መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዮሐንስ 18

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ ከቄድሮን ሸለቆ ማዶ የአትክልት ስፍራ ወደሚገኝበት ቦታ ሄደ፣ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ አትክልት ስፍራው ገባ፡፡
2ኢየሱስ በተደጋጋሚ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደዚያ ስፍራ ይመጣ ስለ ነበር አሳልፎ ሊሰጠው ያለው ይሁዳ ቦታውን ያውቅ ነበር፡፡
3ከዚያም ይሁዳ ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን ብዙ ወታደሮችንና ጠባቂዎችን ከተቀበለ በኋላ ፋኖስ፣ ችቦና የጦር መሣሪያ ይዞ ወደ አትክልት ስፍራው መጣ፡፡
4ከዚያም እየደረሰበት ያለውን የተረዳው ኢየሱስ ወደ ፊት ወጥቶ፣ ‹‹ማንን ፈለጋችሁ?›› አላቸው፤
5እነርሱ፣ ‹‹የናዝሬቱ ኢየሱስን›› ብለው መለሱለት፡፡ ኢየሱስ፣ ‹‹እኔ ነኝ›› አላቸው፡፡ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ከወታደሮቹ ጋር ቆሞ ነበር፡፡
6ስለዚህ ‹‹እኔ ነኝ›› ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በምድር ላይ ወደቁ፡፡
7እንደ ገናም፣ ‹‹ማንን ፈለጋችሁ?›› አላቸው። እነርሱም፣ ‹‹የናዝሬቱ ኢየሱስን›› ብለው በድጋሚ መለሱለት፡፡
8ኢየሱስ፣ ‹‹እኔ ነኝ አልኋችሁ፤ ስለዚህ እኔን የምትፈልጉ ከሆነ እነዚህን እንዲሄዱ ተዉአቸው›› አላቸው፡፡
9ይህም ‹‹ከሰጠኸኝ ከእነዚህ አንዱም አልጠፋብኝም›› ተብሎ የተነገረው ቃል እንዲፈጸም ነው፡፡
10ከዚያም ስምዖን ጴጥሮስ የታጠቀውን ሰይፍ መዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፡፡ የአገልጋዩም ስም ማልኮስ ነበረ፡፡
11ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ‹‹ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፡፡ አብ የሰጠኝን ጽዋ መጠጣት የለብኝም እንዴ?›› አለው፡፡
12ስለዚህ ወታደሮቹና አዛዣቸው እንዲሁም የአይሁድ ጠባቂዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት፡፡
13በዚያን ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረው ቀያፋ ለሐና አማቹ ስለ ነበረ፣ በመጀመሪያ ወደ ሐና ወሰዱት ፡፡
14ቀያፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ቢሞት ይሻላል ብሎ አይሁድን የመከረው ሰው ነው፡፡
15ጴጥሮስና አንድ ሌላ ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከትለው ሄዱ፡፡ ሌላኛው ደቀ መዝሙር ከሊቀ ካህናቱ ጋር ይተዋወቅ ስለ ነበረ፣ ከኢየሱስ ጋር ወደ ሊቀ ካህናቱ አደባባይ ገባ፡፡
16ጴጥሮስ ግን በውጭ በር ላይ ቆሞ ነበር፡፡ ከሊቀ ካህናቱ ጋር የሚተዋወቀው ያ ደቀ መዝሙር በር የምትጠብቀውን አገልጋይ አናግሮ ጴጥሮስን ወደ ውስጥ አስገባው፡፡
17ከዚያም በር ትጠብቅ የነበረችው አገልጋይ ጴጥሮስን፣ ‹‹አንተ ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህም እንዴ?›› አለችው፡፡ እርሱ፣ ‹‹አይደለሁም›› አለ፡፡
18ጊዜው ብርድ ስለ ነበረ፣ አገልጋዮችና ጠባቂዎች እሳት አቀጣጥለው ዙሪያውን ከበው እየሞቁ ነበር፡፡ ጴጥሮስም በዚያ ከእነርሱ ጋር ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር፡፡
19ከዚያም ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ አስተማረው ትምህርት ጠየቀው፡፡
20ኢየሱስ፣ ‹‹ለዓለም ሁሉ በግልጽ ስናገር ነበር፤ ሁልጊዜ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብና በቤተ መቅደስ ሳስተምር ነበር፤ በድብቅ የተናገርሁት ምንም ነገር የለም፣
21ታዲያ ለምን ትጠይቀኛለህ? የተናገርኋቸውን ነገሮች ስለሚያውቁ ሲሰሙኝ የነበሩትን ሰዎች ስለተናገርኋቸው ነገሮች ጠይቅ›› ብሎ መለሰለት፡፡
22ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ፣ በዚያ ከቆሙት ጠባቂዎች መካከል አንዱ በጥፊ መታውና፣ ‹‹እንደዚህ ነው ለሊቀ ካህናቱ የምትመልሰው?›› አለው፡፡
23ኢየሱስ፣ ‹‹አንዳች ክፉ ነገር ተናግሬ ከሆነ መስክርብኝ፤ በትክክል መልሼ ከሆነ ግን ለምን ትመታኛለህ?›› አለው፡፡
24ሐናም ኢየሱስን እንደ ታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው፡፡
25ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት እየሞቀ ነበር። ሰዎቹ፣ ‹‹አንተ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አይደለህም እንዴ?›› አሉት። ጴጥሮስ፣ ‹‹አይደለሁም›› ብሎ ካደ፡፡
26ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ሰው ዘመድ የሆነ ከሊቀ ካህናቱ አገልጋዮች አንዱ፣ ጴጥሮስን፣ ‹‹አንተን በአትክልት ስፍራው ከእርሱ ጋር አላየሁህም እንዴ?›› አለው፡፡
27ጴጥሮስ እንደ ገና ካደ፣ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ፡፡
28ከዚያም ኢየሱስን ከቀያፋ ወደ ገዢው ግቢ ወሰዱት። ጊዜው ማለዳ ነበረ፣ ይዘውት የመጡት አይሁድ እንዳይረክሱና ፋሲካን መብላት እንዲችሉ ወደ ገዢው ግቢ መግባት አልፈለጉም።
29ስለዚህ ጲላጦስ ወደ ውጭ ወጥቶ፣ «በዚህ ሰው ላይ ያላችሁ ክስ ምንድን ነው?» ብሎ ጠየቃቸው።
30እነርሱም፣ «ይህ ሰው ክፉ ባያደርግ ኖሮ ወደ አንተ አናመጣውም ነበር» አሉት።
31ስለዚህ ጲላጦስ፣ «እናንተ ወስዳችሁ በሕጋችሁ መሠረት ፍረዱበት» አላቸው። አይሁድ፣ «እኛ ማንንም ሰው ለመግደል አልተፈቀደልንም» ብለው መለሱለት።
32ይህንም ያሉት ኢየሱስ በእንዴት ዓይነት ሞት እንደሚሞት የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።
33ጲላጦስ ወደ ግቢው ተመልሶ ኢየሱስን ጠራውና፣ «አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?» አለው።
34ኢየሱስ፣ «ይህን የምትጠይቀኝ ከራስህ ነው ወይስ ሌሎች እንድትጠይቀኝ ስለ ነገሩህ ነው?» አለው።
35ጲላጦስ፣ «እኔ አይሁዳዊ አይደለሁም፤ ነኝ እንዴ? ለእኔ አሳልፈው የሰጡህ የገዛ አገርህ ሰዎችና የካህናት አለቆች ናቸው፣ ምን አድርገህ ነው?» አለው።
36ኢየሱስ፣ «የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም፤ የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም ቢሆን ኖሮ አይሁድ እንዳይዙኝ አገልጋዮቼ ይዋጉልኝ ነበር። በመሠረቱ የእኔ መንግሥት ከምድር አይደለም» ብሎ መለሰለት።
37ጲላጦስ፣ «ታዲያ አንተ ንጉሥ ነህ?» አለው፤ ኢየሱስ፣ «እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ተናገርህ፤ የተወለድሁት ወደ ዓለምም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል» ብሎ መለሰለት።
38ጲላጦስ፣ «እውነት ምንድን ነው?» ካለ በኋላ፣ እንደ ገና ወደ አይሁድ ወጣና፣ «በዚህ ሰው ላይ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም።
39እንደ ተለመደው በየዓመቱ በፋሲካ በዓል አንድ እስረኛ እለቅላችኋለሁ፣ ታዲያ የአይሁድን ንጉሥ ልፍታላችሁን?» አላቸው።
40ከዚያም፣ እነርሱ፣ እንደ ገና ጮኸው «ይህን ሰው አይደለም፣ በርባንን ፍታልን» አሉ። በርባን ግን ወንበዴ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።