1“እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች በረት በበር ሳይሆን፣ በሌላ መንገድ ተንጠላጥሎ የሚገባ እርሱ ሌባና ወንበዴ ነው።
2በበር የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው።
3በር ጠባቂውም ለእርሱ ይከፍትለታል። በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ፤ እርሱም የራሱን በጎች በስማቸው ጠርቶ፣ ወደ ውጭ ይመራቸዋል።
4የራሱን ሁሉ ካወጣቸው በኋላ፣ ፊት ፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል።
5ባዕድ የሆነውን አይከተሉትም፤ ይልቁንም የባዕዱን ድምፅ ስለማያውቁት ይሸሹታል።”
6ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸው ስለ ምን እንደ ሆነ አልገባቸውም።
7ኢየሱስም እንደ ገና እንዲህ አላቸው፤ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፤ የበጎች በር እኔ ነኝ።
8ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ በጎቹ ግን አላዳመጡአቸውም።
9በሩ እኔ ነኝ። ማንም በእኔ በኩል ቢገባ፣ ይድናል፤ ይገባል፣ ይወጣልም፤ መሰማሪያም ያገኛል።
10ሌባው የሚመጣው ሊሰርቅ፣ ሊገድልና ሊያጠፋ ብቻ ነው። እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ።
11መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ለበጎቹ ሲል ነፍሱን ይሰጣል።
12እረኛ ያልሆነው ተቀጣሪ በጎቹም የእርሱ ያልሆኑት፣ ቀበሮ መምጣቱን ሲያይ በጎቹን ጥሎ ይሸሻል ። ቀበሮም ነጥቆአቸው ይሄዳል፤ ይበታትናቸውማል።
13የሚሸሸውም ተቀጣሪ ስለ ሆነና ለበጎቹ ደንታ ስለሌለው ነው።
14መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ የእኔ የሆኑትን ዐውቃቸዋለው፤ የእኔ የሆኑትም ያውቁኛል።
15አብ እንደሚያውቀኝ፤ እኔም አብን ዐውቀዋለው፤ ነፍሴንም ስለ በጎች እሰጣለሁ።
16ከዚህ በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ። እነዚያን ደግሞ ማምጣት አለብኝ፤ እነርሱ ድምፄን ይሰማሉ። አንድ መንጋ ይሆናሉ፤ እረኛቸውም አንድ ይሆናል።
17አባቴ የሚወደኝ ለዚህ ነው፤ መልሼ ልወስደው እንድችል ነፍሴን እሰጣለሁ ።
18ነፍሴን ማንም ከእኔ አይወሰድም፤ ግን እኔው ራሴ እሰጣለሁ ። ለመስጠት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ ለመውሰድም ሥልጣን አለኝ። ይህን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀብያለሁ።”
19ከዚህ አባባል የተነሣም በአይሁድ መካከል እንደ ገና መከፋፈል ተፈጠረ።
20ብዙዎች፣ “ጋኔን ስላለበት ዐብዶአል፤ ለምን ታዳምጡታላችሁ?” አሉ።
21ሌሎችም፣ “ንግግሩ ጋኔን ያለበት ሰው ንግግር አይደለም። ጋኔን ያለበት ሰው የዐይነ ስውርን ዐይን መክፈት ይችላልን?” አሉ።
22በኢየሩሳሌምም የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል ደርሶ ነበር።
23ጊዜው ክረምት ነበረ፤ ኢየሱስም በቤተ መቅደስ በሰሎሞን መተላለፊያ ይመላለስ ነበር።
24ከዚያም አይሁድ ወደ እርሱ ተሰብስበው፣ «እስከ መቼ ድረስ ልባችንን ታንጠለጥላለህ? አንተ ክርስቶስ ከሆንህ፣ በግልጽ ንገረን» አሉት።
25ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ነገርኋችሁኮ፤ እናንተ ግን አታምኑም፤ በአባቴ ስም የማደርጋቸው ሥራዎች እነዚህ ስለ እኔ ይመሰክራሉ።
26እናንተ ግን በጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም።
27በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔ ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል።
28የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለው፤ ፈጽሞም አይጠፉም፤ ነጥቆ ከእጄ የሚያወጣቸው ማንም የለም።
29እነርሱን ለእኔ የሰጠ አባቴ ከሌሎች ሁሉ ይበልጣል፤ ስለዚህ ከአብ እጅ ነጥቆ ሊያወጣቸው የሚችል ማንም የለም።
30እኔና አብ አንድ ነን።”
31አይሁድ ሊወግሩት እንደ ገና ድንጋይ አነሡ።
32ኢየሱስም መልሶ፣ «ከአብ የሆነ ብዙ መልካም ሥራ አሳይቻችኋለሁ፤ ከእነዚህ ሥራዎች ውስጥ በየትኛው ምክንያት ትወግሩኛላችሁ?” አላቸው።
33አይሁድም መልሰው፣ «የምንወግርህ በየትኛውም መልካም ሥራ ምክንያት አይደለም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ በምትሰነዝረው የስድብ ቃል ምክንያት ነው፤ አንተ ሰው ሆነህ ሳለህ፣ ራስህን አምላክ እያደረግህ ስለ ሆነ ነው» አሉት።
34ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ «በሕጋችሁ፣ ‘አማልክት ናችሁ አልሁ’ ተብሎ አልተጻፈምን?
35የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ናችሁ ካላቸው፣ የመጻሕፍት ቃል አይሻርምና፣
36እኔ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ስላልሁ፣ አብ ቀድሶ ወደ ዓለም የላከውን እንዴት የስድብ ቃል ሰነዘረ ትሉታላችሁ?
37እኔ የአባቴን ሥራዎች የማላደርግ ከሆንሁ አትመኑኝ።
38ነገር ግን የማደርጋቸው ከሆንሁ፣ በእኔ ባታምኑ እንኳ፣ አብ በእኔ እንዳለ፣ እኔም በአብ እንዳለሁ እንድታውቁና እንድትረዱ፣ በሥራዎቹ እመኑ።»
39እነርሱም ኢያሱስን እንደ ገና ለመያዝ ሞከሩ፣ እርሱ ግን ከእጃቸው አምልጦ ሄደ።
40ኢየሱስ ዮርዳኖስን ተሻግሮ፣ ዮሐንስ በመጀመሪያ ሲያጠምቅበት ወደ ነበረው ቦታ እንደ ገና ሄደ፤ በዚያም ቆየ ።
41ብዙ ሰዎች ወደ ኢየሱስ መጡ። እነርሱም፣ «በርግጥ ዮሐንስ ምንም ተአምር አልሠራም፤ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነው» ይሉ ነበር።
42በዚያም ብዙ ሰዎች በኢያሱስ አመኑ።