1ኢየሱስ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ።
2ጠዋት በማለዳ ተመልሶ ወደ ቤተ መቅደስ መጣ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱም ተቀምጦ አስተማራቸው።
3የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያንም ስታመነዝር የተያዘችን ሴት አምጥተው፤ በመካከላቸው አቆሟት።
4ከዚያም ኢየሱስን እንዲህ አሉት፤ «መምህር ሆይ፣ ይህች ሴት ስታመነዝር እጅ ከፍንጅ የተያዘች ናት፤
5ሙሴ በሕጉ እንዲህ ያሉትን በድንጋይ እንድንወግር አዞናል፤ አንተስ ስለ እርሷ ምን ትላለህ?»
6ይህን ያሉት እርሱን ወጥመድ ውስጥ ለማስገባትና ለመክሰስ ፈልገው ነው፤ ኢየሱስ ግን ጎንበስ ብሎ በጣቱ መሬት ላይ ጻፈ።
7ጥያቄ ማቅረባቸውን በቀጠሉ ጊዜም፣ ተነሥቶ ቆመና፣ “ከእናንተ መካከል ኃጢአት የሌለበት ሰው በመጀመሪያ ይውገራት” አላቸው።
8ዳግመኛም ጐንበስ ብሎ፣ በጣቱ መሬት ላይ ጻፈ።
9ይህንም በሰሙ ጊዜ፣ ከታላቅ ጀምረው አንድ ባንድ ወጥተው ሄዱ። በመጨረሻ ኢየሱስ በመካከላቸው ቆማ ከነበረችው ሴት ጋር ለብቻው ቀረ።
10ኢየሱስ ተነሥቶ በመቆም፣ “አንቺ ሴት፤ የከሰሱሽ ሰዎች የት ናቸው? አንድም የፈረደብሽ የለም?” አላት።
11እርሷም፣ “ጌታ ሆይ፣ አንድም የለም” አለች። ኢየሱስ፣ “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁን በኋላ ግን ደግመሽ ኀጢአት አትሥሪ” አላት።
12ደግሞም ኢየሱስ ሕዝቡን፣ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ ቢኖር የሕይወት ብርሃን ያገኛል እንጂ፣ በጨለማ አይመላለስም” አላቸው።
13ፈሪሳውያንም፣ “አንተው ስለ ራስህ ስለምትመሰክር፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም” አሉት።
14ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር እንኳ ምስክርነቴ እውነት ነው። ከየት እንደ መጣሁ፣ ወዴትም እንደምሄድ ዐውቃለሁ፤ እናንተ ግን እኔ ከየት እንደ መጣሁ ወይም ወዴት እንደምሄድ አታውቁም።
15እናንተ በሥጋዊ ዐይን ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በማንም አልፈርድም።
16ብፈርድም እንኳ፣ ብቻዬን አይደለሁም፤ ከላከኝ አብ ጋር ስለ ሆንሁ፣ ፍርዴ እውነት ነው።
17አዎን፤ በሕጋችሁ የሁለት ሰዎች ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ ተጽፎአል።
18እኔ ስለ ራሴ እመሰክራለሁ፤ የላከኝም አብ ስለ እኔ ይመሰክራል።”
19እነርሱም፣ “አባትህ የት ነው ያለው?” አሉት። ኢየሱስም፣ “እናንተ እኔንም ሆነ አባቴን አታውቁንም፤ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር” አላቸው።
20ይህንም የተናገረው በቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት አጠገብ ሆኖ ሲያስተምር ነበር፤ ሆኖም ሰዓቱ ገና ስላልደረሰ፣ ማንም አልያዘውም።
21ደግሞም፣ “እኔ ተለይቻችሁ እሄዳለሁ፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ። እኔ ወደምሄድበት መምጣት አትችሉም” አላቸው።
22አይሁድም፣ “ይህ 'እኔ ወደምሄድበት መምጣት አትችሉም' የሚለው ራሱን ሊገድል ዐስቦ ይሆን?” አሉ።
23ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ከታች ናችሁ፤ እኔ ግን ከላይ ነኝ። እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፤ እኔ ግን ከዚህ ዓለም አይደለሁም።
24በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ ያልኋችሁ ለዚህ ነው። ምክንያቱም እኔ ነኝ ስላችሁ ካላመናችሁ፣ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ።”
25እነርሱም፣ “ለመሆኑ፣ አንተ ማን ነህ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤”ከመጀመሪያው እንደ ነገርኋችሁ ነኝ።
26ብዙ የምናገረውና ስለ እናንተም የምፈርደው አለኝ። ይሁን እንጂ የላከኝ እርሱ እውነተኛ ነው፤ እኔም ከእርሱ የሰማሁትን፣ ያንኑ ለዓለም እናገራለሁ።”
27እነርሱ ግን ስለ አብ እየነገራቸው እንደ ነበር አልተረዱም።
28ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የሰውን ልጅ ወደ ላይ ከፍ ስታደርጉት፣ በዚያን ጊዜ እኔው እንደ ሆንሁና ከራሴ አንድም ነገር እንደማላደርግ ታውቃላችሁ። አብ እንዳስተማረኝ ይህን እናገራለሁ።
29የላከኝ እርሱ ከእኔ ጋር ነው፤ ብቻዬንም አልተወኝም፤ እኔ ሁልጊዜ እርሱን ደስ የሚያሰኘውን ነገር አደርጋለሁና።”
30ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች በተናገረ ጊዜ ብዙ ሰዎች በእርሱ አመኑ።
31ኢየሱስ በእርሱ ያመኑትን አይሁድ፣ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ፣ በርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤
32እውነትን ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል” አላቸው።
33እነርሱም፣ “እኛ የአብርሃም ዘሮች ነን፤ የማንም ባሪያ ሆነን አናውቅም፤ ታዲያ እንዴት ‘ነጻ ትወጣላችሁ’ ትለናለህ?” አሉት።
34ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ኃጢአት የሚሠራ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው።
35ባሪያ ለዘለቄታ በቤት አይኖርም፤ ልጅ ግን ለዘለቄታ ይኖራል።
36ስለዚህ ልጁ ነጻ ካወጣችሁ፣ በርግጥ ነጻ ትወጣላችሁ።
37የአብርሃም ዘር መሆናችሁን ዐውቃለሁ፤ ቃሌን ስላልተቀበላችሁ፣ ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ።
38አባቴ ጋ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተም ደግሞ ከአባታችሁ የሰማችሁትን ታደርጋላችሁ።”
39እነርሱም መልሰው፣ “አባታችንስ አብርሃም ነው” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “የአብርሃም ልጆችስ ብትሆኑ ኖሮ፣ የአብርሃምን ሥራ በሠራችሁ ነበር።
40አሁን ግን ከእግዚአብሔር የሰማሁትን እውነት የነገርኋችሁን ሰው ለመግደል ትፈልጋላችሁ። አብርሃምኮ ይህን አላደረገም።
41እናንተ ግን የአባታችሁን ሥራ ትሠራላችሁ።” እነርሱም፣ “እኛ በዝሙት የተወለድን አይደለንም፤ አንድ አባት እግዚአብሔር አለን” አሉት።
42ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር አባታችሁ ቢሆን ኖሮ፣ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ ስለ መጣሁ፣ በወደዳችሁኝ ነበር፤ በራሴም ፈቃድ አልመጣሁም፤ ነገር ግን እርሱ ላከኝ።
43ቃሌን የማትረዱት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ቃሌን መስማት ስለማትችሉ ነው።
44እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት ለማድረግ ትመኛላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያውም ነፍሰ ገዳይ ነበር፤ እውነት በእርሱ ዘንድ ስለሌለም፣ በእውነት አይጸናም። ሐሰትንም ሲናገር ከራሱ አፍልቆ ይናገራል፤ ምክንያቱም እርሱ ሐሰተኛ፣ የሐሰትም አባት ነው።
45እኔ ግን እውነትን ስለምናገር አታምኑኝም።
46ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ሰው ማን ነው? እውነትን የምናገር ከሆነስ፣ ታዲያ ለምን አታምኑኝም?
47ከእግዚአብሔር ስላልሆናችሁ፣ ቃሉን አትሰሙም።”
48አይሁድም፣ “እንግዲህ ጋኔን ያደረብህ ሳምራዊ ነህ በማለታችን እውነት አልተናገርንምን?” በማለት መለሱለት።
49ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ ጋኔን የለብኝም፤ እኔ አባቴን አከብረዋለሁ እንጂ፣ እናንተ ግን ታዋርዱኛላችሁ።
50እኔ የራሴን ክብር አልሻም፤ የሚሻና የሚፈርድ አንድ አለ።
51እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚጠብቅ ማንም ቢኖር፣ እርሱ ሞትን በፍጹም አያይም።”
52አይሁድም፣ “አሁን ጋኔን እንዳለብህ ዐወቅን። አብርሃምም ነቢያትም ሞተዋል፤ አንተ ግን 'ማንም ቃሌን ቢጠብቅ ሞትን አይቀምስም' ትላለህ።
53አንተ ከሞተው ከአባታችን፣ ከአብርሃም ትበልጣለህን? ነቢያትም ሞተዋል። ለመሆኑ፣ አንተ ማን ነኝ ልትል ነው?” አሉት።
54ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ራሴን ባከብር፣ ክብሬ ከንቱ ነው፤ እኔን የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን ነው የምትሉት አባቴ ነው።
55እናንተ እርሱን አላወቃችሁትም፤ እኔ ግን ዐውቀዋለሁ። እኔ ‘አላውቀውም’ ብል እንደ እናንተው ሐሰተኛ እሆናለሁ። ነገር ግን እኔ ዐውቀዋለሁ፤ ቃሉንም እጠብቃለሁ።
56አባታችሁ አብርሃም ቀኔን በማየቱ ደስ አለው፤ አይቶም ሐሤት አደረገ።”
57አይሁድም፣ “ገና ዐምሳ ዓመት ያልሞላህ፣ አንተ አብርሃምን አይተሃልን?” አሉት።
58ኢየሱስም፣ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ አለሁ” አላቸው።
59እነርሱም፣ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ራሱን ሰውሮ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሄደ።