1ኢየሱስ በመንገድ ሲያልፍ ፣ ከተወለደ ጀምሮ ዐይነ ስውር የነበረ አንድ ሰው አየ።
2ደቀ መዛሙርቱ፣ “መምህር ሆይ፤ ይህ ሰው ዐይነ ስውር ሆኖ እንዲወለድ ያደረገው የራሱ ኀጢአት ነው ወይስ የወላጆቹ?” አሉት።
3ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ፣ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኀጢአት አልሠሩም።
4የላከኝን ሥራ ቀን ሳለ መሥራት ይገባናል። ማንም ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት እየመጣ ነው።
5በዓለም እስካለሁ፣ የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ።”
6ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ፣ መሬት ላይ እንትፍ ብሎ፣ በምራቁ ጭቃ ሠራ፤ በጭቃውም የሰውየውን ዐይን ቀባ።
7ሰውየውንም፣ “ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠበ” አለው፣ ‘ሰሊሆም’ የተላከ ማለት ነው። ሰውየውም ወደዚያው ሄዶ ታጠበ፤ ዐይኑም እያየለት ተመልሶ መጣ።
8የሰውየው ጐረቤቶችና ቀድሞ ለማኝ ሆኖ ያዩት ሰዎችም፣ “ይህ ሰው ተቀምጦ ሲለምን የነበረው ሰው አይደለምን?” አሉ።
9አንዳንዶቹ፣ “እርሱ ነው” አሉ፤ ሌሎችም፣ “ይመስለዋል እንጂ እርሱ አይደለም” አሉ። እርሱ ግን፣ “እኔው ነኝ” አለ።
10እነርሱም፣ “ታዲያ፣ ዐይኖችህ እንዴት ተከፈቱልህ?” አሉት።
11እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “ኢየሱስ የሚባለው ሰው ጭቃ ሠርቶ ዐይኔን ቀባ፤ ከዚያም፣ ‘ወደ ሰሊሆም ሄደህ ታጠብ’ አለኝ። እኔም ሄጄ ታጠብሁ፤ ዐይኖቼም በሩ።”
12እነርሱም፣ “ታዲያ፣ እርሱ የት ነው?” አሉ። እርሱም፣ “እኔ አላውቅም” ብሎ መለሰላቸው።
13እነርሱም ዐይነ ስውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት።
14ኢየሱስ ጭቃ ሠርቶ የሰውየውን ዐይን የከፈተው በሰንበት ቀን ነበረ።
15ፈሪሳውያንም ዐይኑ እንዴት እንደ ተከፈተለት እንደ ገና ሰውየውን ጠየቁት። እርሱም፣ “ዐይኖቼን ጭቃ ቀባ፤ ታጠብሁና ማየት ቻልሁ” አላቸው።
16ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ፣ “ይህ ሰው ሰንበትን ስለማያከብር፣ ከእግዚአብሔር አይደለም” አሉ። ሌሎቹም፣ “ኀጢአተኛ የሆነ ሰው እንዴት እንደዚህ ያለ ተአምር ይሠራል?” አሉ። ስለዚህ በመካከላቸው መከፋፈል ተፈጠረ።
17እንደ ገናም ዐይነ ስውሩን ሰው፣ “ዐይንህን ስለ ከፈተው ሰው ምን ትላለህ?” አሉት። ዐይነ ስውሩም፣ “ነቢይ ነው” አለ።
18ፈሪሳውያንም ዐይነ ስውር የነበረው ሰው ዐይኖች መከፈታቸውን አሁንም ስላላመኑ፣ ዐይኑ የበራለትን ሰው ወላጆች አስጠሩ።
19ወላጆቹንም፣ “ይህ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደ ነው የምትሉት ሰው ልጃችሁ ነውን? ከሆነስ፣ አሁን እንዴት ማየት ቻለ?” ብለው ጠየቋቸው።
20ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤ “ይህ ልጃችን መሆኑንና ዐይነ ስውር ሆኖ መወለዱን እናውቃለን።
21አሁን እንዴት ማየት እንደ ቻለ ግን አናውቅም፤ ዐይኑን የከፈተለት ማን እንደ ሆነም አናውቅም። እርሱን ጠይቁት፤ ጕልማሳ ነው፤ ስለ ራሱ መናገር ይችላል።”
22ወላጆቹ እንዲህ ያሉት አይሁድን ስለ ፈሩ ነበር። ምክንያቱም አይሁድ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው የሚል ሰው ካገኙ፣ ከምኵራብ ሊያስወግዱት ቀደም ብለው ተስማምተው ነበር።
23ወላጆቹ፣ “እርሱ ጕልማሳ ነው፤ ራሱን ጠይቁት” ያሉትም በዚህ ምክንያት ነበር።
24ዐይነ ስውር የነበረውን ሰው እንደ ገና አስጠርተው፣ “ለእግዚአብሔር ክብር ስጥ፤ እኛ ይህ ሰው ኀጢአተኛ እንደ ሆነ እናውቃለን” አሉት።
25ሰውየውም፣ “እኔ እርሱ ኀጢአተኛ መሆኑን አላውቅም። ነገር ግን አንድ ነገር ዐውቃለሁ፤ ዐይነ ስውር ነበርሁ፤ አሁን ግን እያየሁ ነው” አላቸው።
26እነርሱም፣ “ያደረገልህ ምንድን ነው? ዐይኖችህንስ የከፈተው እንዴት ነው?” አሉት።
27እርሱም፣ “አስቀድሜ ነግሬአችሁ ነበር! እናንተ ግን አትሰሙም። እንደ ገና መስማትስ ለምን ፈለጋችሁ? እናንተም የእርሱ ደቀ መዛሙርት ለመሆን ትፈልጋላችሁን?” ብሎ መለሰ።
28ሰደቡትና እንዲህ አሉ፤ “አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ነህ፣ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን።
29እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከየት እንደ መጣ አናውቅም።”
30ሰውየውም፣ “ይህ ሰው ከየት እንደ መጣ አለማወቃችሁ የሚገርም ነው፤ ይሁን እንጂ፣ ዐይኔን የከፈተው እርሱ ነው።
31እግዚአብሔር ኀጢአተኞችን እንደማይሰማ እናውቃለን፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚያመልክና ፈቃዱን የሚያደርግ ሰው ሁሉ እግዚአብሔር ይሰማዋል።
32ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ፣ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዐይን የከፈተ ሰው ከቶ አልተሰማም።
33ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ፣ አንድም ነገር ማድረግ ባልቻለ ነበር።”
34እነርሱም፣ መልሰው “አንተ ሁለንተናህ በኀጢአት የተወለደ፣ አሁን አንተ እኛን ታስተምረናለህን?” አሉት። ከዚያም ከምኵራብ አስወጡት።
35ኢየሱስም ሰውየውን ከምኵራብ እንዳስወጡት ሰማ። ሰውየውንም አግኝቶ፣ “በሰው ልጅ ታምናለህን?” አለው።
36እርሱም፣ “ጌታ ሆይ፣ አምንበት ዘንድ እርሱ ማን ነው?” አለው።
37ኢየሱስም፣ “አይተኸዋል፤ አሁን እንኳ ከአንተ ጋር እየተነጋገረ ያለው እርሱ ነው” አለው።
38ሰውየውም፣ “ጌታ ሆይ፣ አምናለሁ” አለ። ከዚያም ሰገደለት።
39ኢየሱስም፣ “የማያዩ እንዲያዩ፣ የሚያዩም እንዳያዩ፣ ለፍርድ ወደዚህ ዓለም መጣሁ” አለ።
40ከእነርሱም ጋር ከነበሩት አንዳንድ ፈሪሳውያን ይህን ሰምተው፣ “እኛም ደግሞ ዐይነ ስውራን ነን ወይ?” አሉት።
41ኢየሱስም ፣ “ዐይነ ስውራን ብትሆኑማ፣ ኀጢአት ባልሆነባችሁ ነበር። ነገር ግን፣ ‘እናያለን’ ስለምትሉ፣ ኀጢአታችሁ እንዳለ ይኖራል።”