መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዮሐንስ 7

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከዚህ በኋላ ኢየሱስ አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበር፣ ወደ ይሁዳ መሄድ አልፈለገም፤ ስለዚህ እዚያው በገሊላ ውስጥ ይመላለስ ነበር፡፡
2የአይሁድ የዳስ በዓል የሚከበርበትም ጊዜ ተቃርቦ ነበር፡፡
3ስለዚህ ወንድሞቹ እንዲህ አሉት፤ ‹‹ተነሥተህ ከዚህ ስፍራ ወደ ይሁዳ አውራጃ ሂድ፤ ደቀ መዛሙርትህም ደግሞ አንተ የምትሠራውን ሥራ ይዩ፡፡
4በሕዝብ ፊት መታወቅ የሚፈልግ ሰው የሚሠራውን ሥራ በድብቅ አያደርግም፡፡ እነዚህን ነገሮች የምታደርግ ከሆነ፣ ራስህን ለዓለም አሳይ፡፡››
5ምክንያቱም ወንድሞቹ እንኳ ገና አላመኑበትም ነበር፡፡
6ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ ‹‹ጊዜዬ ገና ነው፡፡ ለእናንተማ ጊዜው ሁሉ የተመቸ ነው፡፡
7ዓለም እናንተን ሊጠላችሁ አይችልም፡፡ እኔን ግን በክፉ ሥራው ስለምመሰክርበት፣ ይጠላኛል፡፡
8እናንተ ወደ በዓሉ ውጡ፤ እኔ ግን ጊዜዬ ገና ስላልደረሰ፣ ወደ በዓሉ አልሄድም፡፡››
9እርሱ ይህን ካላቸው በኋላ፣ በገሊላ ቈየ፡፡
10ነገር ግን ወንድሞቹ ወደ በዓሉ ከሄዱ በኋላ እርሱም በግልጽ ሳይሆን በስውር ወደዚያው ሄደ፡፡
11አይሁድ በበዓሉ ላይ ሊፈልጉት ሄደው፣ ‹‹እርሱ ያለው የት ነው?›› አሉ፡፡
12በሕዝቡም መካከል ብዙ ውይይት ተነሥቶ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ፣ ‹‹እርሱ ጥሩ ሰው ነው›› አሉ፤ ሌሎቹም፣ ‹‹አይደለም፣ ሕዝቡን እያሳተ ነው›› አሉ፡፡
13ይሁን እንጂ፣ አይሁድን ስለ ፈሩ፣ ስለ እርሱ በግልጽ የተናገረ ማንም አልነበረም፡፡
14በበዓሉ አጋማሽ ላይ፣ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ወጥቶ ማስተማር ጀመረ፡፡
15አይሁድም እየተደነቁ፣ ‹‹ይህ ሰው እንዴት ይህን ሁሉ ዐወቀ? ትምህርት እንኳ አልተማረም›› ይሉ ነበር፡፡
16ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ ‹‹የማስተምረው ከራሴ አይደለም፤ ነገር ግን ትምህርቴ ከላከኝ ነው›፡፡
17ማንም የእርሱን ፈቃድ ለማድረግ ቢፈልግ፣ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር የመጣ መሆኑን ወይም ከራሴ የምናገር መሆኑን ያውቃል፡፡
18ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እውነተኛ ነው፤ ሐሰትም የለበትም፡፡
19ሙሴ ሕግ ሰጥቶአችሁ አልነበረምን? ነገር ግን ከእናንተ ሕጉን የሚጠብቅ አንድም ሰው የለም፡፡ ለመሆኑ፣ ልትገድሉኝ የምትፈልጉት ለምንድን ነው?››
20ሕዝቡ፣ ‹‹ጋኔን አለብህ፤ አንተን ማን ሊገድል ይፈልጋል?›› ብለው መለሱ፡፡
21ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ ‹‹አንድን ሥራ በመሥራቴ ሁላችሁም በዚህ ትደነቃላችሁ፡፡
22ሙሴ ግዝረትን ሰጣችሁ፤ ይህም የመጣው ከአባቶች እንጂ ከሙሴ አልነበረም፤ ስለሆነም፣ በሰንበት ቀን ሰውን ትገርዛላችሁ፡፡
23ሰውን በሰንበት ቀን ስትገርዙ የሙሴ ሕግ የማይሻር ከሆነ፣ እኔ በሰንበት ቀን የሰውን መላ አካል ስላዳንሁ ለምን በእኔ ላይ ትቈጣላችሁ?
24መልክ በማየት ሳይሆን በቅንነት ፍረዱ፡፡››
25ከኢየሩሳሌም ከመጡት አንዳንዶቹ እንዲህ አሉ፤ ‹‹ሊገድሉት የሚፈልጉት ይህን ሰው አልነበረም?
26ተመልከቱ፤ እንዲህ በግልጽ እየተናገረ ምንም አይሉትም፡፡ ገዦቹ እርሱ በትክክል ክርስቶስ መሆኑን ዐውቀው ይሆን?
27እኛ ግን ይህ ሰው ከየት እንደ መጣ እናውቃለን፤ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ማንም ከየት እንደ መጣ አያውቅም፡፡››
28ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሲያስተምር ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ ‹‹እኔን ታውቁኛላችሁ፤ ከየት እንደ መጣሁም ታውቃላችሁ፤ ሆኖም በራሴ አልመጣሁም፤ የላከኝ ግን እውነተኛ ነው፤ እርሱን ደግሞ እናንተ አታውቁትም፡፡
29እኔ ከእርሱ ዘንድ ስለ መጣሁ፣ ዐውቀዋለሁ፤ የላከኝም እርሱ ነው፡፡››
30እነርሱም በዚህ ጊዜ ሊይዙት ሞከሩ፤ ነገር ግን የነካው አንድም ሰው አልነበረም፤ ምክንያቱም የተወሰነለት ሰዓት ገና ነበር፡፡
31ይሁን እንጂ፣ በሕዝቡ መካከል ብዙዎች በእርሱ አመኑ፡፡ ያመኑትም፣ ‹‹ክርስቶስ ሲመጣ ይህ ሰው ከሠራው ተአምር የሚበልጥ ሊሠራ ይችላልን?›› አሉ፡፡
32ፈሪሳውያን ሕዝቡ ስለ ኢየሱስ በሹክሹክታ የሚያወሩትን ሰሙ፤ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ሊያስይዙት የጥበቃ ሰዎችን ላኩበት፡፡
33ኢየሱስ፣ ‹‹ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ከዚያም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፡፡
34ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፡፡ እናንተ ወደምሄድበት መምጣት አትችሉም›› አላቸው፡፡
35ስለዚህ አይሁድ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ ‹‹ይህ ሰው እንዳናገኘው ወዴት ሊሄድ ነው? ተበትነው በግሪክ ወዳሉት ሰዎች ሄዶ እነርሱን ሊያስተምር ይሆን?
36‹ትፈልጉኛላችሁ፤ ግን አታገኙኝም፡፡ እናንተ እኔ ወደምሄድበት መምጣት አትችሉም› ያለውስ ቃል ምን ማለት ነው?››
37በታላቁ የበዓሉ ቀን፣ በመጨረሻው ቀን፣ ኢየሱስ ቆሞ ድምፁን ከፍ በማድረግ፣ ‹‹የተጠማ ማንም ቢኖር፣ ወደ እኔ መጥቶ ይጠጣ፡፡
38ቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተናገሩት፣ በእኔ የሚያምን የሕይወት ውሃ ወንዝ ከውስጡ ይፈልቃል›› አለ፡፡
39ይህን ያለው ግን በእርሱ የሚያምኑት ወደ ፊት ስለሚቀበሉት፣ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ፣ መንፈስ ቅዱስ ገና አልተሰጠም ነበር፡፡
40ከሕዝቡ አንዳንዶቹ ይህን ቃል ሲሰሙ፣ ‹‹ይህ በእርግጥ ነቢዩ ነው›› አሉ፡፡
41ሌሎቹ ደግሞ፣ ‹‹እርሱ ክርስቶስ ነው›› አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ግን፣ ‹‹ክርስቶስ ከገሊላ እንዴት ይመጣል!
42ቅዱሳት መጻሕፍት ክርስቶስ ከዳዊት ዘር፣ የዳዊት ከተማ ከሆነችው ከቤተ ልሔም እንደሚመጣ ተናግረው የለምን?›› አሉ፡፡
43ስለዚህ እርሱን በተመለከተ በመካከለቸው መለያየት ተከሠተ፡፡
44ከእነርሱ አንዳንዶቹ ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ማንም አልነካውም፡፡
45ከዚያም የጥበቃ ሰዎቹ ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን ተመልሰው መጡ፤ የላኳቸውም፣ ‹‹ለምንድን ነው ይዛችሁ ያላመጣችሁት?›› አሏቸው፡፡
46የጥበቃ ሰዎቹ፣ ‹‹ከዚህ ቀደም እንደዚህ የተናገረ አልነበረም›› አሏቸው፡፡
47ፈሪሳውያንም እንዲህ አሏቸው፤ ‹‹እናንተም ሳታችሁን?
48ከገዦቹ ወይም ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለ?
49ነገር ግን ሕጉን የማያውቅ ይህ ሕዝብ የተረገመ ነው፡፡››
50ከፈሪሳውያን አንዱ፣ ከዚህ በፊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስ፣
51‹‹መጀመሪያ ከሰውየው ሳይሰማና የሚሠራውን ሳያውቅ፣ የእኛ ሕግ በሰው ላይ ይፈርዳልን?›› አላቸው፡፡
52እነርሱ፣ ‹‹አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህ ወይ? ነቢይ ከገሊላ እንደማይመጣ መርምረህ ዕወቅ›› አሉት፡፡
53ከዚያም እያንዳንዱ ሰው ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ (*53 የጥንት ቅጆች በዮሐንስ 7፡53-8፡11 ላይ ያለውን ክፍል አያካትቱም፡፡)
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።