1«እነዚህን ነገሮች የምነግራችሁ እምነታችሁ እንዳይናወጥ ነው፡፡
2ከምኵራብ ያስወጡአችኋል፤ እናንተን የሚገድል ሁሉ ለእግዚአብሔር መልካም እንዳደረገ የሚያስብበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም፡፡
3እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉት አብንም ሆነ እኔን ስለማያውቁ ነው፡፡
4ይህን የምነግራችሁ እነርሱ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙበት ጊዜ በደረሰ ጊዜ፣ ነገሮቹን እንድታስተውሷቸውና እንዴት እንደነገርኋችሁ እንድታስቡ ነው፡፡ አብሬችሁ ስለ ነበርሁ ስለነዚህ ነገሮች ቀደም ሲል አልነገርኋችሁም፡፡
5ነገር ግን አሁን ወደ ላከኝ እመለሳለሁ፤ ያም ሆኖ ከእናንተ ማንም 'የት ነው የምትሄደው? ˋ ብሎ የሚጠይቀኝ የለም።
6ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች ስላልኋችሁ ልባችሁ በሐዘን ተሞልቷል፡፡
7ነገር ግን እውነቱን ልንገራችሁ፤ እኔ ብሄድ ይሻላችኋል፤ እኔ ካልሄድሁ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ፡፡
8አጽናኙ በመጣ ጊዜ ስለ ኃጢአት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ዓለምን ይወቅሳል፤
9ስለ ኀጢአት በእኔ ባለማመናቸው፤
10ስለ ጽድቅ እኔ ወደ አባቴ ስለምሄድና ከእንግዲህ ስለማታዩኝ፣ እንዲሁም
11ስለ ፍርድ የዚህ ዓለም ገዢ ስለ ተፈረደበት ነው፡፡
12ብዙ የምነግራችሁ ነገር አለኝ፤ ነገር ግን አሁን ልትረዱአቸው አትችሉም፡፡
13ነገር ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፣ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ ምክንያቱም እርሱ ከራሱ አይናገርም፤ ነገር ግን ከእኔ የሰማውን ሁሉ እነዚያን ይናገራል፤ ደግሞም ሊመጡ ስላሉ ነገሮች ይነግራችኋል፡፡
14የእኔ የሆኑትን ነገሮች ወስዶ ስለሚነግራችሁም ያከብረኛል፡፡
15የአባቴ የሆነው ነገር ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ ነው መንፈስ ቅዱስ የእኔ የሆኑትን ነገሮች ወስዶ ይነግራችኋል ያልኋችሁ፡፡
16ከጥቂት ጊዜ በኋላ ፈጽሞ አታዩኝም ደግሞም እንደ ገና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታዩኛላችሁ።»
17ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ እርስ በርሳቸው ‹‹ወደ አባቴ ስለምሄድ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ፈጽሞ አታዩኝም ደግሞም እንደ ገና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታዩኛላችሁˋ እያለ የሚነግረን ነገር ምንድን ነው?›› ተባባሉ፡፡
18ከዚህም የተነሣ ‹‹ከጥቂት ጊዜ በኋላˋ ሲል ምን ማለቱ ነው። ምን እያለ እንደ ሆነ አናውቅም›› አሉ፡፡
19ኢየሱስም ሊጠይቁት በጣም እንደ ፈለጉ አይቶ፣ ‹‹ከጥቂት ጊዜ በኋላ ፈጽሞ አታዩኝም ደግሞም እንደ ገና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታዩኛላችሁˋ ስላልሁት ነገር እርስ በርሳችሁ ትጠያየቃላችሁን?
20እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ እናንተ ታለቅሳለችሁ ታዝናላችሁም፤ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተ በሐዘን ትሞላላችሁ፣ ነገር ግን ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል፡፡
21አንዲት ሴት የመውለጃዋ ወራት በደረሰ ጊዜ፣ የምጧን ሥቃይ እያሰበች ታዝናለች፤ ነገር ግን ከወለደች በኋላ ሕፃን ወደዚህ ዓለም በመምጣቱ ከሚሰማት ደስታ የተነሣ ጭንቀቷን ፈጽሞ አታስበውም፡፡
22ደግሞም አሁን ዐዝናችኋል፤ ነገር ግን ተመልሼ አያችኋለሁ፤ ልባችሁም ደስ ይለዋል፤ ደስታችሁንም ማንም ከእናንተ ሊወስድ አይችልም፡፡
23በዚያም ቀን ምንም ጥያቄ አትጠይቁኝም፤ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ከአብ ዘንድ ማንኛውንም ነገር ብትለምኑ አብ ስለስሜ ይሰጣችኋል፡፡
24እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፣ ለምኑ፣ ደስታችሁም ሙሉ ይሆን ዘንድ ትቀበላላችሁ፡፡
25እስከ አሁን በምሳሌ ስነግራችሁ ነበር፤ ነገር ግን በምሳሌ የማልናገርበትና ለእናንተ ስለ አብ በግልጽ የምናገርበት ጊዜ ይመጣል፡፡
26በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ ወደ አብ እለምናለሁ አልላችሁም፤
27ምክንያቱም አብ ራሱ እኔን ስለወደዳችሁኝና ከአብ ዘንድ እንደ መጣሁ ስላመናችሁ ይወዳችኋልና ነው፡፡
28ከአብ ወደዚህ ዓለም መጥቻለሁ፤ እንደ ገናም ይህን ዓለም ትቼ ወደ አብ እሄዳለሁ፡፡»
29ደቀ መዛሙርቱ፣ ‹‹እነሆ፣ አሁን በግልጽ ተናገርህ፤ ምንም በምሳሌ አልተናገርህም፡፡
30አሁን ሁሉን እንደምታውቅና ማንም ጥያቄ ሊጠይቅህ እንደማያስፈልግ አውቀናል። በዚህም ምክንያት አንተ ከአብ እንደ መጣህ እናምናለን» አሉት፡፡
31ኢየሱስ፣ ‹‹አሁንስ አመናችሁ ማለት ነው?››
32እነሆ፣ እያንዳንዳችሁ እኔን ብቻዬን ትታችሁ ወደየቤታችሁ የምትበታተኑበት ጊዜ እየመጣ ነው፡፡ አዎን፣ በርግጥም መጥቷል፡፡ ነገር ግን አብ ከእኔ ጋር ስላለ ብቻዬን አይደለሁም፡፡
33በስሜ ሰላም እንዲሆንላችሁ እነዚህን ነገሮች ነግሬአችኋለሁ፡፡ በዓለም ውስጥ ስትኖሩ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዟችሁ፣ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ፡፡»