መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዮሐንስ 6

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከዚህ በኋላ ኢየሱስ የጥብርያዶስ ባሕር ወደሚባለው ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ተሻገረ፡፡
2ብዙ ሰዎች ሕመምተኞችን በመፈወስ ያደረጋቸውን ተአምራት ስላዩ ተከተሉት፡፡
3ኢየሱስ ወደ ተራራ ወጥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚያ ተቀመጠ፡፡
4የአይሁድ የፋሲካ በዓልም ተቃርቦ ነበር፡፡
5ኢየሱስ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ ባየ ጊዜ፣ ፊልጶስን፣ ‹‹ይህ ሁሉ ሕዝብ እንዲበላ እንጀራ ከየት እንግዛ?›› አለው፡፡
6ኢየሱስ ይህን ያለው ፊልጶስን ሊፈትን ነበር እንጂ፣ እርሱ ራሱ ሊያደርግ ያሰበውን ያውቅ ነበር፡፡
7ፊልጶስ፣ ‹‹ይህ ለእያንዳንዱ ሰው ቍራሽ እንዲደርሰው የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ እንኳ ብንገዛ አይበቃም›› አለ፡፡
8ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም የሆነው እንድርያስም ኢየሱስን፣
9‹‹አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ አንድ ልጅ እዚህ አለ፤ ነገር ግን ይህ ለዚህ ሁሉ ሕዝብ ምን ይጠቅማል?›› አለው፡፡
10ኢየሱስ፣ ‹‹ሕዝቡ እንዲቀመጡ አድርጉ›› አላቸው፡፡ ስፍራውም በሣር የተሸፈነ ነበር፡፡ ስለዚህ ቍጥራቸው አምስት ሺህ የሚያህል ወንዶች ተቀመጡ፡፡
11ከዚያም ኢየሱስ እንጀራውንና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ባረከና ለተቀመጡት ዐደለ፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ከዓሣውም የሚፈልጉትን ያህል ዐደላቸው፡፡
12ሕዝቡ በጠገቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፣ ‹‹አንዳችም እንዳይጣል የተረፈውን ፍርፋሪ ሰብስቡ›› አላቸው፡፡
13ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ ሕዝቡ ከበሉ በኋላ የተረፈውን ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ የገብስ እንጀራ ፍርፋሪ ሰበሰቡ፡፡
14ከዚያም ሕዝቡ ኢየሱስ ያደረገውን ይህን ምልክት ባዩ ጊዜ፣ ‹‹ይህስ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው›› አሉ፡፡
15ኢየሱስም ሊመጡና ይዘው በግድ ሊያነግሡት እንደ ፈለጉ በተረዳ ጊዜ፣ እንደ ገና ለብቻው ወደ ተራራ ጫፍ ወጣ፡፡
16በመሸም ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕሩ ወረዱ፤
17በጀልባ ተሳፍረው ወደ ቅፍርናሆም በባሕር ላይ መጓዝ ጀመሩ፡፡ ጊዜው መሽቶ ነበር፤ ኢየሱስም ገና ወደ እነርሱ አልመጣም ነበር፡፡
18በዚህ ጊዜ ባሕሩ ከኀይለኛ ነፋስ የተነሣ ይታወክ ነበር፡፡
19ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ሃያ አምስት ወይም ሠላሳ ምዕራፍ ያህል እንደ ቀዘፉ፣ ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ እነርሱ ወዳሉበት ጀልባ ሲቃረብ አይተውት ፈሩ፡፡
20ይሁን እንጂ እርሱ፣ ‹‹እኔ ነኝ አትፍሩ›› አላቸው፡፡
21ከዚያም ጀልባዋ ላይ እንዲወጣ ፈቀዱለት፣ ጀልባዋም ወዲያው ወደሚሄዱበት ስፍራ ደረሰች፡፡
22በማግስቱም በማዶ ቆመው የነበሩ ሕዝብ አንድም ጀልባ በባሕሩ ላይ እንዳልነበረ አዩ፤ በዚያ የነበረው አንድ ጀልባ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ያልተሳፈረበት ብቻ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም ብቻቸውን ከዚያ ሄደው ነበር፡፡
23ይሁን እንጂ ጌታ አመስግኖ ሰዎቹን እንጀራ ካበላበት ስፍራ አጠገብ፣ ከጥብርያዶስ የመጡ አንዳንድ ጀልባዎች እዚያ ነበሩ፡፡
24ሕዝቡም፣ ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ እዚያ እንዳልነበሩ በተረዱ ጊዜ፣ ራሳቸው በጀልባዎቹ ተሳፍረው ኢየሱስን ፍለጋ ሄዱ፡፡
25በባሕሩ ማዶ ኢየሱስን ባገኙት ጊዜ፣ ‹‹መምህር ሆይ፤ ወደዚህ የመጣኸው መቼ ነው?›› አሉት፡፡
26ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ ‹‹እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ እኔን የምትፈልጉኝ ምልክቶችን ስላያችሁ ሳይሆን፣ እንጀራውን በልታችሁ ስለ ጠገባችሁ ነው፡፡
27ለሚጠፋ ምግብ አትሥሩ፤ ይልቁን ወልድ ለሚሰጣችሁ ዘላለም ለሚኖር ሕይወት ሥሩ፤ እግዚአብሔር አብ ማኅተሙን በእርሱ ላይ አትሞአልና፡፡››
28ከዚያም፣ ‹‹የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ?›› አሉት፡፡
29ኢየሱስ፣ ‹‹የምትሠሩት የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው ማመን ነው›› ብሎ መለሰላቸው፡፡
30ስለዚህ እነርሱ እንዲህ አሉት፤ ‹‹አይተን እንድናምንህ ምን ተአምር ትሠራለህ? ምንስ ታደርጋለህ?
31‹እንዲበሉ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው› ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ፡፡››
32ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ ‹‹እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፤ መና እንድትበሉ ከሰማይ የሰጣችሁ ሙሴ አልነበረም፤ ነገር ግን ከሰማይ እውነተኛ እንጀራ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው፤
33ከሰማይ የሚወርድና ለዓለም ሕይወትን የሚሰጥ የእግዚአብሔር እንጀራ ነውና፡፡››
34ስለዚህ፣ ‹‹ጌታ ሆይ፣ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን›› አሉት፡፡
35ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ ‹‹እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ አይራብም፤ በእኔ የሚያምንም ከቶ አይጠማም፡፡
36ነገር ግን እኔን አይታችሁ አሁንም ገና ስላላመናችሁብኝ ይህን አልኋችሁ፡፡
37አባቴ የሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ እኔም አባቴ የሰጠኝን ከቶ ወደ ውጭ አላባርርም፡፡
38ከሰማይ የወረድሁት የራሴን ፈቃድ ለማድረግ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለመፈጸም ነውና፡፡
39የላከኝም ፈቃድ፣ እርሱ ከሰጠኝ ሁሉ አንድም ሳይጠፋ፣ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣቸው ነው፡፡
40የአባቴ ፈቃድ፣ ወልድን አይቶ በእርሱ ያመነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው፡፡ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ፡፡››
41ከዚያም የአይሁድ መሪዎች፣ ‹‹እኔ ከሰማይ የወረድሁ የሕይወት እንጀራ ነኝ›› በማለቱ አጕረመረሙበት፡፡
42እነርሱ፣ ‹‹ይህ ኢየሱስ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን? አባቱንና እናቱንስ የምናውቃቸው አይደሉምን? ታዲያ፣ እንዴት ከሰማይ ወረድሁ ይለናል?›› ተባባሉ፡፡
43ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ ‹‹እርስ በርስ ማጕረምረማችሁን ተዉት፡፡
44አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ የሚመጣ የለም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ፡፡
45በነቢያት፣ ‹ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ› ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ከአብ የሰማና የተማረ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፡፡
46ከእግዚአብሔር ከሆነው በቀር አብን ያየ ማንም የለም፤ እርሱ አብን አይቶታል፡፡
47እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፤ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፡፡
48እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ፡፡
49አባቶቻችሁ በበረሐ መና በሉ፣ ሞቱም፡፡
50ሰው በልቶት እንዳይሞት፣ ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፡፡
51ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፡፡ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፡፡ ለዓለም ሕይወት እንዲሆነው የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው፡፡››
52አይሁድ በዚህ አባባሉ ተቈጥተው፣ ‹‹ይህ ሰው እንዴት እንድንበላ ሥጋውን ሊሰጠን ይችላል?›› በማለት እርስ በርስ ተከራከሩ፡፡
53ከዚያም ኢየሱስ፣ ‹‹እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ፣ ደሙንም ካልጠጣችሁ የራሳችሁ የሆነ ሕይወት አይኖራችሁም›› አላቸው፡፡
54‹‹ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ፤
55ሥጋዬ እውነተኛ መብል፣ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና፡፡
56ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ፡፡
57ሕያው አብ እንደ ላከኝና እኔ ከአብ የተነሣ እንደምኖር፣ የሚበላኝም ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል፡፡
58አባቶቻችን በልተውት እንደ ሞቱ ዐይነት ሳይሆን፣ ይህ ከሰማይ የወረደ እንጀራ ነው፡፡ ይህን እንጀራ የበላ ለዘላለም ይኖራል፡፡››
59ኢየሱስ ይህን የተናገረው በቅፍርናሆም፣ በምኵራብ ሲያስተምር ነበር፡፡
60ከዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ይህን ሲሰሙ፣ ‹‹ይህ ጠንካራ ትምህርት ነው፤ ማን ሊቀበለው ይችላል?›› አሉ፡፡
61ኢየሱስ በዚህ ማጕረምረማቸውን በገዛ ራሱ ስላወቀ፣ ‹‹ይህ አሰናከላችሁ እንዴ?
62ታዲያ፣ የሰው ልጅ ቀድሞ ወደ ነበረበት ስፍራ፣ ተመልሶ ወደ ላይ ሲወጣ ብታዩ ምን ልትሉ ነው?
63ሕይወት የሚሰጠው መንፈስ ነው፤ ሥጋ ለምንም አይጠቅምም፡፡ እኔ የነገርኋችሁ ቃላት መንፈስ ናቸው፤ ሕይወትም ናቸው፡፡
64ይሁን እንጂ፣ ከእናንተ መካከል የማያምኑ አንዳንዶች አሉ›› አለ፡፡ ከመጀመሪያው በእርሱ የማያምኑ እነማን እንደ ሆኑና የሚከዳው ማን እንደ ሆነ ያውቅ ነበርና፡፡
65ደግሞም፣ ‹‹ከአብ ከተሰጠው በቀር ማንም ወደ እኔ ሊመጣ አይችልም ያልኋችሁ ለዚህ ነው›› አለ፡፡
66ከዚህ በኋላ፣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ትተውት ወደ ኋላቸው ተመለሱ፤ አብረውትም አልተጓዙም፡፡
67ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን፣ ‹‹እናንተም ትታችሁኝ ልትሄዱ ትፈልጋላችሁን?›› አላቸው፡፡
68ስምዖን ጴጥሮስ እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ ‹‹ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤
69እኛም አምነናል፤ አንድያ የእግዚአብሔር ቅዱስ መሆንህንም ዐወቀናል፡፡››
70ኢየሱስ፣ ‹‹እኔ ዐሥራ ሁለታችሁንም መርጫችሁ የለም ወይ? ከእናንተም መካከል አንዱ ዲያብሎስ ነው›› አላቸው፡፡
71ይህን ያለው ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ስለ ሆነውና ኋላም ኢየሱስን አሳልፎ ስለ ሰጠው፣ ስለ አስቆሮቱ ስምዖን ልጅ፣ ስለ ይሁዳ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።