መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዮሐንስ 5

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፤ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።
2በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ፣ አምስት ጣሪያ ያላቸው መመላለሻዎች ነበሩ። በዚያ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የሚባል አንድ መጠመቂያ ነበረ።
3በእነዚህ መመላለሻዎች ወለል ላይ በጣም ብዙ ሕሙማን፣ ዐይነ ስውሮች፣ አንካሶች ወይም ሽባዎች ተኝተው ነበር።
5በዚያም ለሠላሳ ስምንት ዓመት ሽባ ሆኖ የኖረ አንድ ሰው ነበረ።
6ኢየሱስ ሰውየውን እዚያ ተኝቶ ባየው ጊዜ፣ ለረጅም ጊዜ በዚያ መቆየቱን ዐውቆ፣ «መዳን ትፈልጋለህን?» አለው።
7ሕመምተኛውም ሰው መልሶ፣ «ጌታ ሆይ፣ ውሃው በሚናወጥበት ጊዜ መጠመቂያው ውስጥ የሚያስገባኝ ሰው የለኝም፤ ለመግባትም ስሞክር ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል» አለው።
8ኢየሱስ፣ «ተነሥ! የተኛህበትን ምንጣፍ ተሸክመህ ሂድ» አለው።
9ሰውየው ወዲያውኑ ተፈወሰ፤ የተኛበትንም ምንጣፍ ተሸክሞ ሄደ። ያም ቀን ሰንበት ነበረ።
10ስለዚህ የአይሁድ መሪዎች የተፈወሰውን ሰው፣ «ሰንበት ነው፤ ምንጣፍህን ልትሸከም አልተፈቀደልህም» አሉት።
11እርሱ ግን፣ «ያ ያዳነኝ ሰው፣ 'የተኛህበትን ምንጣፍ ተሸክመህ ሂድ'» አለኝ ብሎ መለሰላቸው።
12እነርሱም፣ «የተኛህበትን ምንጣፍ ተሸክመህ ሂድ» ያለህ ሰው ማን ነው?» ብለው ጠየቁት።
13የተፈወሰው ሰው ግን ኢየሱስ ከአጠገቡ ፈቀቅ ስላለና በስፍራው ብዙ ሕዝብ ስለ ነበር፣ ማን እንደ ፈወሰው አላወቀም።
14በኋላ ኢየሱስ ያን ሰው በቤተ መቅደስ አግኝቶት፣ «እነሆ፣ ተፈውሰሃል፤ ከዚህ የባሰ ነገር እንዳይደርስብህ ከእንግዲህ ኀጢአት አትሥራ» አለው።
15ሰውየው ሄዶ የፈወሰው ኢየሱስ መሆኑን ለአይሁድ መሪዎች ነገራቸው።
16ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች በሰንበት ስላደረገ፣ የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር።
17ኢየሱስ፣ «አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም እሠራለሁ» አላቸው።
18በዚህ ምክንያት አይሁድ ኢየሱስ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን አባቴ ነው በማለት፣ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ስላደረገ፣ ሊገድሉት አጥብቀው ይፈልጉ ነበር።
19ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው፤ «እውነት እላችኋለሁ፣ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድም ያንኑ ያደርጋልና።
20አብ ወልድን ይወዳልና፣ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ነገር ያሳየዋል።
21አብ ሙታንን እንደሚያስነሣና ሕይወትንም እንደሚሰጣቸው፣ ወልድም ደግሞ ለሚፈልገው ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል።
22አብ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ነገር ግን ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጥቶታል፤
23ይኸውም፣ ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ ወልድን የማያከብር፣ የላከውን አብንም አያከብርም።
24እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ፣ በላከኝም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ አይፈረድበትም።
25እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእኔን፣ የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜ እየመጣ ነው፤ አሁንም መጥቶአል፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።
26አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው ሁሉ፣ ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና፤
27ወልድ የሰው ልጅ ስለ ሆነ፣ አብ የመፍረድን ሥልጣን ለወልድ ሰጥቶታል።
28በዚህ አትደነቁ፤ በመቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤
29መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩም ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።
30እኔ ከራሴ ምንም ማድረግ አልችልም፤ የምፈርደው በሰማሁት መሠረት ነው፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ የራሴን ፈቃድ ስለማልሻም፣ ፍርዴ ትክክል ነው።
31እኔው ስለ ራሴ ብመሰክር፣ ምስክርነቴ እውነት አይደለም።
32ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ አለ፤ እርሱ ስለ እኔ የሚሰጠውም ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ ዐውቃለሁ።
33ወደ ዮሐንስ ልካችሁ ነበር፤ እርሱም ስለ እውነት መስክሮአል፤
34ይሁን እንጂ፣ እኔ የሰው ምስክርነት የምቀበል አይደለሁም፤ ነገር ግን ይህን የምናገረው እናንተ እንድትድኑ ነው።
35ዮሐንስ እየነደደ ብርሃን የሚሰጥ መብራት ነበረ፤ እናንተም ለጥቂት ጊዜ በብርሃኑ ሐሤት ልታደርጉ ፈለጋችሁ።
36እኔ ያለኝ ምስክርነት ግን ከዮሐንስ ምስክርነት ይበልጣል፡፡ አብ እንድፈጽመው የሰጠኝ፣ እኔም እየሠራሁት ያለሁት ሥራ አብ እንደ ላከኝ ይመሰክራል።
37የላከኝ አብ እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል፤ እናንተም ከቶ ድምፁን አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም፤
38እርሱ በላከው አላመናችሁምና ቃሉ በእናንተ አይኖርም።
39በእነርሱ የዘላለምን ሕይወት የምታገኙ ስለሚመስላችሁ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ ይመሰክራሉ፤
40እናንተ ወደ እኔ መጥታችሁ ሕይወት ማግኘት አትፈልጉም።
41እኔ ከሰው ክብር አልቀበልም፤
42ነገር ግን የእግዚአብሔር ፍቅር በእናንተ ውስጥ እንደሌለ ዐውቃለሁ።
43እኔ በአባቴ ስም መጥቼ አልተቀበላችሁኝም፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ ግን ትቀበሉታላችሁ።
44እናንተ አንዳችሁ ከሌላችሁ ክብር የምትቀበሉ፣ ነገር ግን ከአንዱ አምላክ የሚመጣውን ክብር የማትሹ ከሆነ፣ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ?
45በአብ ፊት የምከሳችሁ እኔ አልምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ ሌላ አለ እርሱም ተስፋ ያደረጋችሁበት ሙሴ ነው።
46ሙሴን ብታምኑ ኖሮ፣ እኔን ባመናችሁ ነበር፤ ምክንያቱም እርሱም የጻፈው ስለ እኔ ነው።
47ታዲያ እርሱ የጻፈውን ካላመናችሁ፣ ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?»
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።