መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዮሐንስ 4

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ፈሪሳውያን ኢየሱስ ከዮሐንስ የበለጠ ብዙ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንደሚያደርግና እንደሚያጠምቅ ሰሙ፤ ኢየሱስም ይህን ዐወቀ፤
2(ያጠምቁ የነበሩት ደቀ መዛሙርቱ እንጂ እርሱ ባይሆንም)፣ ኢየሱስ መስማታቸውን ባወቀ ጊዜ
3የይሁዳን ምድር ለቅቆ ወደ ገሊላ ሄደ።
4በሰማርያም በኩል ማለፍ ነበረበት።
5ከዚያም በሰማርያ ከተማ፣ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ቦታ አጠገብ ወደምትገኝ፣ ሲካር ወደምትባል ቦታ መጣ።
6በዚያም የያዕቆብ የውሃ ጒድጓድ ነበረ፤ ኢየሱስ ከጒዞው ብዛት ደክሞት ስለ ነበር፣ በውሃው ጒድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም እኩለ ቀን አካባቢ ነበር።
7አንዲት ሳምራዊት ሴት ውሃ ልትቀዳ ስትመጣ፣ ኢየሱስ፣ «እባክሽ የምጠጣው ውሃ ስጪኝ» አላት።
8ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ለመግዛት ወደ ከተማ ሄደው ነበር።
9ሳምራዊቷም ሴት፣ «አንተ አይሁዳዊ ሆነህ፣ እኔን ሳምራዊቷን ሴት እንዴት ውሃ አጠጪኝ ትለኛለህ?» አለችው። አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና።
10ኢየሱስ፣ «የእግዚአብሔርን ስጦታና ውሃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን እንደሆነ ዐውቀሽ ቢሆን ኖሮ ፣ አንቺው በጠየቅሽው፣ እርሱም ሕያው ውሃ በሰጠሽ ነበር» ብሎ መለሰላት።
11ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ «ጌታ ሆይ፣ አንተ መቅጃ የለህም፤ ጒድጓዱም ጥልቅ ነው፤ ታዲያ ሕያዉን ውሃ ከየት ታገኛለህ?
12አንተ፣ ይህን ጒድጓድ ከሰጠን፣ ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እርሱ ራሱ፣ ልጆቹና ከብቶቹም ከዚሁ ጒድጓድ ጠጥተዋል።
13ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰላት፤ «ከዚህ ውሃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤
14እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ግን ፈጽሞ ዳግመኛ አይጠማም፤ ይልቁንም፣ እኔ የምሰጠው ውሃ፣ ከውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት ውሃ ምንጭ ይሆናል።»
15ሴትዮዋም፣ «ጌታዬ፤ ከእንግዲህ እንዳልጠማና ውሃ ለመቅዳት ወደዚህ እንዳልመጣ፣ ይህን ውሃ ስጠኝ» አለችው።
16ኢየሱስም፣ «ሂጂ፣ ባልሽን ጥሪና ወደዚህ ተመልሰሽ ነይ» አላት።
17ሴትዮዋ፣ «ባል የለኝም» በማለት መለሰች፤ ኢየሱስ፣ 'ባል የለኝም' በማለትሽ ልክ ነሽ፤
18አምስት ባሎች ነበሩሽና፤ አሁን ከአንቺ ጋር ያለው ሰው ባልሽ አይደለም፤ ስለዚህ እውነቱን ተናግረሻል» ብሎ መለሰ።
19ሴትዮዋ፣ «ጌታ ሆይ፣ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ ይገባኛል፤
20አባቶቻችን በዚህ ተራራ ላይ ሰገዱ፤ እናንተ ግን ሰው መስገድ ያለበት በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ» አለችው።
21ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰላት፤ «አንቺ ሴት፣ በዚህ ተራራም ሆነ በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ እየመጣ መሆኑን እመኚኝ።
22እናንተ ሳምራውያን ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ። እኛ ግን፣ ድነት ከአይሁድ ስለ ሆነ፣ ለምናውቀው እንሰግዳለን።
23ይሁን እንጂ፣ በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ እየመጣ ነው፤ አሁንም መጥቶአል፤ አብ እንደዚህ በእውነት የሚሰግዱለትን ሰዎች ይፈልጋልና።
24እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል።»
25ሴትዮዋ፣ «ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንደሚመጣ ዐውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉንም ነገር ይነግረናል» አለችው።
26ኢየሱስ፣ «አሁን እያነጋገርሁሽ ያለሁት እኔ እርሱ ነኝ» አላት።
27ልክ በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው መጡ፤ ኢየሱስ ከሴት ጋር በመነጋገሩ ተገረሙ፤ ይሁን እንጂ፣ ማንም፣ «ምን ትፈልጋለህ? ወይም ከእርስዋ ጋር ለምን ትነጋገራለህ?» ያለው የለም።
28ሴትዮዋ እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ተመለሰች፤ ለሕዝቡም፣
29«ያደረግሁትን ነገር ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?» አለች፤
30ሕዝቡ ከከተማ ወጥተው እርሱ ወዳለበት መጡ።
31በዚህም መሐል ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን፣ «መምህር ሆይ፣ ምግብ ብላ» አሉት።
32እርሱ ግን፣ «እናንተ የማታውቁት፣ የምበላው ምግብ አለኝ» አላቸው።
33ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ እርስ በርስ፣ «ምግብ ያመጣለት ሰው ይኖር ይሆን?» ተባባሉ።
34ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ «የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውንም መፈጸም ነው።
35እናንተ 'መከር ገና አራት ወር ቀርቶታል፤ ከዚያም መከሩ ይመጣል' ትሉ የለምን? ቀና በሉና ዕርሻዎቹን ተመልከቱ፣ መከሩ ደርሷልና እያልኋችሁ ነው፤
36የሚያጭድ ደመወዙን ይቀበላል፤ ለዘላለም ሕይወት የሚሆን ፍሬም ይሰበስባል፤ ስለዚህ የሚዘራውም፣ የሚያጭደውም አብረው ይደሰታሉ።
37'አንዱ ይዘራል፣ ሌላውም ያጭዳል' የሚለው አባባል እውነት የሚሆነው በዚህ ምክንያት ነው።
38እኔ ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ፤ ሌሎች በሥራ ደከሙ፤ እናንተም በእነርሱ ሥራ ገባችሁ።»
39ሴትዮዋ፣ «ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ» ብላ ስለ እርሱ በሰጠችው ምስክርነት የተነሣ፣ በዚያች ከተማ ከሚኖሩ ሳምራውያን ብዙዎቹ በእርሱ አመኑ።
40ስለዚህ፣ ሳምራውያኑ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ፣ ከእነርሱ ጋር እንዲቈይ ለመኑት፤ እዚያም ሁለት ቀን ቈየ።
41ከቃሉም የተነሣ ሌሎች ብዙ ሰዎች አመኑ።
42ሴትዮዋንም፣ «የምናምነው አንቺ ስለ ነገርሽን ቃል ብቻ አይደለም፤ እኛ ራሳችን ሰምተነዋል፤ ይህ ሰው በእውነት የዓለም አዳኝ እንደ ሆነ እናውቃለን» ይሏት ነበር።
43ከእነዚያ ሁለት ቀናት በኋላም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ገሊላ ሄደ።
44ነቢይ በገዛ አገሩ እንደማይከበር ኢየሱስ ራሱ ተናግሮ ነበርና።
45ወደ ገሊላ በደረሰ ጊዜ፣ የገሊላ ሰዎች በደስታ ተቀበሉት፤ እነርሱ በፋሲካ በዓል ወደዚያ ሄደው ስለ ነበር፣ በኢየሩሳሌም ያደረጋቸውን ነገሮች ሁሉ አይተው ነበር። እነርሱ ደግሞ ወደ በዓሉ ሄደው ነበርና።
46ኢየሱስም ውሃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገባት፣ በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ቃና ከተማ ዳግመኛ መጣ፤ በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት አንድ ከንጉሣዊ ቤተ ሰብ የሆነ ሹም ነበር፤
47እርሱም ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መምጣቱን በሰማ ጊዜ፣ ወደ እርሱ ሄደና በሞት አፋፍ ላይ የሚገኘውን ልጁን መጥቶ እንዲፈውስለት ለመነው።
48ከዚያም ኢየሱስ፣ «እናንተ ሰዎች ምልክቶችንና ድንቆችን ካላያችሁ አታምኑም» አለው።
49ሹሙ፣ «ጌታ ሆይ፤ ልጄ ከመሞቱ በፊት እባክህ ውረድ» አለው።
50ኢየሱስ፣ «ሂድ፤ ልጅህ በሕይወት ይኖራል» አለው። ሰውየው ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አምኖ ሄደ።
51በመንገድ ላይ ሳለም፣ አገልጋዮቹ አገኙትና ልጁ ተሽሎት በሕይወት እንዳለ ነገሩት።
52እርሱም ልጁ የተሻለው በስንት ሰዓት ላይ እንደ ነበረ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ «ትኵሳቱ የለቀቀው ትናንት በሰባተኛው ሰዓት ላይ ነበር» አሉት።
53አባትየውም፣ ኢየሱስ «ልጅህ በሕይወት ይኖራል» ብሎት የነበረው በዚያ ሰዓት እንደ ነበረ ተገነዘበ፤ ስለዚህ እርሱ ራሱና ቤተ ሰቡ በሙሉ በኢየሱስ አመኑ።
54ይህም ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ በመጣ ጊዜ ያደረገው ሁለተኛው ምልክት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።