1ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው፣
2በእግዚአብሔር ቤት በራፍ ላይ ቁም! እንዲህ በል፣ 'ይሁዳ ሁሉ ሆይ፣ እግዚአብሔርን ልታመልኩ በእነዚህ በራፎች የምትገቡ ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
3የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መንገዳችሁንና ሥራችሁን መልካም አድርጉ፣በዚህም ስፍራ መኖር እንድትቀጥሉ አደርጋችኋለሁ።
4ራሳችሁን አታላይ በሆኑ ቃሎች ላይ ታምናችሁ፣ "የእግዚአብሔር መቅደስ! የእግዚአብሔር መቅደስ! የእግዚአብሔር መቅደስ!" አትበሉ።
5መንገዳችሁንና ሥራችሁን ፈጽማችሁ መልካም ብታደርጉ፤ በሰውና በጎረቤቱ መካከል ቅን ፍርድ ብትፈርዱ፤
6በምድሪቱ የሚቆየውን እንግዳ፣ ወላጅ አልባውን፣ ወይም መበለቲቱንም ባትበዘብዙ፣ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን ባታፈስሱ፣ ለገዛ ጉዳታችሁ እንዲሆንባችሁ ሌሎች አማልክትን ባትከተሉ፤
7ያን ጊዜ ከጥንቱ ጊዜ ጀምሮ እስከ ለዘላለም ለአባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር በዚህ ስፍራ አሳድራችኋለሁ።
8እነሆ! በማይረዳችሁ የሐሰት ቃል እየታመናችሁ ናችሁ።
9ትሰርቃላችሁ፣ ትገድላላችሁ፣ ታመነዝራላችሁ? ደግሞም በሐሰትም ትምላላችሁ፣ ለበኣልም ታጥናላችሁ፣ የማታውቋቸውንም ሌሎች አማልክት ትከተላላችሁ?
10ከዚያም መጥታችሁ ስሜም በተጠራበት በዚህ ቤት በፊቴ ቆማችሁ፣ እነዚህን ሁሉ ጥፋቶች ማድረግ እንድትችሉ "ድነናል፣" አላችሁ።
11ይህስ ስሜ የተጠራበት ቤት በዓይናችሁ ፊት የሌቦች ዋሻ ሆኖአልን? ነገር ግን፣ እነሆ፣ እኔ አይቻለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር።
12'ስለዚህ በቀድሞ ዘመን ስሜን ከመጀመሪያ ወዳሳደርሁበት በሴሎ ወደ ነበረው ስፍራዬ ሂዱ፣ ከሕዝቤም ከእስራኤል ክፋት የተነሣ ያደረግሁበትን እዩ።
13ስለዚህ አሁንም፣ ይህን ሥራችሁን ሁሉ ስላደረጋችሁ፣ በተደጋጋሚ ጊዜ ተናገርኳችሁ፣ እናንተ ግን አልሰማችሁም። በጠራኋችሁም ጊዜ፣ አልመለሳችሁም።
14ስለዚህ፣ በሴሎ እንዳደረግሁ፣ እንዲሁ ስሜ በተጠራበት በምትታመኑበት ቤት፣ ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ስፍራ ላይ እንዲሁ አደርጋለሁ።
15የኤፍሬምንም ዘር የሆኑትን ወንድሞቻችሁን ሁሉ እንደ ጣልሁ፣ እንዲሁ ከፊቴ እጥላችኋለሁ።
16ደግሞም አንተ፣ ኤርምያስ አልሰማህምና ለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፣ ስለ እነርሱም ልመናና ጸሎት አታድርግ፣ አትማልድላቸው።
17እነርሱ በይሁዳ ከተሞች ውስጥና በኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ላይ የሚያደርጉትን አታይምን?
18ያስቈጡኝ ዘንድ፣ ለሰማይ ንግሥት እንጐቻ እንዲያደርጉ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቍርባን እንዲያፈስሱ፣ ልጆች እንጨት ይሰበስባሉ፣ አባቶችም እሳት ያነድዳሉ፣ ሴቶችም ዱቄት ያቦካሉ።
19በእውነት እኔን ያስቈጣሉን? ይላል እግዚአብሔር፤ ለእነርሱስ እፍረት እንዲሆንባቸው የሚያስቆጡት ራሳቸውን አይደለምን?
20እንግዲያው ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'ተመልከቱ፣ ቍጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ ላይ ይፈስሳል፣ በሰውና በአውሬው ላይ፣ በዱር ዛፎችና በምድር ፍሬ ላይ ይፈስሳል። ይነድዳል፣ መቼም አይጠፋም።'
21የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 'ለመሥዋዕታችሁ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን ጨምሩ፣ ከዚያም ላይ ሥጋውን ጨምሩ።
22አባቶቻችሁን ከግብጽ ምድር ባወጣኋቸው ቀን፣ የትኛውንም ነገር ከእነርሱ አልጠየቅሁም። ስለሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ሌላ መሥዋዕት አላዘዝኋቸውምም።
23ይህንን ትእዛዝ ብቻ ሰጠኋቸው፣ "ቃሌን ስሙ፣ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ። መልካምም ይሆንላችሁ ዘንድ ባዘዝኋችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ።"
24ነገር ግን በክፉ ልባቸው አሳብና እልከኝነት ሄዱ ወደ ፊትም ሳይሆን ወደ ፊታቸው ሳይሆን ወደ ኋላቸው ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም።
25አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፣ አገልጋዮቼን፣ ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር። እነርሱን ተግቼ ላክሁባችሁ።
26ነገር ግን አልሰሙኝም። ምንም ትኩረት አልሰጡም። ይልቊን፣ አባቶቻቸውም ካደረጉት ይልቅ የባሰ አደረጉ።
27እነዚህን ቃሎች ሁሉ ንገራቸው፣ ነገር ግን አይሰሙህም። እነዚህን ነገሮች አውጅላቸው፣ ነገር ግን አይመልሱልህም።
28የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቃል ያልሰማ፣ ተግሣጽንም ያልተቀበለ ሕዝብ ይህ ነው። እውነት ጠፍቶአል ከአፋቸውም ተቈርጦአል በላቸው።
29ፀጕርሽን ቍረጪ፣ ተላጪው፣ ጣዪውም። በወናዎች ኮረብቶችም ላይ ሙሾን አውጪ። እግዚአብሔር በቍጣው ይህንን ትውልድ ጥሎአልና፣ ትቶታልምና ።
30የይሁዳ ልጆች በፊቴ ክፉን ነገር ሠርተዋል፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ያረክሱትም ዘንድ ስሜ በተጠራበት ቤት ርኵሰታቸውን አኑረዋል።
31ከዚያም ቶፌት ውስጥ በቤን ሄኖም ሸለቆ መስገጃዎችን ገነቡ። እኔም ያላዘዝሁትንና ፈጽሞ በልቤ ያላሰብሁትን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ዘንድ ይህንን አድርገዋል።
32ስለዚህ፣ ተመልከቱ፣ ቶፌት ወይም የቤን ሄኖም ሸለቆ ተብሎ ዳግመኛ አይጠራም። የእርድ ሸለቆ ይባላል፤ የሚተርፍ ስፍራ እስኪታጣ ድረስ በቶፌት በድኖችን ይቀብራሉ ይላል እግዚአብሔር።
33የዚህም ሕዝብ ሬሳ ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል፣ የሚያስፈራራቸውም አይኖርም።
34ምድሪቱም ወና ትሆናለችና ከይሁዳ ከተሞችና ከኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ላይ የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፣ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ አጠፋለሁ።