1አልዓዛር የተባለ አንድ ሰውም ታሞ ነበር። እርሱም ማርያምና እኅትዋ ማርታ በሚኖሩበት መንደር በቢታንያ ይኖር ነበር።
2ወንድምዋ የታመመባትም የጌታ ኢየሱስን እግር ሽቱ የቀባችውና በጠጕርዋ ያበሰችው ናት።
3ከዚያም እኅትማማቹ፣ ‹‹እነሆ፣ የምትወደው ታሞአልና በፍጥነት ድረስ›› በማለት ወደ ኢየሱስ ላኩበት።
4ኢየሱስ መልእክቱን በሰማ ጊዜ፣ ‹‹ይህ የእግዚአብሔር ልጅ እንዲከብርበት ለእግዚአብሔር ክብር የሚሆን ነው›› አለ።
5ኢየሱስ ማርታንና እኅቷን እንዲሁም አልዓዛርን ይወድ ነበር፡፡
6ስለሆነም አልዓዛር መታመሙን በሰማ ጊዜ፣ ኢየሱስ በነበረበት ቦታ ሁለት ተጨማሪ ቀናት ቆየ፡፡
7ከዚህ በኋላም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ወደ ይሁዳ ዳግመኛ እንሂድ” አላቸው፡፡
8ደቀ መዛሙርቱ፣ “መምህር ሆይ፣ አይሁድ አሁን ሊወግሩህ ነበር፣ እንደ ገና ወደዚያ ተመልሰህ ትሄዳለህን?” አሉት፡፡
9ኢየሱስም፣ “በአንድ ቀን ውስጥ አሥራ ሁለት የብርሃን ሰዓታት አሉ አይደለምን? አንድ ሰው በቀን የሚራመድ ከሆነ የቀኑን ብርሃን ስለሚመለከት፣ አይደናቀፍም፡፡
10በሌሊት የሚራመድ ከሆነ ግን ብርሃኑ በእርሱ ውስጥ ስለሌለ፣ ይደናቀፋል፡፡”
11ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ተናገረ፣ ከእነዚህም ነገሮች በኋላ፣ “ወዳጃችን አልዓዛር አንቀላፍቷል፣ እኔ ግን ከእንቅልፉ ላነቃው እሄዳለሁ” አላቸው፡፡
12ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ፣ “ጌታ ሆይ፣ ተኝቶስ ከሆነ ይድናል” አሉት፡፡
13ኢየሱስም የተናገረው አልዓዛር ስለ መሞቱ ነበር፣ እነርሱ ግን ዕረፍት ለማድረግ ስለ መተኛቱ የተናገረ መስሎአቸው ነበር፡፡
14ከዚያም ኢየሱስ በግልጽ፣ “አልዓዛር ሞቷል
15እናንተ ታምኑ ዘንድ እኔ እዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ብሎኛል” አላቸው፡፡
16ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ ባልደረቦቹ ደቀ መዛሙርትን፣ “ከኢየሱስ ጋር እንሞት ዘንድ እኛም ከእርሱ ጋር እንሂድ” አላቸው፡፡
17ኢየሱስ በመጣ ጊዜ፣ አልዓዛር በመቃብር ውስጥ አራት ቀን መቆየቱን ተረዳ፡፡
18ቢታንያ አሥራ አምስት ኪሎ ሜትር ብቻ የምትርቅ ለኢየሩሳሌም ቅርብ ስፍራ ነበረች፡፡
19ስለ ወንድማቸው ሞት ሊያጽናኗቸው ከአይሁድ ብዙዎቹ መጥተው ነበር፡፡
20ከዚያም ማርታ ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ፣ ልትቀበለው ወጣች፣ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር፡፡
21ከዚያም ማርታ ኢየሱስን፣ “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትኖር ኖሮ ወንድሜ ባልሞተም ነበር፡፡
22አሁንም ቢሆን የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ ዐውቃለሁ” አለችው፡፡
23ኢየሱስ፣ “ወንድምሽ ይነሣል” አላት፡፡
24ማርታ፣ “በመጨረሻው ቀን በሚሆነው በትንሣኤ ከሞት እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” አለችው፡፡
25ኢየሱስ፣ “እኔ ትንሣኤና ሕይወት ነኝ፣ በእኔ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፡፡
26በእኔ የሚኖርና የሚያምንብኝ ሁሉ ፈጽሞ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽን?” አላት፡፡
27እርሷም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፣ አንተ ወደ ዓለም ልትመጣ ያለኸው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ አምናለሁ” አለችው፡፡
28ማርታ ይህን ከተናገረች በኋላ እኅቷን ማርያምን በግል ለማነጋገር ትጠራት ዘንድ ሄደችና፣ “መምህሩ እዚህ ነው፣ ሊያነጋግርሽ ይፈልጋል” አለቻት፡፡
29ማርያም ይህን እንደ ሰማች በፍጥነት ተነሥታ ወደ ኢየሱስ ሄደች፡፡
30ኢየሱስም ማርታን ባገኘበት ስፍራ ነበር እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር፡፡
31ከዚያም በቤት ውስጥ ሆነው ማርያምን ሲያጽናኗት የነበሩት አይሁድ ፈጥና ስትወጣ ባዩአት ጊዜ፣ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሏቸው ተከተሏት፡፡
32ከዚያም ማርያም ኢየሱስ ወደ ነበረበት መጥታ ስታየው በእግሩ ሥር ወድቃ፣ “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው፡፡
33ኢየሱስ እርሷና ዐብረዋት የነበሩት አይሁድ ሲያለቅሱ ተመልክቶ በመንፈሱ ቃትቶና ተጨንቆ፣
34“ወዴት አኖራችሁት?” አላቸው፡፡ እነርሱም፣ “ጌታ ሆይ፣ መጥተህ እይ” አሉት፡፡
35ኢየሱስ አለቀሰ፡፡
36ከዚያም አይሁድ፣ “አልዓዛርን ምን ያህል ይወደው እንደ ነበረ ተመልከቱ!” አሉ፡፡
37ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን፣ “ዓይነ ስውር የነበረውን ሰውዬ ዓይን የከፈተ ይህ ሰው የሞተውን ይህን ሰው እንዳይሞት ማድረግ አይችልም ነበር?” አሉ፡፡
38ከዚያም ኢየሱስ አሁንም በውስጡ እየቃተተ ወደ መቃብሩ ሄደ፡፡ መቃብሩ ዋሻ ነበረ፣ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር፡፡
39ኢየሱስ፣ “ድንጋዩን አንሡት” አለ፡፡ የሟቹ የአልዓዛር እኅት ማርታም ኢየሱስን፣ “ከሞተ አራት ቀን ስለሆነው፣ በአሁኑ ጊዜ ገላው ይበሰብሳል” አለችው፡፡
40ኢየሱስ ማርታን፣ “ብታምኚስ፣ የእግዚአብሔርን ክብር እንደምታዪ አልነገርሁሽምን” አላት፡፡
41ስለዚህ ድንጋዩን አነሡት፡፡ ኢየሱስም ሽቅብ እየተመለከተ፣ “አባት ሆይ፣ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ፤
42ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ ዐውቃለሁ፣ ነገር ግን ይህን ያልሁት አንተ እንደላክኸኝ ያምኑ ዘንድ እዚህ በዙሪያዬ ስለቆመው ሕዝብ ነው” አለ፡፡
43ይህን ካለ በኋላ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “አልዓዛር ሆይ፣ ውጣ!” አለ፡፡
44የሞተው ሰው እጁና እግሩ በመገነዣ ጨርቅ እንደ ተጠቀለለ፣ ፊቱም በጨርቅ እንደ ተሸፈነ ወጣ፡፡ ኢየሱስ፣ “ፍቱትና ይሂድ” አላቸው፡፡
45ከዚያም ወደ ማርያም ከመጡትና ይህን ከተመለከቱት አይሁድ አብዛኛዎቹ በእርሱ አመኑ፤
46ነገር ግን ከእነርሱ አንዳንዶቹ ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገሯቸው፡፡
47ከዚያም ሊቀ ካህናቱና ፈሪሳውያን ጉባዔ ጠርተው፣ “ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶችን እያደረገ ነው፡፡
48እንደዚሁ የምንተወው ከሆነ፣ ሮማውያን መጥተው ስፍራችንና አገራችንንም ይወስዳሉ” አሉ፡፡
49ሆኖም በዚያ ዓመት ሊቀ ካህን የነበረ ከእነርሱ መካከል ቀያፋ የተባለው አንዱ፣ “እናንተ ምንም አታውቁም፤
50አገሪቱ በመላ ከምትጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ቢሞት የተሻለ እንደሆነ ከግምት ውስጥ አላስገባችሁም” አላቸው፡፡
51እርሱ ይህን የተናገረው ከራሱ አልነበረም፣ ይልቁንም በዚያ ዓመት ሊቀ ካህን ስለ ነበረ፣ ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ፣
52ደግሞም ስለ ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በልዩ ልዩ ስፍራ የተበታተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ይሰበስብ ዘንድ መሞት እንደሚገባው ትንቢት ተናገረ፡፡
53ስለዚህ ከዚያ ቀን ጀምሮ ኢየሱስን እንዴት መግደል እንዳለባቸው ዕቅድ አወጡ፡፡
54ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ በአይሁድ መካከል በግልጽ መውጣትና መግባቱን ትቶ ኤፍሬም ወደ ተባለው በበረሐው አጠገብ ወዳለው ከተማ ሄደ፡፡ እዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ቈየ፡፡
55የአይሁድ የፋሲካ በዓልም ቀርቦ ነበረና ብዙዎች ራሳቸውን ያነጹ ዘንድ ከፋሲካው በፊት ከየገጠሩ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር፡፡
56ኢየሱስን እየፈለጉት፣ በቤተ መቅደስ ቆመው ሳሉ፣ “ምን ይመስላችኋል? ወደ በዓሉ አይመጣ ይሆን?” እያሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር፡፡
57ሊቀ ካህናቱና ፈሪሳውያኑም ኢየሱስን ይይዙት ዘንድ እርሱ የት እንዳለ ያወቀ ማንኛውም ሰው ጥቆማ እንዲያቀርብ ትእዛዝ አስተላለፉ፡፡