1በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፤ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች።
2ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ተጠርተው ነበር፡፡
3የወይን ጠጁ ባለቀ ጊዜ፣ የኢየሱስ እናት ኢየሱስን፣ «የወይን ጠጅ እኮ ዐልቆባቸዋል» አለችው፡፡
4ኢየሱስ መልሶ፣ «አንቺ ሴት፣ ከዚህ ጋር እኔ ምን ጉዳይ አለኝ? ጊዜዬ እኮ ገና አልደረሰም» አላት፡፡
5እናቱ ለአሳላፊዎቹ፣ እርሱ «የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ» አለቻቸው፡፡
6በዚያ፣ ለአይሁድ የመንጻት ሥርዐት የሚያገለግሉ እያንዳንዳቸው ሁለት ወይም ሦስት እንስራ የሚይዙ ስድስት የድንጋይ ጋኖች ነበሩ፡፡
7ኢየሱስ፣ «ጋኖቹን ውሃ ሙሉአቸው» አላቸው፡፡ እነርሱም እስከ አፋቸው ሞሉአቸው፡፡
8ከዚያም ኢየሱስ አሳላፊዎቹን፣ «ጥቂት ቅዱና ለመስተንግዶው ኀላፊ ስጡት» አላቸው፤ እነርሱም እንዳላቸው አደረጉ፡፡
9የመስተንግዶው ኀላፊ፣ ወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ ቀመሰው፤ ከየት እንደ መጣ ግን አላወቀም፤ ውሃውን የቀዱት አሳላፊዎች ግን ያውቁ ነበር፡፡ እርሱም ሙሽራውን ጠርቶ
10«ሰው ሁሉ መልካሙን ወይን ጠጅ በመጀመሪያ ያቀርባል፤ መናኛውን ሰዎች ከሰከሩ በኋላ ነው የሚያቀርበው፤ አንተ ግን መልካሙን የወይን ጠጅ እስካሁን ድረስ አቈይተሃል» አለው፡፡
11ይህ በገሊላ ቃና የተደረገው ተአምር ኢየሱስ ካደረጋቸው ተአምራዊ ምልክቶች የመጀመሪያ ነው፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።
12ከዚህ በኋላ ከእናቱ፣ ከወንድሞቹና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፤ በዚያም ጥቂት ቀናት ቈዩ፡፡
13የአይሁድ ፋሲካ ቀርቦ ስለ ነበረ፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡
14በቤተ መቅደስ ውስጥ በሬዎችን፣ በጎችንና ርግቦችን ሲሸጡ የነበሩ ሰዎችን አገኘ፡፡ ገንዘብ ለዋጮችም ደግሞ በዚያ ተቀምጠው ነበር፡፡
15እርሱም የገመድ ጅራፍ አበጅቶ በጎችንና ከብቶችን ጭምር ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣቸው፤ የገንዘብ ለዋጮችንም ገንዘብ በተነ፤ ጠረጴዛዎቻቸውንም ገለባበጠ።
16ርግብ ሻጮችንም፣ «እነዚህን ከዚህ አስወጧቸው፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት ማድረጋችሁን አቁሙ!» አላቸው።
17ደቀ መዛሙርቱ፣ «ለቤትህ ያለኝ ቅናት ይበላኛል» ተብሎ የተጻፈውን አስታወሱ፡፡
18ከዚያም የአይሁድ ባለ ሥልጣኖች፣ «እነዚህን ነገሮች ለማድረግ መብት እንዳለህ ምን ምልክት ታሳየናለህ?» በማለት መለሱለት፡፡
19ኢየሱስ፣ «ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ እኔ በሦስት ቀን አስነሣዋለሁ» ብሎ መለሰ፡፡
20ከዚያም አይሁድ፣ «ይህን ቤተ መቅደስ ለመገንባት ዐርባ ስድስት ዓመት ፈጅቶአል፤ አንተ በሦስት ቀን መልሰህ ታስነሣዋለህ?» አሉት።
21ይሁን እንጂ፣ እርሱ ቤተ መቅደስ ብሎ የተናገረው፣ ስለ ራሱ ሰውነት ነበር።
22ከሙታን ከተነሣም በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ይህን እንደ ተናገረ አስታወሱ፤ መጻሕፍትንና ኢየሱስ የተናገረውንም ቃል አመኑ።
23በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ፣ ያደረጋቸውን ተአምራት አይተው ብዙዎች በስሙ አመኑ።
24ሆኖም፣ ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ስለ ነበር፣ እነርሱን አላመናቸውም፤
25ደግሞም በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ ስለ ነበር፣ ማንም ስለ ሰው እንዲመሰክርለት አያስፈልገውም ነበር።