1ከዚያም ጲላጦስ ኢየሱስን ወስዶ አስገረፈው።
2ወታደሮቹ የእሾኽ አክሊል ጐንጕነው በኢየሱስ ራስ ላይ አደረጉ። ሐምራዊ ልብስም አለበሱት።
3ወደ እርሱ መጥተው፣ «የተከበሩ የአይሁድ ንጉሥ ሆይ!» አሉ በጥፊም መቱት።
4ከዚያም ጲላጦስ እንደ ገና ወደ ወጥቶ ሕዝቡን፣ «ምንም ጥፋት እንዳላገኘሁበት እንድታውቁ እነሆ፣ ሰውየውን ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ» አላቸው።
5ስለዚህ ኢየሱስ የእሾኽ አክሊል ደፍቶና ሐምራዊ ልብስ ለብሶ ወደ ውጭ ወጣ። ጲላጦስም፣ «እነሆ፣ ሰውየው!» አላቸው።
6የካህናት አለቆችና ጠባቂዎቹ ኢየሱስን ባዩ ጊዜ፣ «ስቀለው፣ ስቀለው» እያሉ ጮኹ። ጲላጦስ፣ «እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት፤ እኔ ምንም ወንጀል አላገኘሁበትም» አላቸው።
7አይሁድ፣ «እኛ ሕግ አለን፣ በሕጋችን መሠረትም ይህ ሰው ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጓልና ሞት ይገባዋል» ብለው መለሱ።
8ጲላጦስ ይህን ሲሰማ የበለጠ ደነገጠ፤
9ወደ ግቢውም ተመልሶ ኢየሱስን፣ «ከየት ነው የመጣኸው?» ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም።
10ጲላጦስም ኢየሱስን፣ «አናግረኝ እንጂ፤ ልፈታህም ሆነ ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅም እንዴ?» አለው።
11ኢየሱስ፣ «ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልኖረህ ነበር። ስለዚህም ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ኀጢአቱ የከፋ ነው» አለው።
12ከዚህ መልሱ የተነሣ ጲላጦስ ሊፈታው ፈለገ፣ ነገር ግን አይሁድ፣ «ራሱን ንጉሥ ብሎ የሚጠራ ቄሣርን የሚቃወም ስለ ሆነ፣ ይህን ሰው ብትለቀው አንተ የቄሣር ወዳጅ አይደለህም» እያሉ ይጮኹ ነበር።
13ጲላጦስ እነዚህን ቃላት በሰማ ጊዜ ኢየሱስን ወደ ውጭ አውጥቶ የድንጋይ ንጣፍ፣ በዕብራይስጥ ግን ገበታ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀመጠ።
14ቀኑ ለፋሲካ በዓል ዝግጅት የሚደረግበትና ሰዓቱም ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ ነበር። ጲላጦስ አይሁድን፣ «እነሆ፣ ንጉሣችሁ» አላቸው።
15እነርሱም፣ «አስወግደው፣ አስወግደው፣ ስቀለው!» እያሉ ጮኹ። እርሱ፣ «ንጉሣችሁን ልስቀለውን?» አላቸው። የካህናት አለቆችም፣ «እኛ ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ አናውቅም» ብለው መለሱለት።
16ስለዚህ ጲላጦስ ኢየሱስን እንዲሰቅሉት ፈቀደላቸው።
17ከዚያም ኢየሱስን፣ የሚሰቀልበትን መስቀል አሸክመው የራስ ቅል፣ በዕብራይስጥ ደግሞ ጎልጎልታ ወደሚባል ቦታ ወሰዱት።
18በዚያም ስፍራ ሰቀሉት፤ ሁለት ሌሎች ሰዎችንም በኢየሱስ ግራና ቀኝ ሰቀሉ።
19ጲላጦስም ጽሑፍ አዘጋጅቶ በኢየሱስ መስቀል ላይ አስቀመጠ። ጽሑፉም፣ «የናዝሬቱ ኢየሱስ፣ የአይሁድ ንጉሥ» የሚል ነበር።
20ኢየሱስ የተሰቀለበት ቦታ ለከተማው ቅርብ ስለ ነበር፣ ብዙ አይሁድ ጽሑፉን ያነቡት ነበር። ጽሑፉም የተጻፈው በዕብራይስጥ፣ በላቲንና በግሪክ ቋንቋዎች ነበር።
21የአይሁድ የካህናት አለቆችም ጲላጦስን «እርሱ ራሱን 'የአይሁድ ንጉሥ ነኝ' ብሏል ብለህ ነው እንጂ፣ 'የአይሁድ ንጉሥ' ብለህ መጻፍ የለብህም» አሉት።
22ጲላጦስም፣ «አንዴ የጻፍሁትን ጽፌአለሁ» አላቸው።
23ወታደሮቹ ኢየሱስን ከሰቀሉት በኋላ ልብሱን ወስደው ለእያንዳንዳቸው እንዲዳረስ አድርገው አራት ቦታ ቈራረጡት፣ እጀ ጠባቡንም ወሰዱ።
24እጀ ጠባቡ ግን ከላይ ጀምሮ ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበረና እርስ በርሳቸው «ከምንቀደው ዕጣ እንጣጣልና የሚደርሰው ይውሰደው» ተባባሉ። ይህም የሆነው በቅዱስ መጽሐፍ፣ «ልብሴን ተከፋፈሉት በእጀ ጠባቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉበት» የተባለው ቃል እንዲፈጸም ነው።
25ወታደሮቹ ይህን በሚያደርጉበት ጊዜ የኢየሱስ እናት ማርያም፣ የእናቱ እኅት፣ የቀለዮጳ ሚስት ማርያምና መግደላዊት ማርያም በዚያ በኢየሱስ መስቀል አጠገብ ቆመው ነበር።
26ኢየሱስ እናቱንና ይወደው የነበረውን ደቀ መዝሙር አብረው ቆመው ባየ ጊዜ፣ እናቱን «አንቺ ሴት እነሆ፣ ከአጠገብሽ ያለው እንደ ልጅሽ ይሁንልሽ» አላት ፤
27ደቀ መዝሙሩንም፣ «እነኋት፣ በአጠገብህ ያለችው እንደ እናትህ ትሁንልህ» አለው። ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት።
28ኢየሱስ ሁሉ እንደ ተፈጸመ ዐውቆ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈው እንዲፈጸም፣ «ተጠማሁ» አለ።
29በዚያም በሆምጣጤ የተሞላ ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ ወዲያውም በሆምጣጤ የተሞላ ሰፍነግ በሂሶጵ ወደ አፉ አስጠጉለት።
30ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከጠጣ በኋላ «ተፈጸመ» አለ። ራሱንም አዘንብሎ ሞተ።
31ቀኑ የመዘጋጀት ቀን በመሆኑና ሰንበትም በአይሁድ ዘንድ በጣም የሚከበር ስለነበረ በሰንበት ሥጋቸው በመስቀል ላይ መቆየት ስለሌለበት የሞት ፍርድ የተፈጸመባቸው ሰዎች እግሮቻቸው እየተሰበረ ሥጋቸው ከመስቀል እንዲወርድ አይሁድ ጲላጦስን ለመኑት።
32ከዚያም ወታደሮቹ መጥተው ከኢየሱስ ጋር ከተሰቀሉት ሰዎች በመጀመሪያ የአንዱን፣ ቀጥሎም የሌላኛውን ሰው እግሮች ሰበሩ።
33ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን ሞቶ ስላገኙት እግሮቹን አልሰበሩም።
34ይሁን እንጂ፣ ከወታደሮቹ አንዱ ጐኑን በጦር ወጋው፣ ወዲያውም ከጐኑ ደምና ውሃ ወጣ።
35ይህን ያየው ሰው ስለዚህ መስክሯል፣ ምስክርነቱም እውነት ነው። እናንተም እንድታምኑ የተናገረው እውነት እንደ ሆነ ያውቃል።
36እነዚህ ነገሮች የሆኑት «ከዐጥንቱ አንድም አይሰበርም» የሚለው የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው።
37ደግሞም በሌላ መጽሐፍ፣ «የወጉትን ያዩታል» ተብሎ ተጽፎአል።
38ከእነዚህ ነገሮች በኋላ አይሁድን ፈርቶ በድብቅ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረውና ከአርማትያስ ከተማ የሆነው ዮሴፍ የኢየሱስን አስከሬን ለመውሰድ ጲላጦስን ለመነ። ጲላጦስም ፈቀደለት። ዮሴፍም መጥቶ የኢየሱስን አስከሬን ወሰደ።
39በአንድ ወቅት በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስም አንድ መቶ ነጥር ያህል የእሬትና የከርቤ ቅልቅል ይዞ መጣ።
40ስለዚህ የኢየሱስን አስከሬን ወስደው በአይሁድ ባህል አስከሬን ከመቀበሩ በፊት እንደሚደረገው ልማድ አስከሬኑን ሽቱ በተቀባ በበፍታ ጨርቅ ገነዙት።
41ኢየሱስ ከተቀበረበት ቦታ አጠገብ የአትክልት ስፍራ ነበረ፤ በዚያም ማንም ገና ያልተቀበረበት ዐዲስ መቃብር ይገኝ ነበረ።
42ቀኑ ለአይሁድ የመዘጋጀት ቀን በመሆኑና መቃብሩም ቅርብ ስለ ነበር፣ የኢየሱስን አስከሬን በዐዲሱ መቃብር አኖሩት።