላችሁን?
10በስውር ወደ እርሱ ብታደሉ እንኳ፤ እርሱ በእርግጥ ይገስጻችኋል።
11ግርማዊነቱ አያስፈራችሁምን? ማስደንገጡስ በላያችሁ አይወድቅምን?
12አስገራሚ ንግግራችሁ ከአመድ የተሰሩ ምሳሌዎች ናቸው፤ ምላሻችሁም ከሸክላ የተሰሩ መመከቻዎች ናቸው።
13ዝም በሉ፥ እኔም እንድናገር ተዉኝ፤ የሚመጣው ነገር ይምጣብኝ።
14ሥጋዬን በጥርሴ እይዛለሁ፥ ሕይወቴንም በእጆቼ አኖራታለሁ።
15እነሆ ቢገድለኝ የሚቀርልኝ ተስፋ የለኝም፤ ቢሆንም ስለ መንገዴ በፊቱ እሟገታለሁ።
16አምላክ እንደሌለው ሰው ወደ ፊቱ አልቀረብኩምና፤ለደህንነቴ ይሆንልኛል።
17አምላኬ፡ንግግሬን በሚገባ አድምጥ፥ አስረግጬ የምለውም ለጆሮህ ይድረስ።
18እነሆ አሁን፥ ሙግቴን አሰናድቻለሁ፤ ነጻ እንደምወጣም አውቃለሁ።
19በሸንጎስ ቆሞ የሚከራከረኝ ማን ነው? ጥፋተኛ ሆኜ ከተገኘሁ፤ በዝምታ ህይወቴን ለሞት እሰጣለሁ።
20አማላኬ ሁለት ነገር ብቻ አድርግልኝ፤ እኔም ራሴን ከፊትህ አልሸሽግም፤
21ጠንካራ እጅህን ከእኔ አርቅ፤ በማስደንገጥህም አታስፈራኝ።
22ከዚያም ጥራኝ፥ እኔም እመልስልሃለሁ። ወይም እኔ ልናገር፥ አንተም መልስልኝ።
23በደሌና ኃጢአቴ ምን ያህል ሆነ? መተላለፌንና ኃጢአቴን አስታውቀኝ።
24ፊትህን ከእኔ ለምን ትሰውራለህ፥ እንደ ጠላትህስ ለምን ታደርገኛለህ?
25የረገፈን ቅጠል ታሳድደዋለህን? ወይስ የደረቀን ገለባ ትከታተለዋለህ?
26የመረረ ነገር ስለጻፍህብኝ፤ የወጣትነቴን ኃጢአት ታወርሰኛለህ።
27እግሬንም በእግር ግንድ አስገባኸው፥ መንገዶቼን ሁሉ በቅርበት አየኻቸው፤ የእግሬ መርገጫ የተራመደበትን መሬት ሁሉ መረመርህ።
28ምንምእንኳ እኔ እንደሚጣል ብስባሽ፥ ብልም እንደበላው ልብስ ብሆንም።