1በሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ገና ጨለማ እያለ መግደላዊት ማርያም በሌሊት ወደ መቃብሩ መጣች፤ ድንጋዩ ከመቃብሩ ተንከባሎ አየች።
2ስለዚህ ወዲያው እየሮጠች ተመልሳ ወደ ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ደቀ መዝሙር መጥታ፣ «ጌታን ከመቃብሩ አውጥተው ወስደውታል፣ የት እንዳደረጉትም አናውቅም» አለቻቸው።
3ከዚያም ጴጥሮስና ሌላኛው ደቀ መዝሙር ወደ መቃብሩ ሄዱ።
4አብረው እየሮጡ ሳለ፣ ሌላኛው ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን ቀድሞ ወደ መቃብሩ ደረሰ።
5ጐንበስ ብሎ ወደ ውስጥ ሲመለከት፣ የበፍታ ጨርቁ ተቀምጦ አየ፣ ወደ ውስጥ ግን አልገባም።
6ከእርሱም በኋላ ጴጥሮስ ደረሰና ወደ መቃብሩ ውስጥ ገባ። የበፍታ ጨርቁ ተቀምጦ አየ፣
7በኢየሱስ ራስ ላይ የነበረውንም ጨርቅ ከበፍታ ጨርቁ ጋር ዐብሮ ሳይሆን ለብቻው እንደ ተጠቀለለ በቦታው ተቀምጦ አየ።
8ከዚያም ጴጥሮስ ቀድሞ ወደ መቃብሩ ደርሶ የነበረው ደቀ መዝሙር ወደ ውስጥ ገባና አይቶ አመነ።
9ምክንያቱም እስከዚያን ሰዓት ድረስ ኢየሱስ ከሞት እንደሚነሣ በመጻሕፍት የተነገረውን ቃል አላስተዋሉም ነበር።
10ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ ወደየቤታቸው ሄዱ።
11ነገር ግን መግደላዊት ማርያም እያለቀስች ከመቃብሩ ውጭ ቆማ ነበር፤ እያለቀሰችም ጐንበስ ብላ ወደ መቃብሩ ውስጥ ተመለከተ።
12የኢየሱስ አስከሬን ተጋድሞበት በነበረው ቦታ ላይ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት፣ አንደኛው በራስጌ፣ ሌላው ደግሞ በእግርጌ ተቀምጠው አየች።
13እነርሱም፣ «አንቺ ሴት፣ ለምን ታለቅሻለሽ?» አሏት፤ እርሷም፣ «ጌታዬን ስለወሰዱትና ወዴትም እንዳኖሩት ስለማላውቅ ነው።» አለቻቸው።
14ይህን ብላ ዞር ስትል፣ ኢየሱስን እዚያው ቆሞ አየችው፤ እርሱ እንደ ሆነ ግን አላወቀችም ነበር።
15ኢየሱስ፣ «አንቺ ሴት ለምን ታለቅሽያለሽ፣ ማንንስ እየፈለግሽ ነው?» አላት። እርሷም የአትክልት ስፍራው ጠባቂ መስሏት፣ «ጌታዬ የወሰድኸው አንተ ከሆንህ እባክህ የት እንዳስቀመጥኸው ንገረኝና ልውሰደው።» አለችው።
16ኢየሱስም፣ «ማርያም» አላት። ዞር ብላ በአረማይክ ቋንቋ፣ «ረቡኒ» አለችው፤ ትርጓሜውም «መምህር» ማለት ነው።
17ኢየሱስም«ገና ወደ አብ አልሄድሁምና አትንኪኝ፣ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ መሄዴ ነው ብለሽ ንገሪአቸው» አላት።
18መግደላዊት ማርያምም ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥታ፣ «ጌታን አየሁት» ብላ ኢየሱስ የነገራትን ሁሉ ነገረቻቸው።
19በዚያው ቀን ማለትም ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ምሽት ላይ፣ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን ፈርተው በሮቹ ተዘግተው ሳለ ኢየሱስ በመካከላቸው ቆሞ፣ «ሰላም ለእናንተ ይሁን» አላቸው።
20ይህንም ብሎ እጁንና ጐኑን አሳያቸው። ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩት ጊዜ፣ ደስ አላቸው።
21እንደ ገናም ኢየሱስ፣ «ሰላም ለእናንተ ይሁን፣ አብ እንደ ላከኝ እኔም እልካችኋለሁ» አላቸው።
22ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና፣ «መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፣
23ኀጢአቱን ይቅር ያላችሁት ማንም ይቅር ይባልለታል፣ ኀጢአቱን የያዛችሁበት ማንም ይያዝበታል» አላቸው።
24ኢየሱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ በመጣ ጊዜ፣ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ሌላ ስሙ ዲዲሞስ የሚባለው ቶማስ ዐብሮአቸው አልነበረም።
25ኋላ ላይ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት፣ «ጌታን አየነው እኮ» አሉት። እርሱም፣ «የምስማር ምልክቱን በእጆቹ ላይ ካላየሁ፣ ጣቶቼንም በምስማር ምልክቱና እጄን በጐኑ ካላስገባሁ አላምንም» አላቸው።
26ከስምንት ቀን በኋላ ደቀ መዛሙርቱ በቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ዐብሯቸው ነበረ። በሮቹ ተዘግተው ሳለ ኢየሱስ በመካከላቸው ቆሞ፣ «ሰላም ለእናንተ ይሁን» አላቸው።
27ቶማስንም፣ «ጣቶችህን አምጣና እጆቼን ንካ፣ እጆችህንም ወደ ጐኔ አስገባ፣ እመን እንጂ የማታምን አትሁን» አለው።
28ቶማስም፣ «ጌታዬና አምላኬ» ብሎ መለሰለት።
29ኢየሱስ «አንተ ስላየኸኝ አመንህ፣ ሳያዩ የሚያምኑ የተባረኩ ናቸው» አለው።
30ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ብዙ ምልክቶችን በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤
31ነገር ግን ይህ የተጻፈው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እንድታምኑና አምናችሁም በስሙ ሕይወት እንድታገኙ ነው።