1በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ከፋሲካ በዓል በፊት ከዚህ ዓለም ተለይቶ ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ ስላወቀ፣ ቀድሞውኑ የሚወዳቸውን በዓለም ይኖሩ የነበሩትን የራሱን ወገኖች እስከ መጨረሻው ወደዳቸው።
2ዲያብሎስም ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ ይሁዳ ልብ ክፉ ዐሳብ አስገባ።
3ኢየሱስ አብ ሁሉን ነገር በእጁ አሳልፎ እንደ ሰጠው፣ ከእግዚአብሔር እንደ መጣ ወደ እግዚአብሔርም ተመልሶ እንደሚሄድ ዐወቀ፤
4ከእራት ላይ ተነሣ፤ መጎናጸፊያውንም አስቀመጠ፤ ከዚያም ፎጣ ወስዶ ወገቡ ላይ ከታጠቀ በኋላ
5በሳሕን ውስጥ ውሃ ጨምሮ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠብና በያዘውም ፎጣ ማበስ ጀመረ።
6ወደ ስምዖን ጴጥሮስ መጣ፤ ጴጥሮስም «ጌታ ሆይ የእኔን እግር ልታጥብ ነውን?» አለው
7ኢየሱስም «የማደርገውን አሁን አይገባህም፤ወደፊት ግን ትረዳዋለህ» በማለት መለሰለት
8ጴጥሮስም «ፈጽሞ የእኔን እግር አታጥብም» አለው ኢየሱስም «እግርህን ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ አይኖርህም» ሲል መለሰለት
9ስምዖን ጴጥሮስም «ጌታ ሆይ እንግዲያስ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንና ራሴንም እጠበኝ» አለው
10ኢየሱስም «ገላውን የታጠበ እግሩን ብቻ ከመታጠብ በስተቀር ሌላ ሰውነቱ ንጹህ ነው፤ እናንተ ንጹሓን ናችሁ ነገር ግን ይህን ስል ሁላችሁንም ማለቴ አይደለም»
11ኢየሱስ «ሁላችሁም ንጹህ አይደላችሁም» ያለው ኣሳልፎ የሚሰጠው ማን እንደሆነ ያውቅ ስለነበረ ነው
12ኢየሱስ እግራቸውን አጥቦ ከጨረሰ በኋላ ልብሱን ለብሶ ተቀመጠ፤ እነርሱንም፣ «ያደረግሁላችሁን ልብ ብላችኋል?
13'መምህር' እና 'ጌታ' ትሉኛላችሁ። እንደዚያም ስለሆንሁ አባባላችሁ ትክክል ነው።
14እኔ ጌታና መምህር ሆኜ እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባል።
15እኔ እንዳደረግሁላችሁ እንደዚያው ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ትቼላችኋለሁ።
16እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም ወይም የተላከ ሰው ከላኪው አይበልጥም።
17እነዚህን ነገሮች ብታውቁና ብታደርጓቸው የተባረካችሁ ናችሁ።
18የምናገረው ሁላችሁን በሚመለከት አይደለም፤ የመረጥኋቸውን አውቃለሁና፣ ነገር ግን እንደዚህ የምናገረው እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ የሚለው የመጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም ነው።
19ከመሆኑ በፊት አስቀድሜ የምነግራችሁ በሚፈጸምበት ጊዜ እኔ እንደሆንሁ እንድታምኑ ነው።
20እውነት እውነት እላችኋለሁ እኔን የሚቀበል የላክሁትን ይቀበላል፤ እኔን የተቀበለ ደግሞ የላክኝን ይቀባላል»
21ኢየሱስ ይህን በሚናገርበት ጊዜ በመንፈሱ ታወከ፤ «እውነት እውነት እላችኋለሁ ከእናንተ መካከል አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል» ብሎ በግልጽ ነገራቸው
22ደቀ መዛሙርቱም ስለማን እየተናገረ እንደሆነ ስላልገባቸው እርስ በርስ ተያዩ።
23ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የሆነው ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር ወደ ደረቱ ተጠግቶ ተቀምጦ ነበር።
24ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደዚህ ደቀ መዝሙር ጠጋ ብሎ «ንገረን ለመሆኑ ስለ ማን ነው እየተናገረ ያለው?» በማለት ጠየቀው።
25ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ የተቀመጠው ደቀ መዝሙርም፣ «ጌታ ሆይ፣ ይህ የምትለው ሰው ማን ነው?» ብሎ ጠየቀው።
26ከዚያም ኢየሱስ፣ «ይህን ቍራሽ እንጀራ ከወጭቱ አጥቅሼ የምሰጠው ያ ሰው እርሱ ነው» በማለት መለሰለት። ስለዚህ ቍራሹን እንጀራ አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ይሁዳ ሰጠው።
27ቍራሹንም እንጀራ ከተቀበለ በኋላ፣ ሰይጣን ገባበት። ከዚያም ኢየሱስ፣ «ለማድረግ ያሰብኸውን ፈጥነህ አድርግ» አለው።
28ኢየሱስ ለይሁዳ እንደዚያ ለምን እንዳለው በማዕድ ላይ ከተቀመጡት ማንም ያወቀ የለም።
29አንዳንዶቹ ይሁዳ ገንዝብ ያዥ ስለ ነበር፣ ኢየሱስ «ለበዓሉ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ግዛ» ወይም ለድኾች ገንዘብ ስጥ ብሎ ነግሮታል ብለው ዐሰቡ።
30ይሁዳ ቍራሹን እንጀራ ከተቀበለ በኋላ፣ ፈጥኖ ወጣ ምሽትም ነበረ።
31ይሁዳ በሄደ ጊዜ፣ ኢየሱስ እንዲህ በማለት ተናገረ፤ «አሁን የሰው ልጅ ከብሯል፣ እግዚአብሔርም በእርሱ ከብሯል።
32እግዚአብሔር በራሱ ያከብረዋል፣ ደግሞም ፈጥኖ ያከብረዋል።
33ልጆች ሆይ፣ ከእንግዲህ ከእናንተ ጋር የምቆየው ለጥቂት ጊዜ ነው። እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፣ ይሁን እንጂ፣ ለአይሁድ፣ 'እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም' እንዳልኋቸው፣ ለእናንተም የምናገረው እንደዚያ ነው።
34እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ዐዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።
35እርስ በርሳችሁም ብትዋደዱ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ ሰዎች በዚህ ያውቃሉ።»
36ስምዖን ጴጥሮስ «ጌታ ሆይ፣ ወዴት ልትሄድ ነው?» ሲል ጠየቀው። ኢየሱስ፣ «ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፣ በኋላ ግን ትከተለኛለህ» በማለት መለሰለት።
37ጴጥሮስ፣ «ጌታ ሆይ፣ አሁን ልከተልህ የማልችለው ለምንድን ነው? ስላንተ ሕይወቴን እንኳ አሳልፌ ለመስጠት ቈርጫለሁ» አለው።
38ኢየሱስ፣ «ስለ እኔ ሕይወትህን አሳልፈህ ትሰጣለህን? እውነት፣ እውነት እልሃለሁ፣ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ» ብሎ መለሰለት።