1በዚያን ዘመን፥ የይሁዳን ነገሥታት አጥንትና የመኳንንቶቹን አጥንት፥ የካህናቱን አጥንትና የነቢያቱን አጥንት፥ የኢየሩሳሌምንም ሰዎች አጥንት ከመቃብራቸው ያወጣሉ ይላል እግዚአብሔር።
2በተከተሉአቸው፣ ባገለገሏቸውና በፈለጉአቸው፣ ባመለኳቸውም በፀሐይና በጨረቃ በሰማይም ሠራዊት ሁሉ ፊት ይዘረጉአቸዋል። አጥንቶቻቸው አይሰባሰቡም ወይም በድጋሚ አይቀበሩም። በምድር ፊት ላይ እንደ ጕድፍ ይሆናሉ።
3እኔም ባሳደድኋቸው ስፍራ ሁሉ የቀሩት፣ ከዚህ ክፉ ሕዝብ የተረፉት ቅሬታዎች ሁሉ፣ ከሕይወት ይልቅ ሞትን ይመርጣሉ ይላል የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር።
4እንዲህም ትላቸዋለህ፣ 'እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የትኛውም የወደቀ ሰው አይነሣምን? የጠፋስ ለመመለስ አይሞክርምን?
5ይህ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ዘላቂ በሆነ አለመታመን ስለ ምን ወደ ኋላው ይመለሳል? ተንኰልን ይዞአል ንስሃ ለመግባትም እንቢ ብሎአል።
6አደመጥሁ ሰማሁም፣ ትክክለኛ ነገር አልተናገሩም፤ ማንም ስለ ክፋቱ ንስሃ አልገባም፣ ማንም "ምን አድርጌአለሁ?" አላለም። ወደ ጦርነት እንደሚሮጥ ፈረስ ሁላቸውም በየመንገዳቸው ሄዱ።
7ሽመላ በሰማይ ትክክለኛ ጊዜዋን አውቃለች፤ ዋኖስና ጨረባ ዋልያም ያውቃሉ። እነርሱ ወደ ሚሰደዱበት የሚሄዱት በትክክለኛ ጊዜ ነው፣ ሕዝቤ ግን የእግዚአብሔርን ፍርድ አላወቁም።
8እናንተስ፣ "ጥበበኞች ነን! የእግዚአብሔርም ሕግ ከእኛ ጋር ነው" እንዴት ትላላችሁ? በእርግጥ ተመልከቱ! የአታላይ ጸሐፊ ብዕር ማታለልን አድርጎአል።
9ጥበበኞች ያፍራሉ። ደንግጠውማል ተጠምደዋል። ተመልከቱ! የእግዚአብሔርን ቃል ጥለዋል፣ ስለዚህ ጥበባቸው ምን ጥቅም አለው?
10ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ስስታሞች ናቸውና፣ ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉ ያታልላሉና፣ ስለዚህ ሚስቶቻቸውን ለሌሎች፥ እርሻቸውንም ለሚወርሱባቸው እሰጣለሁ።
11ቀላል ነገር እንደሆነ በማድረግ የሕዝቤን ሴት ልጅ ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ። ሰላም ሳይሆን፣ "ሰላም፣ ሰላም" ይላሉ።
12አስጸያፊ ነገርን ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም። ትሕትናም አልነበራቸውም። ስለዚህ በሚቀጡ ጊዜ ቀድሞውኑ ከወደቊት ጋር ይወድቃሉ ይላል እግዚአብሔር።
13ፈጽሜ አጠፋችኋለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ በወይን ላይ ፍሬ፣ በበለስ ዛፍ ላይ በለስ አይሆንም። ቅጠልም ይረግፋልና የሰጠኋቸውም ያልፋልና።
14ለምን ዝም ብለን እንቀመጣለን? በአንድነት ኑ፤ ወደ ተመሸጉ ከተሞች እንሂድ፣ በዚያም በሞት ዝምተኞች እንሆናለን። እግዚአብሔር ዝም ያሰኘናልና። ስለ በደልነው መርዝ አጠጥቶናል።
15ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፣ ነገር ግን መልካም ነገር አልተገኘም። የፈውስ ጊዜን በተስፋ ተጠባበቅን፣ ነገር ግን ሽብር እንደሆነ ተመልከቱ።
16የፈረሰኞች ድምጽ ከዳን ተሰማ። ከአርበኞች ፈረሶች ማሽካካት የተነሣ ምድር ሁሉ ተንቀጠቀጠች። ምድሪቱንና በእርስዋም ያለውን ሁሉ፥ ከተማይቱንና የሚኖሩባትንም ሊበሉ ይመጣሉና።
17ተመልከቱ፣ አስማት የማይከለክላቸውን እባቦችንና እፉኝቶችን እሰድድባችኋለሁ። እነርሱም ይነድፉአችኋል" ይላል እግዚአብሔር።
18ኅዘኔ ፍጻሜ የለውም፣ ልቤም ታምሞአል።
19ተመልከቱ! እግዚአብሔር በጽዮን የለምን? ወይስ ንጉሥዋ በእርስዋ ዘንድ የለምን? የሚል የሕዝቤ ሴት ልጅ ጩኸት ድምፅ ከሩቅ ምድር ተሰማ። በተቀረጹ ምስሎቻቸውና በባዕድ ከንቱ ጣዖታት ያስቈጡኝ ስለ ምንድር ነው?
20መከሩ አልፎአል፣ በጋው አብቅቷል። እኛ ግን አልዳንነም።
21በሕዝቤ ሴት ልጅ ስብራት እኔ ተሰብሬአለሁ። በደረሰባት ነገር በጭንቀት አለቅሳለሁ፤ ጠቁሬማለሁ።
22በገለዓድ መድኃኒት የለምን? ወይስ በዚያ ፈዋሽ የለምን? የሕዝቤ ሴት ልጅ ፈውስ ስለ ምን አልሆነም?