1በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፤
2ይህም ቃል ከመጀመሪያው ከእግዚአብሔር ጋር ነበር፡፡
3ሁሉም ነገር የተሠራው በእርሱ አማካይነት ነው፤ ከተሠሩት ነገሮች ሁሉ ያለ እርሱ የተሠራ አንድም ነገር አልነበረም፡፡
4በእርሱ ሕይወት ነበረ፤ያም ሕይወት የሰው ሁሉ ብርሃን ነበር፡፡
5ብርሃኑ በጨለማ ይበራል፤ ጨለማም ሊያጠፋው አልቻለም፡፡
6ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበር፡፡
7ሁሉም በእርሱ እንዲያምኑ እርሱ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ።
8ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ ዮሐንስ ራሱ ብርሃን አልነበረም፡፡
9ወደ ዓለም የሚመጣውና ለሰው ሁሉ ብርሃን ሰጭ የሆነው እውነተኛ ብርሃን እየመጣ ነበር፡፡
10እርሱ በዓለም ውስጥ ነበር፤ ዓለሙም የተሠራው በእርሱ ነው፤ ዓለም ግን አላወቀውም፤
11የራሱ ወደ ሆኑት መጣ፤ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም፡፡
12ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆንን መብት ሰጣቸው፡፡
13እነርሱም ከደምና ከሥጋ ወይም ከሰው ፈቃድ አልተወለዱም፤ ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ፡፡
14ቃል ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም ዐደረ፤ እኛም ጸጋና እውነት የተሞላውን ከአብ ዘንድ ያለውን የአንድያ ልጁን ክብር አየን፡፡
15ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ፣ «ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ ይበልጣል፤ 'ከእኔ በፊት ነበርና' ያልኋችሁ ይህ ነው» ይል ነበር፡፡
16ከእርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀበልን፤
17ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ነበር፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ በኩል መጣ፡፡
18በየትኛውም ጊዜ እግዚአብሔርን ያየው አንድም ሰው የለም፤ ነገር ግን በአባቱ ዕቅፍ ያለውና እርሱ ራሱ እግዚአብሔር የሆነው አንድያ ልጁ እርሱ እግዚአብሔርን እንዲታወቅ አደረገው፡፡
19አይሁድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን ልከው፣ «አንተ ማን ነህ?» ብለው በጠየቁት ጊዜ፣ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው፡፡
20እርሱ በግልጽ ተናገረ አልካደምም፤ ነገር ግን፣ «እኔ ክርስቶስ አይደለሁም» ብሎ መለሰላቸው።
21ስለዚህ እነርሱም፣ «ታዲያ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን?» ብለው ጠየቁት፤ እርሱ፣ «አይደለሁም» አላቸው። እነርሱ፣ «ነቢዩ ነህን?» አሉት፤ እርሱ፣ «አይደለሁም» አለ፡፡
22ከዚያም እነርሱ፣ «ለላኩን መልስ መስጠት እንድንችል፣ አንተ ማን ነህ? ስለ ራስህስ ምን ትላለህ?» አሉት፡፡
23እርሱ፣ «ልክ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለው፡- 'የጌታን መንገድ አስተካክሉ' እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ» አላቸው፡፡
24ከፈሪሳውያን የተላኩ ሰዎችም ነበሩ።
25እነርሱ፣ «ክርስቶስ፣ ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንህ፣ ታዲያ ለምን ታጠምቃለህ?» ብለው ጠየቁት፡፡
26ዮሐንስ፣ «እኔ በውሃ አጠምቃለሁ፤ ይሁን እንጂ እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሟል፤
27ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ነው፤ እኔ የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ ነኝ» በማለት መለሰላቸው፤
28ይህ ሁሉ የሆንው ዮሐንስ ሲያጠምቅ በነበረበት በዮርዳኖስ ማዶ በምትገኘው በቢታንያ ነበር፡፡
29በማግስቱ ዮሐንስ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ ተመልክቶ እንዲህ አለ፤ «እነሆ፣ የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ይኸውና!
30'ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበረ ከእኔ ይበልጣል' ብዬ ስለ እርሱ የነገርኋችሁ እርሱ ነው፡፡
31እኔ አላወቅሁትም ነበር፤ ነገር ግን እርሱ ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ እኔ በውሃ እያጠመቅሁ መጣሁ፡፡»
32ዮሐንስ እንዲህ ሲል መሰከረ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሲወርድና በእርሱ ላይ ሲያርፍ አየሁ፡፡
33እኔ አላወቅሁትም ነበር፤ ነገር ግን በውሃ እንዳጠምቅ የላከኝ እርሱ፣ 'መንፈስ ሲወርድበትና ሲያርፍበት የምታየው፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው እርሱ ነው' አለኝ፡፡
34እኔ ይህን አይቻለሁ፤ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነም መስክሬአለሁ፡፡»
35ደግሞም በማግስቱ፣ ዮሐንስ ከሁለት ደቀ መዛሙርቱ ጋር ቆሞ ሳለ፣
36ኢየሱስን በአጠገባቸው ሲያልፍ አዩት፤ ዮሐንስም፣ «እነሆ፣ የእግዚአብሔር በግ» አለ፡፡
37ሁለቱ ደቀ መዛሙርት፣ ዮሐንስ ይህን ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት፤
38ከዚያም ኢየሱስ መለስ ብሎ ሲከተሉት አየና፣ «ምን ትፈልጋላችሁ?» አላቸው፡፡ እነርሱ፣ «ረቢ የት ነው የምትኖረው?» አሉት። ረቢ ማለት 'መምህር' ማለት ነው።
39እርሱ፣ «ኑና እዩ» አላቸው፡፡ ከዚያም እነርሱ መጥተው የሚኖርበትን አዩ፤ በዚያም ቀን ዐብረውት ዋሉ፤ ሰዓቱም ዐሥረኛው ሰዓት ያህል ሆኖ ነበርና፡፡
40ዮሐንስ ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ፡፡
41እርሱ በመጀመሪያ የራሱን ወንድም ጴጥሮስን አገኘውና፣ «መሲሑን አግኝተነዋል» አለው። መሲሕ 'ክርስቶስ ማለት ነው'፡፡
42ወደ ኢየሱስም አመጣው፡፡ ኢየሱስ ጴጥሮስን ተመለከተውና፣ «አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ ኬፋ ትባላለህ» አለው። ኬፋ 'ጴጥሮስ ማለት ነው'፡፡
43በማግስቱ፣ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊሄድ በፈለገ ጊዜ፣ ፊልጶስን አግኝቶ፣ «ተከተለኝ» አለው፡፡
44ፊልጶስም ጴጥሮስና እንድርያስ ከሚኖሩበት ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበር፡፡
45ፊልጶስ ናትናኤልን አገኘውና፣ «ሙሴ በሕግ፣ ነቢያትም በትንቢት የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስ አግኝተነዋል» አለው፡፡
46ናትናኤል፣ «ከናዝሬት መልካም ነገር ይወጣልን?» አለው፡፡ ፊልጶስም መጥተህ እይ አለው፡፡
47ኢየሱስ፣ ናትናኤል ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ፣ «እነሆ፣ ተንኰል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ!» አለ።
48ናትናኤል፣ «እንዴት ታውቀኛለህ?» አለው፡፡ኢየሱስም፣ «ገና ፊልጶስ ሳይጠራህ ከበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ አየሁህ» ብሎ መለሰለት፡፡
49ናትናኤል፣ «አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ!» ብሎ መለሰለት፡፡
50ኢየሱስ፣ «ከበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ አየሁህ ስላልሁህ አመንህን? ገና ከዚህ የሚበልጡ ነገሮችን ታያለህ» ብሎ መለሰለት፡፡
51ኢየሱስ፣ «እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማያት ሲከፈቱ መላእክትም በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ» አለ፡፡