1እነዚህ ነገሮች ከተፈጸሙ በኋላ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ገና በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ተገለጠላቸው፤ ሁኔታውም እንደዚህ ነበር፦
2ስምዖን ጴጥሮስ ዲዲሞስ ከተባለው ከቶማስ፣ ከገሊላ አውራጃ ከቃና መንደር ከሆነው ከናትናኤል፣ ከዘብዴዎስ ልጆችና ከሌሎች ሁለት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጋር ዐብረው ነበሩ።
3ስምዖን ጴጥሮስ፣ «ዓሣ ለማጥመድ መሄዴ ነው» አላቸው። እነርሱም፣ «እኛም ከአንተ ጋር እንሄዳለን» አሉት። በጀልባ ተሳፍረው ሄዱ፤ ነገር ግን በዚያች ሌሊት ምንም ዐሣ አላጠመዱም።
4ቀኑ እየነጋ ሳለ ኢየሱስ መጥቶ በባሕሩ ዳር ቆመ፤ እነርሱ ግን ኢየሱስ እንደ ሆነ አላወቁም ነበር።
5ከዚያም ኢየሱስ «ልጆች ሆይ፣ የሚበላ ዐሣ አላችሁን?» አላቸው። «የለንም» ብለው መለሱለት።
6ኢየሱስ፣ «መረባችሁን ከጀልባው በቀኝ በኩል ጣሉት ታገኙማላችሁ» አላቸው። እነርሱም እንደተባሉት መረባቸውን ጣሉ፤ ነገር ግን ከዐሣው ብዛት የተነሣ መረቡን ወደ ጀልባው ውስጥ መጐተት አቃታቸው።
7ከዚያም ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር ስምዖን ጴጥሮስን፣ «ጌታ እኮ ነው» አለው። ጴጥሮስ ጌታ እኮ ነው የሚለውን ቃል በሰማ ጊዜ፣ መደረቢያውን ልብስ ታጥቆ ወደ ውሃው ውስጥ ዘሎ ገባ።
8ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር የነበራቸው ርቀት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር ዐሣ የሞላውን መረብ እየጐተቱ በጀልባ ወደ ዳር መጡ።
9ወደ መሬትም በደረሱ ጊዜ፣ በላዩ ላይ ዐሣ የተቀመጠበት ፍምና እንጀራ ተዘጋጅቶ አዩ።
10ኢየሱስ፣ «እስኪ ካጠመዳችሁት ዐሣ ጥቂት ወደዚህ አምጡ» አላቸው።
11ስምዖን ጴጥሮስም ሄዶ 153 ዐሣ የሞላውን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ምንም እንኳ የዐሣው ብዛት ከፍተኛ ቢሆንም፣ መረቡ ግን አልተቀደደም ነበር።
12ኢየሱስ፣ «ኑ ቍርስ ብሉ» አላቸው። ኢየሱስ እንደ ሆነ አውቀው ነበርና ከደቀ መዛሙርቱ ማንም፣ «አንተ ማነህ?» ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም።
13ኢየሱስ እንጀራውን አንሥቶ ሰጣቸው፤ ዐሣውንም እንደዚያው አደረገ።
14ከሞት ከተነሣ በኋላ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥላቸው ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነበር።
15ቍርስ ከበሉ በኋላ፣ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፣ «የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ ከእነዚህ የበለጠ ትወደኛለህን?» አለው። ጴጥሮስ፣ «አዎን፣ ጌታ ሆይ፣ እንደምወድህማ አንተም ታውቃለህ» አለው። ኢየሱ፣ «ጠቦቶቼን መግብ» አለው።
16እንደ ገና ለሁለተኛ ጊዜ፣ «የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን?» አለው። ጴጥሮስ፣ «አዎን፣ ጌታ ሆይ፣ እንደምወድህማ አንተም ታውቃለህ» አለው። ኢየሱስ፣ «በጎቼን ጠብቅ» አለው።
17ለሦስተኛ ጊዜ፣ «የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ ትወደኛለህ?» አለው። ለሦስተኛ ጊዜ «ትወደኛለህ ወይ?» ብሎ ስለ ጠየቀው ጴጥሮስ በጣም ዐዘነ። ቀጥሎም፣ «ጌታ ሆይ፣ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንደምወድህም ታውቃለህ» አለው። ኢየሱስም «በጎቼን መግብ።
18እውነት፣ እውነት እልሃለሁ፣ ወጣት እያለህ ልብስህን ራስህ ለብሰህ ወደምትፈልገው ቦታ ትሄድ ነበር፤ ስታረጅ ግን ሌላ ሰው ልብስህን አልብሶህ ወደማትፈልገው ቦታ ይወስድሃል፣ በዚያን ጊዜ አንተ እጅህን ከመዘርጋት ውጪ ሌላ ማድረግ የምትችለው ነገር አይኖርም» አለው።
19ኢየሱስ ይህን የተናገረው ጴጥሮስ በምን ዓይነት አሟሟት እግዚአብሔርን እንደሚያከብር ለማመልከት ነው። ከዚያም ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ «ተከተለኝ» አለው።
20ጴጥሮስም ዞር ብሎ በፋሲካ እራት ላይ እያሉ ወደ ኢየሱስ ደረት ጠጋ ብሎ፣ «አሳልፎ የሚስጥህ ማን ነው?» ብሎ የጠየቀውንና ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀ መዝሙር ሲከተላቸው አየው።
21ጴጥሮስ ኢየሱስን፣ «ጌታ ሆይ፣ ይህ ሰውስ ምን ይሆናል?» አለው።
22ኢየሱስ፣ «እኔ እስክመጣ እንዲቆይ ብፈልግስ አንተን ምን ይመለከትሃል? ዝም ብለህ ተከተለኝ» አለው።
23በዚህ ምክንያት «ያ ደቀ መዝሙር አይሞትም» የሚል ወሬ በየ ስፍራው ተሠራጨ። ኢየሱስ ግን ለጴጥሮስ፣ «እኔ እስክመጣ እንዲቆይ ብፈልግስ አንተን ምን ይመለከትሃል?» አለው እንጂ ያ ደቀ መዝሙር አይሞትም አላለውም።
24ስለ እነዚህ ነገሮች የመሰከረውና የጻፈው ይህ ደቀ መዝሙር ነው፣ ምስክርነቱም እውነት እንደ ሆነ እናውቃለን።
25ከእነዚህ ሌላ ኢየሱስ ያደረጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ። እያንዳንዱ ነገር ቢጻፍ ኖሮ ለሚጻፉት መጻሕፍት ማስቀመጫ ዓለም እንኳ የሚበቃ አይመስለኝም።