1ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ እያየ፣ ‹‹አባት ሆይ፣ ሰዓቱ ደርሷል፣ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው
2ይህም ከአንተ ለተቀበላቸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት እንዲሰጣቸው በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ በሰጠኸው ሥልጣን ልክ ነው፡፡
3ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተን፣ የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያውቁ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው፡፡
4አባት ሆይ፣ እንዳከናውነው የሰጠኸኝን ሥራ በመፈጸም በምድር ላይ አከበርሁህ፡፡
5አሁን አባት ሆይ፣ ዓለም ሳይፈጠር በፊት በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር ከአንተ ጋር አክብረኝ፡፡
6ከዓለም ለሰጠኸኝ ለእነዚህ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ፣ ለእኔም ሰጠሃቸው፣ ቃልህንም ጠብቀዋል።
7አሁን ከአንተ የተቀበልኋቸው ነገሮች ሁሉ በርግጥ ከአንተ እንደ መጡ አምነዋል፣
8የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና። እነርሱም ተቀብለውታል፤ ከአንተ እንደ መጣሁ አውቀዋል አንተ እንደላክኸኝም አምነዋል።
9እነርሱ የአንተ ናቸውና አንተ ለሰጠኸኝ ለእነርሱ እንጂ ለዓለም አልጸልይም፡፡
10የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተ የሆነውም ነገር ሁሉ የእኔ ነው፤ እኔ በእነርሱ ከብሬአለሁ፡፡
11እኔ ወደ አንተ እመጣለሁና። ከእንግዲህ በዓለም አልኖርም፤ እነርሱ ግን በዓለም ውስጥ ናቸው፡፡ ቅዱስ አባት ሆይ፣ እኔና አንተ አንድ እንደ ሆንን አንድ እንዲሆኑ በሰጠኸኝ በስምህ ጠብቃቸው፡፡
12ከእነርሱ ጋር እያለሁ በሰጠኸኝ በስምህ ጠበቅኋቸው፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት የተባለው እንዲፈጸም ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ አንዱም እንዳይጠፋ ጋረድኋቸው፡፡
13አሁን ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ይህን በዓለም ሳለሁ የምናገረው፣ ደስታዬ በእነርሱ ሙሉ እንዲሆን ነው፡፡
14ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ እነርሱም ከዓለም አይደሉምና ዓለም ይጠላቸዋል፡፡
15ከክፉው እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልጸልይም፡፡
16እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ እነርሱም ከዓለም አይደሉም፡፡
17በእውነት ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው፡፡
18አንተ ወደ ዓለም ላክኸኝ፣ እኔም ደግሞ እነርሱን ወደ ዓለም ልኬአቸዋለሁ፡፡
19እነርሱ በእውነት እንዲቀደሱ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ ቀድሼአለሁ፡፡
20ከእነርሱ ምስክርነት የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑት ሁሉ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልጸልይም፡፡
21ይህም አባት ሆይ፣ አንተ በእኔ እኔም በአንተ እንዳለሁ እነርሱም አንድ እንዲሆኑ ነው፡፡ ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ እንዲያምን እነርሱም በእኛ እንዲሆኑ እጸልያለሁ፡፡
22እኛ አንድ እንደ ሆንን እነርሱም አንድ እንዲሆኑ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ፤
23ይህም እኔ በእነርሱ አንተም በእኔ ሆነህ እነርሱ በአንድነት ፍጹማን እንዲሆኑና ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ እኔን በወደድህበት ፍቅር እነርሱንም እንደ ወደድሃቸው እንዲያውቅ ነው።
24አባት ሆይ፣ የሰጠኸኝ እነዚህ ስለ ወደድኸኝ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ የሰጠኸኝን ክብር እንዲያዩ እኔ ባለሁበት እነርሱም ከእኔ ጋር እንዲሆኑ እወዳለሁ፡፡
25ጻድቅ አባት ሆይ፣ ዓለም አላወቀህም፤ እኔ ግን አውቅሃለሁ፤ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ አውቀዋል፡፡
26አንተን እንዲያውቁ አድርጌአለሁ፤ እኔን የወደድህበት ፍቅር በእነርሱም እንዲሆንና እኔም በእነርሱ እንድሆን ስምህን አስታውቃቸዋለሁ፡፡