መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዮሐንስ 12

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የፋሲካ በዓል ሊከበር ስድስት ቀናት ሲቀሩት ኢየሱስ ከሞት ያስነሣው አልዓዛር ወደ ነበረበት ወደ ቢታንያ መጣ፡፡
2ስለዚህ በዚያ እራት አዘጋጁለት፣ አልዓዛር ከኢየሱስ ጋር በማዕድ ከተቀመጡት ጋር ሲሆን ማርታ ደግሞ ታገለግላቸው ነበር፡፡
3ማርያም ከንጹሕ ናርዶስ የተሠራ በጣም ውድ የሽቱ ብልቃጥ ወስዳ የኢየሱስን እግር ትቀባ፣ በፀጉሩዋም ታብስ ስለነበር፣ ቤቱ በሽቱው መዓዛ ታወደ፡፡
4ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ፣
5“ይህ ሽቱ በሦስት መቶ ዲናር ተሸጦ ለድሆች ያልተሰጠው ለምንድን ነው?” አለ፡፡
6ይህን ያለው ለድሆች ተገዶላቸው ሳይሆን ሌባ ስለነበረ ነው፤ የገንዘብ ከረጢቱን የሚይዘው እርሱ ስለነበረ፣ ከዚያ ውስጥ ለራሱ ጥቂት ይወስድ ነበር፡፡
7ኢየሱስ፣ “የያዘችውን ለቀብሬ ቀን እንድታቆየው ፍቀዱላት፤
8ድሆች ምንጊዜም ከእናንተ ጋር ይሆናሉ፣ እኔን ግን ሁልጊዜ አታገኙኝም” አላቸው፡፡
9ብዙ የአይሁድ ሕዝብም ኢየሱስ በዚያ እንደነበረ ተረድተው ነበርና ወደዚያ መጡ፣ የመጡትም ለኢየሱስ ብቻ ብለው ሳይሆን ኢየሱስ ከሞት ያስነሣውን አልዓዛርንም ለማየት ጭምር ነበር፡፡
10የካህናት አለቆች አልዓዛርን ደግሞ ለመግደል በአንድነት የተንኮል ስምምነት አደረጉ፣
11ምክንያቱም ብዙ አይሁድ የሄዱትና በኢየሱስ ያመኑት ከእርሱ የተነሣ ነበር፡፡
12በማግስቱ ብዙ ሕዝብ ወደ በዓሉ መጡ። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም መምጣቱን በሰሙ ጊዜ፣
13የዘንባባ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው፣ “ሆሣዕና! በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው” እያሉ ሊቀበሉት ወጡ፡፡
14ኢየሱስ የአህያ ውርንጫ አገኘና ተቀመጠባት፣ ይህንን ያደረገው፣
15“የጽዮን ልጅ ሆይ፣ አትፍሪ፣ እነሆ፣ ንጉሥሽ በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ይመጣል” ተብሎ በተጻፈው መሠረት ነው፡፡
16ደቀ መዛሙርቱ በመጀመሪያ ይህን አልተረዱም ነበር፣ ኢየሱስ በከበረ ጊዜ ግን እነዚህ ነገሮች ስለ እርሱ ተጽፈው እንደነበረና እነርሱም እነዚህን ነገሮች ለእርሱ እንዳደረጉለት ተገነዘቡ፡፡
17ኢየሱስ አልዓዛርን ከመቃብር በጠራውና ከሞት ባስነሣው ጊዜ በዚያ የነበሩት ሕዝብም ለሌሎች መሰከሩላቸው፡፡
18ይህን ምልክት እንዳደረገ ሰምተው ነበርና ሊቀበሉት የወጡትም በዚህ ምክንያት ነበር፡፡
19ስለዚህ ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው፣ “ምንም ማድረግ እንደማትችሉ ተመልከቱ፣ ዓለሙ ተከትሎታል” ተባባሉ፡፡
20በበዓሉ ሊያመልኩ ከሄዱት መካከል አንዳንድ የግሪክ ሰዎችም ነበሩ፡፡
21እነዚህ በገሊላ ካለችው ከቤተሳይዳ ወደ ሆነው ወደ ፊልጶስ ዘንድ ሄደው፣ “ጌታ ሆይ፣ ኢየሱስን ማየት እንፈልጋለን” አሉት፡፡
22ፊልጶስ ሄዶ ለእንድርያስ ነገረው፣ እንድርያስና ፊልጶስም ዐብረው ሄዱና ለኢየሱስ ነገሩት፡፡
23ኢየሱስም፣ “የሰው ልጅ የሚከብርበት ሰዓት ደርሷል፤
24እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ የስንዴ ዘር ወደ ምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ከሞተች ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች፡፡” ብሎ መለሰላቸው፡፡
25ሕይወቱን የሚወድ ያጠፋታል፤ ነገር ግን በዚህ ዓለም እያለ ሕይወቱን የሚጠላ ለዘላለም ሕይወት እንድትጠበቅ ያደርጋታል።
26ማንም ሊያገለግለኝ የሚወድ ይከተለኝ፤ እኔ ባለሁበት አገልጋዬም በዚያ ይሆናል። ማንም ቢያገለግለኝ አብ ያከብረዋል።
27አሁን ነፍሴ ታውካለች ምን እላለሁ? 'አባት ሆይ፣ ከዚህ ሰዓት አድነኝ' ነገር ግን ስለዚህ ጉዳይ ወደዚህ ሰዓት መጥቻለሁ።
28አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው።» ከዚያም ከሰማይ፣ «አክብሬዋለሁ ደግሞም አከብረዋለሁ» የሚል ድምፅ መጣ።።
29ባጠገቡ ቆመው የነበሩትና ድምፁን የሰሙት ብዙ ሕዝብ ነጐድጓድ መሰላቸው። ሌሎች ደግሞ «መልአክ ተናግሮታል» አሉ።
30ኢየሱስ መልሶ፣ «ይህ ድምፅ የመጣው ስለ እኔ ሳይሆን ስለ እናንተ ነው» አለ።
31በዚህ ዓለም ላይ የሚፈረድበት ጊዜ አሁን ነው፤ አሁን የዚህ ዓለም ገዢ ወደ ውጭ ይጣላል።
32እኔ ከምድር ከፍ ከፍ በምልበት ጊዜ፣ ሰውን ሁሉ ወደ ራሴ እስባለሁ።»
33ይህን የተናገረው በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚሞት ለማመልከት ነበር።
34ሕዝቡ፣ «ክርስቶስ ለዘላለም እንደሚኖር ከሕጉ ሰምተናል። ታዲያ 'የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ማለት አለበት እንዴት ትላለህ?' ይህስ የሰው ልጅ ማን ነው?» ብለው መለሱለት።
35ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ «አሁን ለጥቂት ጊዜ ብርሃን በመካከላችሁ አለ፤ ጨለማ እንዳይውጣችሁ በዚህ ብርሃን ተመላለሱ። በጨለማ የሚመላለስም ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም።
36የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃኑ እያለላችሁ በብርሃኑ እመኑ።» ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ ከእነርሱ ተለየ፤ ተሰወረባቸውም።
37ምንም እንኳ ኢየሱስ በሕዝቡ ፊት ብዙ ምልክቶችን ቢያደርግም በእርሱ አላመኑም።
38ይህም ነቢዩ ኢሳይያስ፣ «ጌታ ሆይ የተናገርነውን ማን አመነ? የጌታስ ክንድ ለማን ተገለጠ?» በማለት የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው።
39በዚህም ምክንያት ማመን አልቻሉም፤ ኢሳይያስ እንደ ገና እንዲህ ብሏልና፤
40«ዐይኖቻቸውን አሳውሯል፤ ልባቸውንም አደንድኗል፤ ይህም የሆነው በዐይናቸው ዐይተው በልባቸው አስተውለውና ተመልሰው እንዳልፈውሳቸው ነው።»
41ኢሳይያስ እነዚህን ነገሮች የተናገረው የኢየሱስን ክብር ስላየና ስለ እርሱም ስለ ተናገረ ነው፤
42የሆነ ሆኖ ከገዢዎች እንኳ ብዙዎች በኢየሱስ አምነዋል፤ ነገር ግን ፈሪሳውያን ከምኵራብ እንዳያግዷቸው በመፍራት ማመናቸውን አልገለጹም።
43በእግዚአብሔር ከመመስገን ይልቅ በሰዎች ለመመስገን ወደዱ።
44ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ «በእኔ የሚያምን በእኔ ብቻ የሚያምን ሳይሆን በላከኝም ያምናል፤
45እንደዚሁም እኔን የሚያይ የላከኝንም ያያል።
46በእኔ የሚያምን በጨለማ ውስጥ እንዳይኖር ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤
47ማንም ቃሌን ሰምቶ ባያደርገው የምፈርድበት እኔ አይደለሁም፤ ዓለምን ለማዳን እንጂ በዓለም ላይ ልፈርድ አልመጣሁምና።
48እኔን የሚቃወምና ቃሌንም የማይቀበል የሚፈርድበት አለ፤ በመጨረሻው ቀን የሚፈርድበት እኔ የተናገርሁት ቃል ነው።
49ምክንያቱም ይህ ቃል ከራሴ የተናገርሁት አይደለም፤ ይልቁን ምን እንደምልና እንደምናገር ትእዛዝ የሰጠኝ የላከኝ አብ ነው።
50ትእዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደሚያስገኝ አውቃለሁ፤ ስለዚህ የምናገረው ቃል አብ እንደ ነገረኝ የምናገረው ነው።»
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።