መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኤርሚያስ 50

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እግዚአብሔር ስለ ከለዳውያን ምድር ስለ ባቢሎን በነቢዩ በኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው፣
2"በአሕዛብ መካከል ተናገሩና እንዲሰሙ አድርጉ። ዓላማውን አንሡና እንዲሰሙ አውሩ። አትደብቁት። 'ባቢሎን ተወሰደች። ቤል አፈረ። ሜሮዳክ ደነገጠ። ጣዖቶችዋ አፈሩ። ምስሎችዋ ደነገጡ' በሉ።
3ሕዝብ ከሰሜን ወጥቶባታል ምድርዋንም ባድማ ያደርጋል፣ የሚቀመጥባት እንዳይገኝባት። ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ በውስጥዋ አይኖሩም። ሸሽተው ሄደዋል።
4በእነዚያም ወራት፣ በዚያም ጊዜ፣ ይላል እግዚአብሔር፣ የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች በአንድነት ሆነው እያለቀሱና አምላካቸውን እግዚአብሔርን እየፈለጉ ይመጣሉ።
5ፊታቸውንም ወደጽዮን አቅንተው ይሄዳሉ። ከቶ በማይረሳ በዘላለም ቃል ኪዳን ወደ እግዚአብሔር ሄደው ራሳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ያገኛኛሉ።
6ሕዝቤ የጠፉ በጎች ሆነዋል። እረኞቻቸው በተራሮች ላይ አስተው አቅበዘበዟቸው፤ ከኮረብታ ወደ ኮረብታ አለፉ። ሄዱ፣ የኖሩበትንም በረታቸውን ረሱ።
7ሲሄዱባቸው ያገኙአቸው ሁሉ በሉአቸው። ጠላቶቻቸውም፣ 'በጽድቅ ማደሪያ በእግዚአብሔር ላይ፣ በአባቶቻቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ላይ፣ ኃጢአት ስለ ሠሩ እኛ አልበደልንም' አሉ።
8ከባቢሎን መካከል ሽሹ፤ ወደ ከከለዳውያን ድር ውጡ፤ በመንጎችም ፊት እንደ አውራ ፍየሎች ሁኑ።
9ተመልከቱ፣ ከሰሜን ምድር የታላላቅ አሕዛብን ጉባኤ አስነሣለሁ በባቢሎንም ላይ አመጣቸዋለሁ። በእርስዋም ላይ ይሰለፋሉ። ባቢሎን ከዚያ ስፍራ ትወሰዳለች። ፍላጾቻቸውም ባዶውን እንደማይመለስ እንደ ተካነ ተዋጊ ፍላጻ ናቸው።
10የከላውዴዎንም ምድር ትበዘበዛለች። የሚበዘብዙአትም ሁሉ ይጠግባሉ፣ ይላል እግዚአብሔር።
11ርስቴን የምትበዘብዙ እናንተ፣ ደስ ይበላችሁ፤ በመስክ ላይም እንዳለች ጊደር ሆናችሁ ሐሤት እያደረጋችሁ ዝለሉ፤ እንደ ብርቱ ፈረሶች አሽካኩ።
12እንዲሁ እናታችሁ በእጅጉ ታፍራለች፤ የወለደቻችሁም ትጐሰቍላለች። ተመልከቱ፣ በአሕዛብ መካከል አነስተኛይቱ ትሆናለችና፣ ምድረ በዳና ደረቅ ምድር፣ በረሀም ትሆናለች።
13ከእግዚአብሔር ቍጣ የተነሣ ባድማ ትሆናለች እንጂ ሰው አይኖርባትም። በባቢሎንም በኩል የሚያልፍ ሁሉ ይደነቃል፣ በመጣባትም መቅሠፍት ሁሉ ያፍዋጫል።
14በባቢሎን ላይ በዙሪያዋ ተሰለፉ። እናንተ ቀስትን የምትገትሩ ሰዎች ሁሉ። በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርታለችና ወርውሩባት ፍላጾችንም አትመልሱ።
15የእግዚአብሔር በቀል ነውና ድል እያደረጋችሁ በዙሪያዋ ጩኹባት። እጅዋን ሰጠች፤ ግንቦችዋ ወደቁ፣ ቅጥሮችዋም ፈረሱ ይህ የእግዚአብሔር በቀል ነውና። እርስዋን ተበቀሉ! እንደ ሠራችውም ሥሩባት።
16ዘሪውንና በመከር ጊዜ ማጭድ የሚይዘውን ከባቢሎን አጥፉ። ከሚያስጨንቅ ሰይፍ ፊት እያንዳንዱ ወደ ወገኑ ይመለሳል እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሸሻል።
17እስራኤል ባዝኖ የተበተነ በግ እና አንበሶች ያሳደዱት ነው። መጀመሪያ የአሦር ንጉሥ በላው፤ በመጨረሻም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አጥንቱን ቈረጠመው።
18ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተመልከቱ፣ የአሦርን ንጉሥ እንደ ቀጣሁ፣ እንዲሁ የባቢሎንን ንጉሥና ምድሩን እቀጣለሁ።
19እስራኤልንም ወደ ማሰማርያ ምድሩ እመልሳለሁ፤ በቀርሜሎስና በባሳንም ላይ ይሰማራል። በኤፍሬም ተራራና በገለዓድ ላይ ይጠግባል።
20በእነዚያም ቀኖች፣ በዚያ ጊዜ፣ እነዚህን ያስቀረኋቸውን ይቅር እላቸዋለሁና፣ ይላል እግዚአብሔር፣ የእስራኤል በደል የይሁዳም ኃጢአት ይፈለጋል ምንም አይገኝም።"
21"በምራታይም ምድር ላይ፣ በፋቁድም በሚኖሩት ላይ ተነሥና ውጣ፤ ግደላቸው ፈጽመህም አጥፋቸው፤ ይላል እግዚአብሔር፣ እንዳዘዝሁህም ሁሉ አድርግ።
22የሰልፍና የታላቅ ጥፋት ውካታ በምድሪቱ ላይ አለ።
23የምድር ሁሉ መዶሻ እንዴት ደቀቀ እንዴትስ ተደመሰሰ። ባቢሎንስ በአሕዛብ መካከል እንዴት መሸበሪያ ሆነች።
24ባቢሎን ሆይ፣ አጥምጄብሻለሁ። አንቺም ሳታውቂ ተይዘሻል፤ ከእኔ ከእግዚአብሔር ጋር ስለ ተዋጋሽ ተገኝተሻል ተይዘሽማል።
25እግዚአብሔር ዕቃ ቤቱን ከፍቶ የቍጣውን ዕቃ ጦር አውጥቶአል። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በከለዳውያን ምድር ይሠራ ዘንድ ሥራ አለውና።
26ከየበኩሉ በእርስዋ ላይ ጥቃትን ፈጽሙ። ጎተራዎችዋንም ክፈቱ። እንደ ክምርም አድርጓት፣ ፈጽማችሁም አጥፉአት። አንዳችም አታስቀሩላት።
27ወይፈኖችዋን ሁሉ እረዱ። ወደ መታረድም ስፍራ ላኳቸው። ቀናቸው፣ የመቀጣታቸው ጊዜ፣ ደርሶአልና ወዮላቸው!
28የአምላካችንን የእግዚአብሔርን በቀል፣ የመቅደሱንም በቀል በጽዮን ይነግሩ ዘንድ ሸሽተው ከባቢሎን አገር ያመለጡት ሰዎች ድምፅ ተሰምቶአል።"
29ቀስትን የሚገትሩትን ቀስተኞችን ሁሉ በባቢሎን ላይ ጥሩአቸው። በዙሪያዋ ስፈሩባት፣ አንድም አያምልጥ። በእስራኤል ቅዱስ ላይ በእግዚአብሔር ላይ ኰርታለችና እንደ ሥራዋ መጠን መልሱላት። እንዳደረገችም ሁሉ አድርጉባት።
30ስለዚህ ጐበዛዝትዋ በአደባባይዋ ላይ ይወድቃሉ፣ በዚያም ቀን ሰልፈኞችዋ ሁሉ ይጠፋሉ፣ ይላል እግዚአብሔር።"
31ትዕቢተኛው ሆይ፣ አንተን የምቀጣበት ጊዜ፣ ቀንህ ደርሶአልና በአንተ ላይ ነኝ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
32ስለዚህ ትዕቢተኞቹ ተሰናክለው ይወድቃሉ። የሚያነሣቸው ማንም አይኖርም። በከተሞቻቸውም ውስጥ እሳት አነድዳለሁ፤ በዙሪያቸው ያለውን ሁሉ ትበላለች።
33የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች በአንድነት ተጨቊነዋል። የማረኳቸውም ሁሉ አሁን ድረስ በኃይል ይዘዋቸዋል፤ ይለቅቁአቸውም ዘንድ እንቢ ብለዋል።
34የሚቤዣቸው ብርቱ ነው። ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። ምድርንም ያሳርፍ ዘንድ፣ በባቢሎንም የሚኖሩትን ያውክ ዘንድ ሙግታቸውን ፈጽሞ ይሟገታል።
35ሰይፍ በከለዳውያንና በባቢሎን በሚኖሩ ላይ፣ በአለቆችዋና በጥበበኞችዋ ላይ አለ፣ ይላል እግዚአብሔር።
36ጥንቆላን በሚናገሩት ላይ ሰይፍ አለ፣ ራሳቸውን ሰነፎች አድርገው ይገልጣሉ። ሰይፍም በጦረኞችዋ ላይ አለ፣ እነርሱም በሽብር ይሞላሉ።
37ሰይፍ በፈረሶቻቸውና በሰረገሎቻቸው ላይ በመካከልዋም ባሉት በልዩ በልዩ ሕዝብ ሁሉ ላይ አለ፣ እነርሱም እንደ ሴቶች ይሆናሉ። ሰይፍ በቤተ መዛግብቷ ላይ አለ፣ ለብዝበዛም ይሆናል።
38እርስዋ የተቀረጹ ምስሎች ምድር ናት፣ እነርሱም በጣዖታት ይመካሉና ድርቅ በውኆችዋ ላይ ይሆናል እነርሱም ይደርቃሉ።
39ስለዚህ የምድረ በዳ አራዊት ከተኵላዎች ጋር ይኖሩባታል፣ ሰጐኖችም ይኖሩባታል፤ ሰውም ከዚያ ወዲያ ለዘላለም አይኖርባትም፣ እስከ ልጅ ልጅም ድረስ የሚኖርባት የለም።
40ሰዶምንና ገሞራን በአጠገባቸውም የነበሩትን ከተምች እግዚአብሔር እንደ ገለበጣቸው፣ ይላል እግዚአብሔር፣ እንዲሁ ሰው በዚያ አይኖርም የሰውም ልጅ አይኖርባትም።"
41"ተመልከቱ፣ ሕዝብ ከሰሜን ይመጣል፣ ታላቅ ሕዝብና ብዙ ነገሥታትም ከምድር ሩቅ ዳርቻዎች ይነሣሉ።
42ቀስትንና ጦርን ይይዛሉ። ጨካኞች ናቸው ምሕረትም አያደርጉም። ድምፃቸው እንደ ባሕር ይተምማል፣ በፈረሶችም ላይ ይቀመጣሉ፤ የባቢሎን ሴት ልጅ ሆይ፣ ለሰልፍ እንደ ተዘጋጀ ሰው እያንዳንዳቸው በአንቺ ላይ ተሰለፉ።
43የባቢሎን ንጉሥ ወሬአቸውን ሰምቶአል፣ እጁም ዝላ ደክማለች። ጭንቀትም ይዞታል፣ ምጥ ወላድ ሴትን እንደሚይዛት ጭንቀት ይዞታል።
44ተመልከቱ! ከእርስዋ ዘንድ በቶሎ አባርራቸዋለሁና በጠነከረው አምባ ላይ ከዮርዳኖስ ትዕቢት ውስጥ እንደ አንበሳ ይወጣል። የተመረጠውንም በእርስዋ ላይ እሾመዋለሁ። እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ወይስ ለእኔ ጊዜ የሚወስን ማን ነው? ወይስ ፊቴን የሚቃወም እረኛ ማን ነው?
45ስለዚህ እግዚአብሔር በባቢሎን ላይ የመከረባትን ምክር፣ በከለዳውያንም ምድር ላይ ያሰባትን አሳብ ስሙ። በእውነት የመንጋ ትናንሾች ሳይቀሩ ይጎተታሉ። በእውነት ማደሪያቸውን ባድማ ያደርግባቸዋል።
46ከባቢሎን መያዝ ድምፅ የተነሣ ምድር ተናወጠች፤ ጩኸትም በአሕዛብ መካከል ዘንድ ተሰማ።"
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።