1እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬው ደግሞ አባቴ ነው።
2እርሱም በእኔ ላይ ያለውን ፍሬ ያማያፈራውን ማንኛውንም ቅርንጫፍ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውን ግን ይበልጥ ያፈራ ዘንድ ያጠራዋል።
3ከነገርኋችሁ ቃል የተነሣ እናንተ ንጹሓን ናችሁ።
4በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ላይ ካልኖረ በቀር በራሱ ፍሬ ማፍራት እንደማይችል ሁሉ፣ እናንተም በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ማፍራት አትችሉም።
5እኔ የወይን ግንድ ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ የምኖርበት ያ ሰው ብዙ ፍሬ ያፈራል። ያለ እኔ ምንም ነገር ልታደርጉ አትችሉም።
6ማንም ሰው በእኔ ባይኖር፣ እንደ ቅርንጫፍ ይወገዳል፣ ይደርቃልም፤ ሰዎች ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉታል፣ ይቃጠላልም።
7በእኔ ብትኖሩ፣ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ፣ የምትፈልጉትን ማንኛውንም ነገር ለምኑ ይሰጣችኋል።
8ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል።
9አብ እንደ ወደደኝ እኔም ወደድኋችሁ፣ በፍቅሬ ኑሩ።
10እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደጠበቅሁና በፍቅሩ እንደምኖር ሁሉ እናንተም ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ።
11ደስታዬ በውስጣችሁ እንዲሆንና ደስታችሁም ፍጹም እንዲሆን እነዚህን ነገሮች ነግሬአችኋለሁ።
12እኔ የምሰጣችሁ ትእዛዝ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው።
13ስለ ወዳጁ ሲል ሕይወቱን አሳልፎ እንዲሰጥ ግድ ከሚል የሚበልጥ ፍቅር ማንም ሰው የለውም።
14ያዘዝኋችሁን ነገር ብታደርጉ ወዳጆቼ ናችሁ።
15ከእንግዲህ አገልጋዮች ብዬ አልጠራችሁም፤ ምክንያቱም አገልጋይ ጌታው ምን እያደረገ እንዳለ አያውቅም። ከአባቴ የሰማሁትን ነገር ሁሉ እንድታውቁ ስለ ነገርኋችሁ፣ ወዳጆች ብያችኋለሁ።
16እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ ነገር ግን እኔ መረጥኋችሁ፤ ሄዳችሁ ፍሬ እንድታፈሩ፣ ፍሬአችሁም ዘላቂ ሆኖ እንዲቆይ ሾምኋችሁ። ይህም አብን በስሜ የምትለምኑትን ማንኛውንም ነገር እንዲሰጣችሁ ነው።
17እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ይህን ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ።
18ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ ዕወቁ።
19ከዓለም ብትሆኑ ኖሮ ዓለም የራሱ እንደሆኑት አድርጎ በወደዳችሁ ነበር። ነገር ግን ከዓለም ስላይደላችሁ ከዓለምም ስለ መረጥኋችሁ ዓለም ይጠላችኋል።
20'አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም' በማለት የነገርኋችሁን ቃል ልብ በሉ፤ እኔን አሳድደውኝ ከሆነ፣ እናንተንም ያሳድዷችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው ከሆነ፣ የእናንተንም ቃል ይጠብቃሉ።
21የላከኝን እርሱን ስለማያውቁ፣ በስሜ ምክንያት ይህን ሁሉ ያደርጉባችኋል።
22እኔ ባልመጣና ባልነግራቸው ኖሮ ኀጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ ነገር ግን አሁን ለኀጢአታቸው የሚሰጡት ምክንያት የለም።
23እኔን የሚጠላ አባቴንም ይጠላል።
24ማንም ያልሠራውን ሥራ በመካከላቸው ሠርቼ ባላሳያቸው ኖሮ ኀጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ሥራዬን አይተዋል፤ እኔንና አባቴንም ጠልተዋል።
25ይህም የሆነው በሕጋቸው 'በከንቱ ጠሉኝ' ተብሎ የተጻፈው ቃል እንዲፈጸም ነው።
26ከአብ የምልክላችሁ አጽናኝ፣ እርሱም ከአብ የሚወጣው የእውነት መንፈስ በሚመጣበት ጊዜ፣ ስለ እኔ ይመሰክራል።
27ከመጀመሪያ ጀምሮ ከእኔ ጋር ስለ ነበራችሁ፣ እናንተም ትመሰክራላችሁ።